1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃ እና የ2015 ዓም ምርጫዎቿ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 9 2008

በጎርጎሪዮሳዊው 2015 ዓም በተለያዩት አፍሪቃውያት ሃገራት የተካሄዱት ምርጫዎች በአህጉሩ ያስገኙታል ተብሎ ተጠብቆ የነበረው የለውጥ ተስፋ ካንዳንድ ሃገራት በስተቀር በብዙዎቹ ዘንድ ገሀድ አልሆነም።

https://p.dw.com/p/1HQ9H
Wahlen Tansania Sansibar Wahlen März 2015
ምስል picture-alliance/dpa/K.Ludbrook

[No title]

የፖለቲካ ታዛቢዎች በጎርጎሪዮሳዊው 2015 ዓም በአፍሪቃ ያልጠበቁት ነገር በመከሰቱ በጣም ተገርመዋል። ምክንያቱም በናይጀሪያ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ በምርጫ ሽንፈት የደረሰበት ፕሬዚደንት ባለፈው መጋቢት ወር የምርጫውን ውጤት፣ ማለትም ፣ ሽንፈቱን ካላንዳች ተቃውሞ በፀጋ ተቀበሎ፣ ስልጣኑን ለተፎካካሪው አስረክቦዋል። የናይጀሪያን ምርጫ ተከትሎም፣ ከስድስት ወር በኋላ ቀጣዩ ታሪካዊ ምርጫ በቡርኪና ፋሶ ተካሂዶ፣ ቡርኪናቤዎቹ አዲስ ፕሬዚደንት መርጠዋል። በዚችው ምዕራብ አፍሪቃዊት ሃገር በምርጫው ዕለት በየምርጫ ጣቢያዎቹ ደጃፍ የተሰለፈው ብዙ መራጭ ሕዝብ፣ባለፉት ሶስት አሰርተ ዓመታት ገደማ በነበረው የቀድሞው ፕሬዚደንት ብሌዝ ካምፓዎሬ አገዛዝ ዘመን በተካሄዱት እና ውጤታቸው አስቀድሞ ይታወቁ በነበሩት ምርጫዎች አንፃር፣ በዚያን ዕለት የሚሰጠው ድምፁ፣ዋጋ እንዳለው አውቆት ነበር።

Nigeria Goodluck Jonathan Abdulsalami Abubakar Muhammadu Buhari
ምስል DW/Ubale Musa

ይሁን እንጂ፣ ጎርጎሪዮሳዊው 2015 ዓም በአፍሪቃ አስገራሚ የምርጫ ሂደት የታየበት ዓመት ሆኖ ሊመዘገብ አይችልም። ምክንያቱም፣ በተለያዩ ሃገራት ርዕሳነ ብሔሮች ሕገ መንግሥቱ ከሚፈቅድላቸው በላይ የስልጣን ዘናቸውን ለማራዘም በወሰዱት ርምጃ ውዝግብ ተነስቶዋል። በቡሩንዲ ፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ በስልጣን ለመቆየት ያቀዱበት ድርጊት ደም አፋሳሹን ሁከት ቀስቅሷል። በጎርጎሪዮሳዊው 2014 ዓም የቡርኪና ፋሶ ሕዝብ በፕሬዚደንት ብሌዝ ካምፓዎሬ አንፃር አደባባይ እንደወጣው ሁሉ፣ በቡሩንዲም ሕዝቡ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በፕሬዚደንታቸው የስልጣን ጥም አንፃር ተቃውሞ አካሂደዋል። ፒየር ንኩሩንዚዛ መጀመሪያ ሕገ መንግሥቱን ለማስቀየር ሞከሩ፣ ግን፣ ይህ አልሳካ ሲላቸው፣ ሕገ መንግሥቱን ለሳቸው እንደሚመች አድርገው ቀይረውታል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ መንግሥታቸው ተቃውሞ ሰልፎችን በኃይል በመበተን፣ ተቃዋሚዎችን በመከታተል እና በማስገደል ላይ እንደሚገኝ፣ ብዙዎቹ ተቺዎቻቸውም ሃገር ለቀው ወደ ውጭ ሃገር እንደሸሹ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ያሳያሉ። ንኩሩንዚዛ ባለፈው ሀምሌ ወር ራሳቸውን እንደገና ለሃገር መሪነቱ ስልጣን አስመርጠዋል።

