1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 ኢትዮጵያ ሕዝባዊ ተቃዉሞና የገዢዉ ፓርቲ ጉባኤዎች

ሐሙስ፣ መስከረም 19 2009

የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ ማዕከላዊ ኮሚቴ (ሕወሐት) ስብሰባ እንደ ኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) አቻዉ በባለሥልጣናቱ ላይ የወሰደዉ ተጨባጭ እርምጃ የለም። የአመራር ለዉጥ ለማድረግ መወሰኑ ግን ተዘግቧል።

https://p.dw.com/p/2Qjni
Äthiopien Asgede Gebrselassie in Mekelle
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

TPLF central comitee meeting - MP3-Stereo

የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የኢሕአዴግ ምክር ቤት በቅርቡ ባደረገዉ ጉባኤዉ በሐገሪቱ ለተቀሰቀሰዉ ሕዝባዊ ተቃዉሞና ግጭት መፍትሔ ለማፈላለግ በወሰነዉ መሠረት የግንባሩ አባል ፓርቲዎች የየራሳቸዉን ጉባኤ አድርገዋል። በማድረግም ላይ ናቸዉ። የኦሮሚያ መስተዳድር ገዢ ፓርቲ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የፓርቲዉን ዋና እና ምክትል ሊቃነመናብርትን ከሥልጣን  አስወግዶ መጠናቀቁን ዘግበናል። የአማራ መስተዳድርን የሚገዛዉ የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) እና የደቡብ መስተዳድር ገዢ ፓርቲ የደኢሕዴን ጉባኤዎች ዉጤት በዉል አልታወቀም። የትግራይ ገዢ ፓርቲ የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሐት) ማዕከላዊ ኮሚቴ ግን የሥልጣን ሽግሽግ ለማድረግ ወስኖ ስብሰባዉን ትናንት አጠናቅቋል። የሕወሐት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባና ዉሳኔዎች በተመለከተ ነጋሽ መሐመድ ያጠናቀረዉ ዘገባ አለ።
                        
የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ ማዕከላዊ ኮሚቴ (ሕወሐት) ስብሰባ እንደ ኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) አቻዉ በባለሥልጣናቱ ላይ የወሰደዉ ተጨባጭ እርምጃ የለም። የአመራር ለዉጥ ለማድረግ መወሰኑ ግን ተዘግቧል። የስብሰባዉን ሒደት የተከታተለዉ ጋዜጠኛ የማነ ናግሽ እንደሚለዉ የማዕከላዊ ኮሚቴዉን ዉሳኔ ገቢር ለማድረግ ፓርቲዉ ሌላ ስብሰባ ቀጥሏል።
                                   
የቀጠለዉ ስብሰባ ዉጤት አይታወቅም። መሪዎቹ የአመራር ሽግሽግም ይበሉት ለዉጥ፤ የሚደርሱበት ዉሳኔ፤ የማነ እንደሚለዉ፤ አንጋፋዎቹን መሪዎች አስወግዶ በወጣቶች የሚቀይር ነዉ ተብሎ ግን አይጠበቅም።
                        
የቀድሞዉ የሕወሐት መሥራችና ያሁኑ ተቃዋሚ አቶ አስገደ ገብረስላሴም የስብሰባዉን ሒደት እዚያዉ መቀሌ ግን ካዳራሽ ዉጪ ሆነዉ ተከታትለዉታል። አቶ አስገደ እንደሚያምኑት የሕወሐት መሪዎች በተናጥል-የኢሕአዴግ በጥቅል፤ ተሸጋሸጉ፤ ተቀያየሩ ለተነሳዉ ሕዝባዊ ተቃዉሞ መልስ ሊሰጡ አይችሉም። «ሽወዳ» እንጂ በሳቸዉ አገላለፅ።
                                
ሕወሐት በትግራይ ሕዝብ ዘንድ ያለዉ ተቀባይነት፤ በመንግሥት ላይ የተነሳዉ ተቃዉሞ እና የሌላዉ አካባቢ የፖለቲካ አቀንቃኝ ሥለ ትግራይ ሕዝብ ያለዉ ግንዛቤ አቶ አስገደ እንደሚሉት «ጥንቃቄ» ያሻዋል።አቶ አስገደ አክለዉ እንዳሉት የሚሰጡ አስተያየቶች፤ ትችቶችና ወቀሳዎች ጥንቃቄ ካልተደረገባቸዉ ዉጤታቸዉ መጥፎ ሊሆን ይችላል።ጋዜጠኛ የማነም በዚሕ ይስማማል።