1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል ሕክምና ለማግኘት ተቸግረዋል

ሐሙስ፣ ኅዳር 7 2010

ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ መሪዎች አንዱ እና በእስር ላይ የሚገኙት ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል ወሕኒ ቤት ታመዉ ሕክምና ለማግኘት መቸገራቸዉን ቤተሰቦቻቸዉ አስታወቁ። አህመዲን በሚገኙበት የቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲጎበኙ የተፈቀደላቸው ከአንድ ሰዓት ላልበለጠ ጊዜ ብቻ መሆኑንም ጨምረው ገልጠዋል።

https://p.dw.com/p/2nlYO
Äthiopischer "Muslim Arbitration" Komitee Mitglied
ምስል A. Ahmed

ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል 8 መፃሕፍት አሳትመዋል

አሕመዲን ጀበል፤ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አመራር ብቻ አይደሉም።የብዙ መፅሐፍት ደራሲ፤ የበርካታ መጣጥፎች ባለቤት እና ኡስታዝ ናቸዉ። ከታመሙ ቤተሰቦቻቸዉ እንዳሉት ከራርሟል። ዛሬ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሔደዉ የጎበኟቸዉ እህታቸው ወ/ሮ ነጃት ጀበል እንደሚሉት ኩላሊታቸዉ አካባቢ ያጋጠማቸዉን ሕመም የመታከም እድል ያገኙት ከዘገየ በኋላ ነው።

የኡስታዝ አሕመዲን ጀበል የሕክምና ቀጠሮ ከሁለት ወራት በኋላ ነዉ።ይሁንና ኡስታዙ መጸዳጃ ቤት ለመቀመጥ፣ ከአልጋ ለመውረድ እና ከጠያቂዎች ጋር ለ30 ደቂቃ እንኳ ቆሞ ለመነጋገር ጭምር መቸገራቸዉን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉት የቤተሰብ አባል ገልጠዋል። ቤተሰቦቹ እንደሚሉት አሕመዲን የሕክምና ፈቃድ ለማግኘት ረጅም ጊዜ የወሰደባቸዉ ሲሆን "አጃቢ የለም፣ መኪና ተበላሽቷል" በሚሉ ሰበቦች ሕክምና ማዕከል የማይሔዱበት ብዙ ጊዜ ነበር ። 

"ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች እያየን አይደለም" ያሉት አንድ ሌላ የቤተሰብ አባል አሕመዲን ከጎብኚዎቻቸው የሚገናኙበት ጊዜም የተገደበ ነው» ብለዋል። "እንደማንኛውም ታሳሪ በተፈለገው ሰዓት አይጎበኝም። ከ6  እስከ 7 ሰዓት ባለችው ጊዜ፤ እሷም ተሸራርፋ 30 ደቂቃ ብታገኝ ነው። ያንንም እህት፣ ወንድም አባት እናት ብቻ እንጂ ሕገ-መንግሥቱ እንደሚፈቅደው ጓደኛ፣ የሐይማኖት አባት" እንዲጎበኛቸው አልተፈቀደም ሲሉ ቤተሰቦቻቸው ተችተዋል። የአሕመዲን ጀበል መታመም ከተሰማ በኋላ በርካታ ኢትዮጵያውያን ተቆጥተዋል። "በጣም ተረብሻለሁ" የሚለው አቀንቃኝ አብዱራሒም አሕመድ አንዱ ነው።

 የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ እና የሕዝብ ግንኙት ኮሚቴው አባል ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል ሌሎች የኮሚቴ አባላት ሲፈቱ በእስር ከቆዩት መካከል አንዱ ሲሆኑ 22 አመት እስራት ተፈርዶባቸዋል።

ኡስታዝ አህመዲን ጀበል 8 መፃሕፍት ለአንባብያን ያቀረቡ ሲሆን በሐይማኖታዊ እና ታሪካዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ይታወቃሉ። "ፈርዖን የአምባገነኖች ተምሳሌት" እና "ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የጭቆናና የትግል ታሪክ" የተሰኙት ሁለት መፃሕፍት በእስር ላይ ሳሉ ካሳተሟቸው መካከል ይጠቀሳሉ። አሕመዲን ጀበል ባለ ትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ናቸዉ።


እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሰ