1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ኢትዮጵያ ወደ ብሎክቼን ቴክኖሎጂ እያማተረች ነው

ረቡዕ፣ ግንቦት 8 2010

የኢትዮጵያ ብሎክቼን የተባለውን ውስብስብ ቴክኖሎጂ ለማስተዋወቅ ገፋ ሲልም ለመጠቀም ዝግጅት ላይ ትገኛለች። የኢትዮጵያ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ኢንፑት አውት ፑት ሖንግ ኮንግ ከተባለ ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።

https://p.dw.com/p/2xqPI
Symbolbild Blockchain
ምስል Colourbox

በቅድሚያ ለወጣት ምሩቃንን ሥልጠና ይሰጣል

ባለፈው ወር የኢትዮጵያ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ብሎክቼን የተባለውን ውስብስብ ቴክኖሎጂ ለማስተዋወቅ ኢንፑት አውት ፑት ሖንግ ኮንግ ከተባለ ኩባንያ ጋር የመግባቢያ ሥምምነት ፈርሟል።  ሥምምነቱን የፈረሙት የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ምኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ እና አይኦኤችኬ የተባለው ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቻርለስ ሖስኪንሰን ናቸው። የመግባቢያ ሥምምነቱ በዋናነት ሁለት ምዕራፎች አሉት። ቻርለስ ሖስኪንሰን የመግባቢያ ስምምነቱን ከመግዛት በፊት ለመሞከር የተደረገ ብለው ይገልጹታል። "ዋናው ሐሳባችን በኢትዮጵያ ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ከዩኒቨርሲቲዊዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር የኮምፒውተር ሳይንስ፣ ሒሳብ እና ፊዚክስ ወጣት ምሩቃንን በክሪፕቶከረንሲ እና ብሎክቼን ዘርፍ እንዴት መስራት እንደሚችሉ ለማሰልጠን ነው። ሥልጠናው በነፃ የሚሰጥ ሲሆን በቅርብ ጊዜ የተመረቁ ሁሉ ሊያመለክቱ ይችላሉ። በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥያቄ መሰረት የመጀመሪያዎቹ ሰልጣኞች ሴቶች ይሆናሉ"  ሲሉ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ሐሳባቸውን አስረድተዋል። 

Kaffee Bauer in Äthiopien
ምስል AP Photo

ኩባንያው በችሎታቸው የላቁ ወጣቶችን አሰልጥኖ በመቅጠር በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ቢሮውን የመክፈት ውጥን አለው። ቻርለስ ሖስኪንሰን እንደሚሉት  ይሕ ሲሳካ በተመረጡ የሥራ ዘርፎች የሙከራ ትግበራ ይጀምራሉ። ኩባንያው በግብርናው ዘርፍ በተለይም በቡና ምርት እና ግብይት ላይ አይኑን ጥሏል። ቀዳሚው ጥያቄ ግን ብሎክ ቼን ምንድነው የሚለው ይሆናል። አቶ ብሩክ ብርሐኔ ይኸን ቴክኖሎጂ የተቆለፈ የሒሳብ ዝውውር ሲሉ ይገልጹታል። አቶ ብሩክ ኤክሶካ አይቲ ሶልዩሽን በተባለ ኩባንያ ሥራ አስፈፃሚ ናቸው። 

ይኸ ቴክኖሎጂ በባንኮች እጅ የሚገኘውን እና በመንግሥታት ግምጃ ቤቶች ቁጥጥር የሚደረግበትን የገንዘብ ዝውውር ያልተማከለ ለማድረግ እቅድ አለው። የቴክኖሎጂው ባለቤቶች ወደ አፍሪቃ አይናቸውን የጣሉ ሲሆን ከገንዘብ ዝውውር እስከ የመሬት ባለቤትነት ምዝገባ ያሉ ሥራዎችን ሊከወንበት እንደሚችል ተስፋ ይሰጣሉ። የማይሳሳት፣ የማይሰረዝ እና የማይደለዝ በሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት የማይዘረፍ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት የቴክኖሎጂው ባለሙያዎች የሚሰጡት ተስፋ ነው። ቴክኖሎጂው ክሪፕቶከረንሲ የተባለ ምናባዊ መገበያያ ይጠቀማል። ላለፈው አንድ አመት ገደማ ዋጋው ሲዋዥቅ የተስተዋለው እና ዛሬም ዓለም በጥርጣሬ የሚመለከተው ቢት ኮይን አንዱ የክሪፕቶከረንሲ አይነት ነው። 

ሙሉ መሰናዶውን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ 

እሸቴ በቀለ 

ነጋሽ መሐመድ