ልክ እንደ ቡሩንዲ ብዙ አፍሪቃውያን መንግሥታት የፕሬዚደንቶቻቸውን ስልጣን በሁለት ዘመን ገድበዋል። ይሁን እንጂ፣ ይህ ደንብ ሁሌ አይከበርም። ይህም ካለፉት ጊዚያት ወዲህ እንደሚታየው ለውዝግብ ምክንያት መሆኑን ከዶይቸ ጋር ቀለ ምልልስ ያደረጉት በፕሪቶርያ፣ ደቡብ አፍሪቃ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም ኃላፊ ጃኪ ሲልየ አመልክተዋል።

Burkina Faso Unruhen in Ouagadougou
ካምፓዎሬን ከስልጣን ያስወገደው የቡርኪና ፋሶ ሁከትምስል Reuters/J. Penney

« ይህ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን ለመወዳደር በሚፈልጉ መሪዎች እና ይህን በሚቃወሙት እና በመራጩ ሕዝብ መካከል የሚታየው ተፃራሪ ፍላጎት በአፍሪቃ ፖለቲካ ውስጥ አዲስ አስገራሚ ክስተት ሆኖዋል።»

እርግጥ ፣ አፍሪቃውያቱ ሃገራት የተለያዩ አሰራር ቢከተሉም፣ በሁሉም የለውጥ ሂደት መነቃቃት መጀመሩን እንደተገነዘቡት ነው ጃኪ ሲልየ የገለጹት።

« እርግጥ ፣ ከሃገር ሃገር ይለያያል። ይሁንና፣ ዋናው ነገር በመራጮች ዘንድ የአስተሳሰብ ለውጥ መታየት መጀመሩ ነው። ቀደም ባሉት ጊዚያት አፍሪቃውያኑ መራጮች ተቃውሞ የማድረግ ፍላጎታቸው ያን ያህል አልነበረም። መሪዎቻቸው እስከፈለጉት ጊዜ ድረስ በስልጣን የመቆየት መብት እንዳላቸው አድርገው ነበር የሚመለከቱት። ያ አስተሳሰብ አሁን በርግጥ እየተለወጠ መጥቷል።»

ምርጫ መንግሥታት ወደፊትም በስልጣን ላይ መቆየት የሚችሉበትን ሁኔታ የሚያረጋግጡበት ሂደት ብቻ መሆኑ ቀርቷል። መራጮች ፣ምርጫን በተመለከተ የአስተሳሰብ ለውጥ በማድረግ፣ ራሳቸው ተሟጋቾች ሆነዋል። አደባባይ በመውጣትም የመንግሥት ለውጥ እንዲደረግ መጠየቅ ጀምረዋል።

በላይፕሲግ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ት ምህርት ዘርፍ መምህር ለሆኑት ኡልፍ ኤንግል በዚህ ዓመት ከተካሄዱት ምርጫዎች ሁሉ በታንዛንያ የተደረገው በትልቅ ጉጉት የተጠበቀ ምርጫ ነበር።

« ምርጫውን በቀላሉ ማሸነፍ እንደማይችል የተረዳው መንግሥት ለራሱ መንገዱን ለማመቻቸት በጊዜ ርምጃ ወስዶዋል። ምርጫታ ነፃና ትክክለኛ አልነበረም። ወቅት በከፊል ራስ ገዟ የዛንዚባር ደሴት ውስጥ የኃይል ተግባር ተካሂዶ፣ የአስመራጩ ኮሚሽን ማዕከል ተይዞ ነበር፣ የድምፅ ቆጠራው እንዲቆም ተደርጓል። ይህ ሁሉ በአፍሪቃ ምርጫ ምን ያህል ከፍተኛ ሚና እየያዘ መምጣቱን አሳይቶዋል። »

Jakaya Kikwete Tansania Präsident
የታንዛንያ ፕሬዚደንት ጃካያ ኪክዌቴምስል Reuters

የታንዛንያ ፕሬዚደንት ጃካያ ኪክዌቴ ከብዙ ዓመታት ወዲህ ስልጣኑን ሙጥኝ ብለው ከሚገኙት በዚምባብዌ ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ወይም በኡጋንዳ ርዕሰ ብሔር ዮዌሪ ሙሴቬኒ አንፃር ከሁለት የስልጣን ዘመን በኋላ ሕገ መንግሥቱ በሚለው መሰረት ስልጣናቸውን በመልቀቅ አዲስ ፕሬዚደንት የተመረጠበትን መንገድ ክፍት አድርገዋል። በታንዛንያ ገዢ ፓርቲ «ቻማ ቻ ማፒንዱዚ» እና በተቃዋሚው ቡድን እጩ መካከል ፉክክሩ ጠንካራ እንደሚሆን ታዛቢዎች ከምርጫው ቀደም ሲል ቢገምቱም፣ የመራጩ ሕዝብ ፍላጎት ገዢው ፓርቲ እንደጠበቀው ላይሆን እንደሚችል እንዳላጣው ጃኪ ሲልየ አስረድተዋል። ኡልፍ ኤንግልም ይህንን የጃኪ ሲልየን አስተያየት ይጋራሉ።

