1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢድ ሙባረክ

ሐሙስ፣ ሰኔ 30 2008

«እስልምና እና የኢትዮጵያ ታሪክ ከመጀመርያዉ እስልምና በአረብያ መሰበክ ከጀመረበት ነብዩ መሐመድ በነብይነት ለሰዉ ልጆችን አስተምራለሁ ብለዉ ከተነሱበት ወይም ደግሞ ከተላኩበት ጊዜ ጀምሮ ነዉ ትስስሩ የሚጀምረዉ። »

https://p.dw.com/p/1JLOy
Deutschland Arabische Flüchtlinge feiern Zuckerfest
ምስል DW/N. Yakine

[No title]

እንኳን ለኢድ ኧልፈጥር በዓል አደረሳችሁ፤ በእስልምና ኃይማኖት ታሪክ ባህል ላይ ምርምር የሚያደርጉና በኃይማኖቱ ዙርያ በርካታ መፃሕፍትን የፃፉ እንዲሁም ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ዉስጥ የሕዝብ ግንኙነት ዋና ኃላፊ ሆነዉ ያገለገሉት አቶ ሃሰን ታጅን የተናገሩት ነበር።

በአለም ዙርያ በሚገኙ ሙስሊሞች ዘንድ የተከበረዉ የኢድ ኧልፈጥር በዓል በጀርመን በሚገኙት ምዕመናንም ዘንድ በድምቀት ነዉ የተከበረዉ። የእስልምና ጉዳይ ላይ ምርምር በማድረግ በርካታ መጽሐፍትን ለአንባብያን ያበቁት ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ዉስጥ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆነዉ ያገለገሉት አቶ ሃሰን ታጅን፤ ኢድ ኧልፈጥር በዓል ከረመዳን ጋር የተያያዘ ነዉ ረመዳን ደግሞ የወር ስም ነዉ ሲሉ ያስረዳሉ፤

« በቅድምያ ለመላዉ የሙስሊም ኅብረተሰብና ለመላዉ የሃገራችን ሕዝቦች እንኳን ለኢድ ኧልፈጥር በዓል አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቼን እገልጻለሁ። ኢድ ኧልፈጥር ማለት ከረመዳን ጾም ጋር የተያያዘ በዓል ነዉ። ረመዳን የወር ስም ነዉ። ዘጠነኛዉ የአረብኛ የወር ስም ነዉ፤ ጾሙም የተሰየመዉ በወሩ ስም ነዉ። እስልምና ዉስጥ ሁለት አይነት ጾሞች አሉ። የግዴታና፤ በበጎ ፍላጎት የሚፈፀሙ ጾሞች ናቸዉ። ረመዳን በግዴታ የሚፈፀም ጾም ነዉ። ማንኛዉም ለአካለ መጠን የደረሰና ጤነኛ የሆነ ሙስሊም ሁሉ ረመዳንን ይጾማል። ከዚህ ጾም ጋር የተያያዘዉ በዓል ኢድ ኧልፈጥር ይባላል። በእስልምና ሦስት ዋና ዋና በዓላት አሉ፤ አንደኛዉ ኢድ ኧልፈጥር ይባላል፤ ሁለተኛዉ ኢድ ኧልአዳህ ይባላል። ኢድ ኧልአዳህ ከሃጅ ስርዓት ጋር የተያያዘዉ በዓል ነዉ። ሦስተኛዉ የነብዩ መሃመድ የልደት በዓል ወይም መዉሊድ ነዉ። እነዚህ ከእስልምና ሃይማኖት ጋር ተያይዘዉ በአገራችን በኢትዮጵያ ብሔራዊ በዓል ሆነዉ ይከበራሉ። »

Berlin Hamburg Sporthalle Festgebet zum Ende des Fastenmonats Ramadan
ምስል picture-alliance/dpa/L. Schulze

ለኢድ ኧልፈጥር በዓል አፈጻፀም ስርዓትስ ምን ይመስላል፤ ለሚለዉ የእስልምና ጉዳይ ላይ ምርምር በማድረግ በርካታ መጽሐፍትን ለአንባብያን ያበቁት ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ዉስጥ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆነዉ ያገለገሉት አቶ ሃሰን ታጅን፤ በመቀጠል እንዳስረዱት፤

«በኢድ ኧልፈጥር በዓል ጠዋት 12 አካባቢ ሰዉ ከቤት ለመዉጣት ሲዘጋጅ አንድ ነገር ቀምሶ መዉጣት ይኖርበታል። በዓሉ የሚፈፀመዉ ሜዳ ላይ ነዉ። ሰዉ ሕጻን አዋቂዉ አዳዲስ ልብሶች ለብሶ፤ ሽቶ ተቀብቶ በተቻለዉ መጠን ተዉቦ ነዉ ወደ አከባበር ስርዓቱ ላይ የሚሄደዉ። በዓል በሚከበርበት ቦታ ላይ መጀመርያ የስግደት ፕሮግራም ይፈፀማል፤ ከዝያም ስግደቱን የመራዉ አካል ንግግር ያደርጋል፤ እርስ በርስ ስለመተዛዘን ስለመረዳዳት ስለ ርህራሄ ስለበጎነት ሰበካዎች ይካሄዳሉ፤ ከዝያ ሰዉ ወደ ቤቱ ይመለስና፤ ለበዓሉ የተዘጋጀዉን ከቤተ-ዘመድ ጋር ይቋደሳል። »

