1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአውስትራሊያ ባለስልጣናትን የተቃወሙ ቤተሰቦች ታሰሩ መባሉ

ሰኞ፣ ጥቅምት 28 2009

ሂዩማን ራይትስ ዎች ኢትዮጵያን የሚመለከቱ መግለጫዎችን በተደጋጋሚ እያወጣ ይገኛል፡፡ ከሳምንታት በፊት ለቀረበበት ውንጀላ የሚሆን ግልጽ ደብዳቤ አርብ ዕለት አውጥቷል፡፡ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ደግሞ የሶማሌ የክልል ፕሬዝዳንትን ተቃውመው በአውስትራሊያ አደባባይ የወጡ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ታስረዋል ሲል ከስሷል፡፡

https://p.dw.com/p/2SJ2a
Menschenrechte Logo human rights watch

HRW Accuses Ethiopian Gov. - MP3-Stereo

ሂዩማን ራይትስ ዎች በዛሬው መግለጫው ከአራት ወር በፊት በሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ሞሀመድ የሚመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ወደ አውስትራሊያ በመጣበት ወቅት ተቃውሟቸውን ያሰሙ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ላይ እስራት መፈጸሙን እና ድርጊቱ አሁንም አለመቆሙን አትቷል፡፡ ድርጅቱ ለተቃውሞ ከወጡ ግለሰቦች ባደረገው ቃለ ምልልስ 32 የቤተሰቦቻቸው አባላት መታሰራቸውን እንደነገሩት በቪዲዮ አስደግፎ አቅርቧል፡፡ ከታሳሪዎቹ ውስጥ የ70 እና 85 ዓመት ዕድሜ ያላቸው እንደሚገኙበት ሲድኒ በሚገኘው ጽህፈት ቤቱ አማካኝነት ዛሬ ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ደጋፊዎች ለሰልፍ በወጡበት ወቅት በቅንጡ ስልኮቻቸው ይቀርጿቸው እንደነበር የሚናገሩት ተቃዋሚዎች “ዘመዶቻችሁ ላይ ምን እንደሚደርስ ታያላችሁ?” ሲሉ ይዝቱባቸው እንደነበር የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ይገልጻል፡፡ ዛቻው እውን ሆኖም አንዳንዶቹ በሰዓታት ውስጥ ኢትዮጵያ ከሚገኙ ዘመዶቻቸው የስልክ ጥሪ እንደደረሳቸውና እና የቤተሰቦቻቸውን መታሰር እንደሰሙ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

የዘፈቀደ እስር በሶማሌ ክልል የተለመደ  እንደሆነ ሂዩማን ራይትስ ዎች ይሟገታል፡፡ በተቋሙ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ ፌሌክስ ሆርን እንደሚሉት በተለይ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር «ኦብነግ» በሚያካሄዳቸው ጥቃቶች ላይ ድጋፍ ሰጥታችኋል አሊያም ተሳትፋችኋል በሚል በርካታ ሰዎች በዘፈቀደ እንደሚታሰሩ ይገልጻሉ፡፡  

“ሂዩማን ራይትስ ዎች በተደጋጋሚ በሶማሌ ክልል ግለሰቦች በዘፈቀደ እንደሚታሰሩ መግለጫ አውጥቷል፡፡ እስሩ ብዙውን ጊዜ የሚከናወነው በኦብነግ እና በልዩ ፖሊስ መካከል ግጭት ከተፈጠረ በኋላ ነው፡፡ በጎረቤት ሀገራት ያሉ ግለሰቦች ላይ ያነጣጠሩ ማዋከቦች እንደሚከናወኑ ብዙ መረጃዎች ይደርሱናል፡፡ በሶማሌ ክልል ቤተሰቦች ያሏቸው ግለሰቦችም ኢላማ እየተደረጉ ነው፡፡ ባለፈው ሰኔ በአውስትራሊያ ያየነውም ይህንን ነው፡፡ የሶማሌ ማህብረሰብ አባላት የአብዲ [ሞሀመድ] ኤሊን መምጣት በመቃወማቸው ከዚያ ተከትሎ ባሉ ቀናት እና ሳምንታት በሶማሌ ክልል ያሉ የቤተሰብ አባላቶቻቸው ታስረውባቸዋል” ይላሉ፡፡