የገዢው ፓርቲ እጩ ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ አዲሱ የታንዛንያ ፕሬዚደንት ሆነው ቢመረጡም፣ መራጩ ሕዝብ የይስሙላ ምርጫዎችን እንደማቀበል ግልጽ ማድረጉን ሲልየ አስረድተዋል።

« የታንዛንያን ምርጫ ስንመለከት፣ ገዢው ፓርቲ ለመጀመሪያ ጊዜ የምርጫው ውጤት እንዳሰበው ላይሆን ይችላል በሚል ስጋት አድሮበት ነበር። ይህም የሚያሳየው በመራጩ ሕዝብ አስተሳሰብ ላይ ለውጥ መኖሩን ነው። ድምፁን የሚሰጠው ሕዝብ መሪዎቹ ከዓመት ዓመት በስልጣን ለመቆየት እያሉ የምርጫውን ውጤት እንደፈለጉ ይቀያይሩ የነበረበትን የቀድሞውን ሁኔታ በዝምታ ለመቀበል ዝግጁ አለመሆናቸውን አሳይተዋል። »

በጎርጎሪዮሳዊው 2015ዓም በ13 አፍሪቃውያት ሃገራት ውስጥ ምርጫ ተካሂደዋል። በሱዳን፣ ቶጎ፣ ጊኒ ኮናክሪ፣ ኮት ዲ ቯር ምርጫዎጥ የሃገራቱ ርዕሳነ ብሔር በስልጣን ኮርቻ እንደተቆናጠጡ መቆየቱ ተሳክቶላቸዋል።

በኢትዮጵያም ባለፈው ግንቦት ወር በተካሄደው ምክር ቤታዊ ምርጫ ገዢው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አ ብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ ኢሕአዴግ እና አጋር ፓርቲዎች ፣ አስመራጩ ኮሚሽን ባወጣው ይፋ ውጤት መሰረት፣ 100 % የመራጩን ድምፅ በማግኘት የምክር ቤቱን መንበሮች በጠቅላላ ተቆጣጥረዋል። እርግጥ፣ እያንዳንዱ ሃገር የሚከተለው የራሱ ፖለቲካዊ አካሄድ አለው፣ ይሁንና፣ ብዙው መራጭ ሕዝብ ሂደቶችን እንደበፊቱ መቀበል የሚገደድበትን አሰራር ለመከተ ዝግጁ አለመሆኑን ያሳየበት ቁርጠኝነት ሰሚ እንዲያገኝ ማድረጉን በቡርኪና ፋሶ ወይም በታንዛንያ የታዩት ዓይነቶቹ ምርጫዎች በግልጽ አሳይተዋል።

Äthiopien Parlament Hailemariam Desalegn
ምስል DW/Y. G. Egziabher

እንደ ፖለቲካ ተንታኙ ጃኪ ሲልየ ገለጻ፣ በገዢ ፓርቲዎች ላይ በወቅቱ ያረፈው ግፊት ቀላል አለመሆኑን እና ምርጫዎችም ከባድ ተግዳሮት እንደገጠማቸው መራጩ ሕዝብ በኤሌክትሮኒክስ ድምፁን በሰጠባቸው በናይጀሪያ፣ ኮት ዲቯር እና በታንዛንያ የተደረጉት ምርጫዎች አረጋግጠዋል።

« በስነ ቴክኒኩ ዘርፍ የተመዘገቡት ለውጦች ግዙፍ ሚና የተጫወቱ ይመስለኛል። ስለዚህ እንደድሮው በምርጫ ወቅት በቀላሉ የማጭበርበር ተግባር መፈፀም አይቻልም። መራጮች በኤሌክትሮኒክሱ ዘዴ ድምፅ የሚሰጡበት አሰራር ፣ እንዲሁም፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚከተላቸው የምርጫ መመሪያዎች የድምፅ አሰጣጡን ሂደት ለውጠውታል፣ ይኸው ለውጥም ገዢ ፓርቲዎች እና መሪዎቻቸው የምርጫውን ውጤት እንደፈለጉ በመቀያየር ማጭበርበር የሚችሉበትን እድል በጉልህ ቀንሶዋል። »