የራድዮ ጣብያችን በሚገኝበት በቦንና አካባቢዋ የሚገኙ ሙስሊሞች ከዛሪ ሦስት ዓመት በፊት ያቋቋሙትና ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ በጀርመን መንግሥት እዉቅና የተሰጠዉ «ነጃሺ ኢትዮ-ጀርመን ሙስሊሞች ማኅበር» አባላት ቤተሰብና ልጆቻቸዉን በማገናኘት በጋራ በድምቀት አክብረዋል። የማኅበሩ ምክትል ሰብሳቢ ሆነዉ የሚያገለግሉት አቶ በክሪ ሃሰን፤ ጾሙን በጋራ እንዳሳለፉ ነግረዉናል።

ኢትዮጵያ በእስልምና ታሪክ ዉስጥ ቀዳሚዉን ስፍራ ይዛ ያለች ሃገር እንደሆነች ይሰማል እስቲ በኢትዮጵያ የእስልምና ታሪክን ይገሩኝ ? በሃረር ነዋሪ እንደነበሩ የነገሩን የአሁንዋ የአዲስ አበባ ነዋሪ አልፍያ አብዱረሃብ፤ ትናንት በክብረ በዓሉ ዕለት ቀትር ላይ እንኳን አደረሶዎት ስንል ደዉለንላቸዉ ነበር ። በረመዳን ፆም ወቅትም ሆነ በክብረ በዓሉ የኢትዮጵያ ሙስሊሙ ኅብረተስብ የተቸገሩትን በመደገፍ በመርዳት ከቤተሰብ ጎረቤት ጋር በፍቅር ያሳልፋል። በኢትዮጵያ የእስልምና ታሪክ ጥንታዊነትን የሚያስረዱን አቶ ሃሰን ታጅን፤

Äthiopien Addis Abeba Fastenbrechen Eid al-Fitr Gebet
ምስል Reuters

« እስልምና እና የኢትዮጵያ ታሪክ ከመጀመርያዉ እስልምና በአረብያ መሰበክ ከጀመረበት ነብዩ መሐመድ በነብይነት ለሰዉ ልጆችን አስተምራለሁ ብለዉ ከተነሱበት ወይም ደግሞ ከተላኩበት ጊዜ ጀምሮ ነዉ ትስስሩ የሚጀምረዉ። ነብዩ መሐመድ ሁለት የሕይወት እርከኖች አልዋቸዉ። መካዊና መዲናዊ የታሪክ እርከኖች ይባላሉ። መካዊ የሚባለዉ የታሪክ ርከናቸዉ መካ ዉስጥ ከተነሱበት ከተወለዱበት እትብታቸዉ ከተቀበረበት፤ ማስተማር ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ያሉትን 13 ዓመታት ያካትታል። እነዛ 13 ዓመታት የስቃይ ዓመታት ናቸዉ። ሕዝባቸዉ አልተቀበላቸዉም፤ በሳቸዉንና በባልደረቦቻቸዉ ላይ ከፍተኛ እንግልት ይፈፀም ነበር። በዚህም እነዚያ 13 ዓመታት የመከራ ዓመታት ናቸዉ። ያን የመከራ ዓመታት ለማለፍ ከተጠቀሙባቸዉ መንገዶች አንዱ ባልደረቦቻቸዉን ወደ ሃበሻ መላክ ነዉ። በዝያ ወቅት ሁለት ጊዜ ነዉ ስደት የተደረገዉ፤ አንደኛ የሃበሻ ስደትና ሁለተኛ የሃበሻ ስደት ተብሎ ይታወቃል ፤ እናም ነብዩ መሐመድ ባልደረቦቻቸዉን ሲልኩዋቸዉ ያሉት ሃበሻ ዉስጥ ፍትኃዊ ንጉስ አለ፤ ከሱ ዘንድ ከሄዳችሁ በሰላም ትኖራላችሁ፤ አትበደሉም፤ ግፍ አይፈጸምባችሁም፤ ኃይማኖታችሁን በነጻነት ማከናወን ትችላላችሁ፤ የሚል መልክት አስይዘዉ ወደ ሃበሻ ላክዋቸዉ። ገና ጥሪ ከጀመሩ ሦስተኛዉ ዓመት አካባቢ የመጀመርያዉ ቡድን ቀጥሎ አገር ሰላም የሆነ መስሎአቸዉ ወደ መካ ሲመለሱ የባሰ ስቃይ ሲገጥማቸዉ ሁለተኛዉ ቡድን በርካታ ስደተኞችን ይዞ ወወደ ሃበሻ ከመጡት ሰዎች መካከል የነብዩ መሃመድ ሴት ልጅና አማቻቸዉ የልጃቸዉ ባልም ነበር። ሌሎችም ለሳቸዉ በጣም ቅርብ የሆኑ ሰዎችም ነበሩ ።