Infografik Karte Proteste und Ausschreitungen in Äthiopien 2016

እንደተቃዋሚዎቹ አባባል ከሆነ የታሰሩ ዘመዶቻቸው ይፈቱ ዘንድ ለሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ያላቸውን ድጋፍ በቪዲዩ መልዕክት እንዲያሳዩ ተገድደዋል፡፡ ትውልዳቸው ከሶማሌ ክልል የሆኑ እና የአውስትራሊያ ዜግነት ካላቸው ከእነዚህ ተቃዋሚዎች መካከል ሶስቱ ለቤተሰቦቻቸው ሲሉ በዚህ አይነት የቪዲዮ ቀረጻ መሳተፋቸውን መግለጫው ያስረዳል፡፡ 

በእንዲህ አይነት የ“ይቅርታ ቪዲዮ” ላይ እንዲሳተፉ ተቃዋሚዎችን ማስፈራራት የሶማሌ ክልል የተለመደ ስልት እንደሆነ ሂዩማን ራይትስ ዎች ይወነጅላል፡፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ተመሳሳይ ድርጊቶች በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሰሜን አውሮፓ በሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ላይ በመንግስት ደጋፊዎች እንደተፈጸሙ አስታውሷል፡፡ በዚህ ዓይነት የሚቀናበሩት ቪዲዮዎች በክልሉ የቴሌቪዥን ጣቢያ እና በመንግስት ደጋፊ ድረ-ገጾች ላይ እንደሚቀርቡ ተቋሙ ይጠቁማል፡፡ 

ለዘመዶቻቸው ተቃውሞ እንደመቀጣጫ ከታሰሩ ግለሰቦች መካከል የተወሰኑት እንደተፈቱ የሚገልጸው ሂዩማን ራይትስ ዎች የኢትዮጵያ መንግስት ቀሪዎቹንም በአፋጣኝ እንዲፈታ አሳስቧል፡፡ ፌሌክስ ግለሰቦቹ ወንጀለኛ ባለመሆናቸው ሊፈቱ ይገባል ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ 

“እነዚህ ግለቦች ምንም ዓይነት ወንጀል አለመፈጸማቸው ግልጽ ነው፡፡ ዘመዶቻቸው በአውስትራሊያ መንግስትን በመቃወማቸው ምክንያት እየተቀጡ ነው፡፡ የሶማሌ ክልል እና አብዲ [ሞሀመድ] ኤሊ የታሰሩትን ወዲያውኑ እንዲለቀቁ እና ወደፊትም ወከባ እንዳይደርስባቸው የኢትዮጵያ መንግስት ማረጋገጥ አለበት“ ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ስለ ጉዳዩ ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ የሂዩማን ራይትስ ዎች መግለጫ የ“ተለመደ ተራ ውንጀላ” ነው ብሏል፡፡ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ሚኒስትሩ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ሂዩማን ራይትስ ዎች ጉዳዩን አስመልክቶ ለመንግስት ምንም አለማሳወቁን እና ውንጀላውን ከዜና መመልከታቸውን ይናገራሉ፡፡ 

“ይህን መረጃ እንዳገኘን ከሶማሌ ክልል መንግስት ለማጣራት ሞክረናል፡፡ ባገኘነው መረጃ መሰረት ይሄ ተራ ውንጀላ እንደሆነ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም ሂዩማን ራይትስ ዎች እንደዚህ ዓይነት ውንጀላዎችን ያቀርብ እንደነበር እና እስካሁን እንዳጣራሁት [ይህም] ተመሳሳይ እንደሆነ ነው፡፡ በመግለጫው ላይ በግልጽ የታሰሩት ሰዎች ዝርዝር በግልጽ የታወቀበት ሁኔታ የለም” ብለዋል፡፡ 

አሁን ባላቸው መረጃ እንደዚህ ዓይነት እርምጃ አለመወሰዱን የሚናገሩት ዶ/ር ነገሪ ወደፊት አዲስ ነገር ካለ እና ተጨማሪ መረጃ ካገኙ እንደሚያሳውቁ ቃል ገብተዋል፡፡ ሂዩማን ራይትስ ዎች በበኩሉ የሚመለከታቸውን የሶማሌ ክልል ባለስልጣናት ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራዎች ማድረጉን ነገር ግን ምላሽ አለማግኘቱን ይናገራል፡፡   

 

ተስፋለም ወልደየስ

አዜብ ታደሰ