የፖለቲካ ተንታኞች ይህንኑ ለውጥ መንግሥታት አመራራቸውን መቀየር እንደሚኖርባቸው ያመላከተ መልካም ዜና አድርገው ተመልክተውታል። ይሁን እንጂ፣ በአህጉሩ በስልጣን አላግባብ መጠቀምን የሚያስወግድ መሳሪያ እስከዛሬ አልተፈጠረም። በዚህም የተነሳ ፣ ብዙ ምርጫ የሚደረግበት ቀጣዩ ዓመት 2016 ም፣ ልክ አስገራሚ ለውጥ ይታይበታል ተብሎ በጉጉት እንደተጠበቀው ፣ግን፣ ይኸው ትፅቢት እውን እንዳልሆነበት እንደ 2015 ዓም ውጤቱ እንደማያምር ነው ተንታኞች ያመለከቱት። የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ እና የኮንጎ ብራዛቪል ሕዝቦች አዲስ ርዕሰ ብሔር ይመርጣሉ። የኮንጎ ብራዛቪል ፕሬዚደንት ዴኒ ሳሱ ንጌሶ እንደገና የሚመረጡበትን ሁኔታ ከወዲሁ ለማረጋገጥ እና ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን መወዳደር የሚያስችላቸው ማሻሻያ የተደረገበትን ሕገ መንግሥት በሬፈረንደም ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርገዋል። የሚያሳዝነው፣ ይህንኑ የፕሬዚደንቱን እቅድ ተቃውሞ በወጣው ሕዝብ አንፃር በተወሰደ ርምጃ ሰዎች ተገድለዋል፣ ቆስለዋል። በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ የሚታየው ሁኔታም ከጎረቤት ብራዛቪል የተለየ አይደለም። ፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላ የርዕሰ ብሔሩን የስልጣን ዘመን በሁለት የሚገድበውን ሕገ መንግሥት የሚያከብሩ አይመስልም። ፕሬዚደንቱ በሕገ መንግሥቱ መሰረት፣ ጊዚያቸው ሲደርስ ከስልጣን ሊወርዱ እንደሚገባ በደብዳቤ የጠየቁዋቸውን ሰባት የጥምሩ መንግሥት ባለስልጣናትን ከስራ አሰናብተዋል።

Joseph Kabila Kabange
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

እጎአ በ2017 ዓም ስልጣናቸውን መልቀቅ ያለባቸው የጎረቤት ርዋንዳ ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜም፣ ከዚያን ጊዜ በኋላም በስልጣን መቆየት የሚያስችላቸውን ማሻሻያ አንቀጽ በሕገ መንግሥቱ ላይ እንዲሰፍር አድርገዋል። የቡሩንዲ ፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ርምጃን ሌሎች ያካባቢ መሪዎችን ሳያበረታታ እንዳልቀረ ጃኪ ሲልየ ገምተዋል። « በቡሩንዲ የተከሰቱት ሁኔታዎች ለሌሎች ያካባቢው ሃገራት አሉታዊ ምሳሌ በመሆናቸው፣ የርዋንዳ እና የኮንጎ መሪዎችም ለሶስተኛ ጊዜ በስልጣን የመቆየት ጥረታቸውን ቀጥለውበታል። »

በምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሃገር ቡርኪና ፋሶ እጎአ በ2014 ዓም ከ27 ዓመታት አገዛዝ በኋላ ፕሬዚደንት ብሌዝ ካምፓዎሬ ከስልጣን ካስወገደው ዓብዮት በኋላ በአፍሪቃ የለውጥ ሂደት እውን የሚሆንበት ጊዜ ተጀምሯል በሚል ተስፋ ያደረጉ ከቡሩንዲ ቀውስ በኋላ ሁሉ፣ ገሀዱ ሌላ መሆኑን በቅሬታ ተገንዝቦታል።በናይጀሪያ የተካሄደው ነፃ እና ትክክለኛ ምርጫም ለሌሎች ሃገራትም አርአያ ይሆናል ብሎ የጠበቁ ሁሉም፣ ይኸው ትፅቢታቸው በታንዛንያ በታየው የምርጫ ማጭበርበር እና ከምርጫ ታዛቢዎች ባጎሉዋቸው ያልተስተካከሉ አሰራሮች ብዙ ተስፋ በተጣለበት በ2015 ዓምም እንደገና መና ቀርቷል።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