እንደተባለዉም ኢትዮጵያ ዉስጥ ወይም ሃበሻ ላይ በአክሱማዊት ዘመነ መንግሥት ኃይማኖታቸዉን ይዘዉ በሰላም ነዉ የኖሩት ። እነዚህ ስደተኞች ወደ ሃገራቸዉ ከተመለሱ በኋላ ስለ ሃበሻ ሁኔታ ስለ ሃበሻ ንጉስ ስለ ሃገሪዉዉ ያስተላለፉት መልክት ቢኖር ኃይማኖታቸዉን በሰላም ማከናወናቸዉን ጥሩ ሃገር እንደሆነች መስክረዉ ነዉ ያለፉት ። ከዝያን ጊዜ ጀምሮ ሃበሾች በነብዩ መሐመድ ዙርያ ጠፍተዉ አያዉቁም። በየትኛዉም ወቅት ነብዩ መሐመድ በሚያጋጥማቸዉ እክል ሁሉ ሃበሾች፤የኛ ወገኖች አብረዉ ከሳቸዉ ጋር ይኖሩ ነበር።ለምሳሌ ኡሁድ በተባለዉ ዉግያ ጊዜ ማለትም ነብዩ መሐመድ ወደ መዲና ወደምትባለዉ ቦታ ከተሰደዱ በኋላ የመካ ወገኖቻቸዉ 500 ኪሎ ሚትር ላይ በሳቸዉና በተከታዮቻቸዉ ላይ ወረራ አድርገዉባቸዉ ነበር። በዚያን ጊዜ አንድ የአበሻ ልዑክ እሳቸዉ ጋር ደርሶ ስለነበር የሳቸዉን ሕይወት ለማትረፍ አበሾች ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል። የሚገርመዉ የነብዩ መሐመድ ባልደረቦች ድሆች ጎስቋሎች ነበሩ። በዝያን ጊዜ ደግሞ ሃበሾች በኃብት ከአረቦች በተሻለ የስልጣኔ ደረጃ ላይ ሁሉ ነበርን ወደ ሃገራቸዉ መጥተዉ ምግብ አልባሳት እዝያ ላሉ ችግረኞች ያደሉበት ሁኔታ ሁሉ አለ። ነብዩ መሐመድን ያሳደገቻቸዉ ሴት በረካ ትባላለች፤ ሃበሻ ናት፤ የመጀመርያዉ ነብዩ መሐመድ ጥሪያቸዉን ሊጀምሩ ከአማኞች መካከል አንዱ ቢላል ይባላል፤ በኋላ ላይ የአዛን ጥሪ ሃላፊ አድርገዉታል፤ ይህ በአሁኑ አገላለጽ የማስታወቅያ ሚኒስቴር እንደማለት ነዉ።

Saudi-Arabien, Masjid al-Nabaw Moschee
ምስል picture alliance/AA/O. Bilgin

ሌሎችም ብዙ ሃበሾች ከነብዩ መሐመድ ጋር እንደነበሩ ይታወቃል። አሁንም ቢሆን የነብዩ መሐመድን መካነ መቃብር ጢስ መማጨስ በማጽዳትና በመንከባከብ እስካሁን ድረስ ቁልፉ ያለዉ በአበሾች እጅ ነዉ። ጥብቅ ትስስር ነዉ ያለን ይህን ዉለታ ነብዩ መሐመድ ራሳቸዉ አልረሱም አንድ ጊዜ 33 አባላት ያሉት የአበሻ ልዑክ ወደ እሳቸዉ ይሄዳል ፤ እሳቸዉ መዲና የሚባለዉ ቦታ ላይ ንጉስ ከሆኑ በኋላ ያስተናገድዋቸዉ ራሳቸዉ ናቸዉ ሌሎች መልክተኞች ሲመጡ ግን የነብዩ መሐመድ ባለሟሎች ናቸዉ የሚያስተናግዷቸዉ የነበረዉ። የአበሻ መልክተኛ ሲመጣ ነብዩ መሐመድ ባለሟሎች እንዲያስተናግዷቸዉ አልፈቀዱም። ነብዩ መሐመድ ራሳቸዉ ቆመዉ ነበር የክብር ምግብ የሆነዉን ቴምርና ዉሃ እየሰጡ እያንዳንዱን ልዑክ ቆመዉ ነበር የሚያስተናግዱዋቸዉ። እናም ይህ ጥብቅ ትስስራችንን ነዉ የሚያሳየዉ። ቁራን ዉስጥ አበሻን በሚመለከት ከ 23 የማያንሱ የቁራን መልክቶችን እናገኛለን። ብዙዉ ነገር እና ጥብቅ ትስስር ነዉ ያለን»

የአረፋ በዓል፤ ኢድ ኧልፈጥር ከተከበረ ከሁለት ወር ከአስር ቀን በኋላ በድምቀት እንደሚከበርና በዚህ ክብረ በዓል፤ በተለይ ክትፎ አይቀሬ መሆኑን ሰምተናል። ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