1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃ፤ ሠላሟ፤ ሠብአዊ መብትና መሪዎችዋ

ሰኞ፣ ጥር 23 2008

የአፍሪቃ መሪዎችን ትናንት እኩለ ሌት ድረስ ሲያከራክር የነበረዉ እስካሁን የዉጪ ጦር በዘመተባቸዉ ሐገራት የተሟላ ሠላም አለመስፈኑ አልነበረም። ጠላት የሚባል ሐይልን አንዴ አሸባሪ ሌላ ጊዜ ዘር አጥፊ እያሉ መግፋት፤ መዉጋት ማሳደዱ በዉይይት አማራጭ ይተካ የሚልም አልነበረም።

https://p.dw.com/p/1Hn88
ምስል Getty Images/AFP/T. Kurumba

አፍሪቃ፣ ሰላሟ፣ ሰብዓዊ መብትና መሪዎችዋ

ተጨማሪ ጦር ወደ ተጨማሪ ሐገር እና ዝምት-አናዝምት ክርክር እንጂአዲስ አበባ ተሰብስበዉ የነበሩት የአፍሪቃ መሪዎች ሠላም እና ፀጥታን ሥለማስፈን እንደገና ተነጋገሩ፤ ፤ ሕዝባቸዉን ከረሐብ፤ ድሕነት እና ኋላ ቀርነት ለማላቀቅ እንደሚጥሩ በድጋሚ ቃል ገቡ።ሠባአዊ መብት ለማክበር-ማስከበር አዉስተዋል አሉም።ብቻ አንዳቸዉ ሌላቸዉን አሞግሰዉ ተሰነባበቱ።«መጡ፤ አወሩ፤ ሔዱ ይል ይሆናል።» አዲስ አበቤዉ። የጉባኤ ዉሳኔ መነሻ፤ ሒደቱ ማጣቀሻ፤ የአፍሪቃ እዉነት መድረሻችን ነዉ።

የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ግንቦት 1963 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከተመሠረተበት ወደ ሕብረት እስከተቀየረበት እስከ ግንቦት 2001 ድረስ አያሌ ጉዳዮችን እያነሳ መነጋገር፤ መወሰን ማስፈፀሙ እርግጥ ነዉ።ተደጋጋሚ ርዕሶቹ ግን ሁለት ነበሩ።የአፍሪቃ ሐገራትን ከቅኝ ገዢዎች ነፃ ማዉጣት-አንድ፤ የደቡብ አፍሪቃን የጥቂት ነጮች አገዛዝ ማስወገድ-ሁለት።

ድርጅቱ የካፒታሊሲት-ሶሻሊስት ተቀናቃኝ ሐይላት መሻኮቺያ መድረክ ሥለነበር ሁለቱ ትላልቅ ርዕሶችን ከግብ ለማድረስ ብዙ ጊዜ ፈጅቷል።ግን የኋላ-ኋላ ተሳክተዋል።

የቀድሞዉን የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የተካዉ የአፍሪቃ ሕብረትም ያላነሳዉ ርዕስ የለም።ንዕስ-ክፍለ ዓለማዊ (አካባቢያዊ) የልማት ትስስርን ማጠናከር፤ መልካም አስተዳደርን ማጠናከር፤ ሰብአዊ መብት እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማስረፅ፤አዲስ አጋርነት ለአፍሪቃ ልማት (NEPAD) እና የዓመአቱን ግብ (MDG)ን ለዉጤት ማብቃት እንዳለ እነሆ የዘንድሮ ጉባኤዉን ትናንት አጠናቀቀ።

አዲስ አበባ ላይ የተሰመዉ የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ለሠብአዊ መብት ይዞታ ልዩ ትኩረት መስጠቱ ተነግሯል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን ለመሪዎቹ አደራ ብለዉ ነበር።

«ሠላምና ፀጥታ፤ ልማትና ዕድገት የሚመጣዉ የሌሎችን መብት ሥናስከብር ብቻ ነዉ።በቀለማቸዉ፤ በሐይማኖታቸዉ፤በጎሳቸዉ በፖለቲካ ዓመለካከታቸዉ፤ በፆታቸዉ በዕድሜና በአካላቸዉ ሳይለዩ ሁሉም እኩል መብታቸዉ ሲከበር ነዉ።»

ረጅም ጊዜ ሥልጣን በመቆየት፤ ተቃዋሚዎቻቸዉን በማጥፋት፤ የየሕዝባቸዉን መብት በመርገጥ የገነኑት አብዛኞቹ የአፍሪቃ መሪዎች ሠብአዊ መብት እንዲከበር፤ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ይወስናሉ ብሎ ማሰብ ግን በርግጥ አሳሳች ነዉ።

Afrikanische Union Gebäude Außenansicht Äthiopien Addis Ababa
ምስል Imago

የፀጥታ ጥናት የተሰኘዉ ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ሐሌሉያ ሉሌ እንደሚሉት ደግሞ በየመሪዎቹ ጉባኤ እንደ መሪ ርዕስ የሚጠቀሱት ሁሉ ጉባኤዉ የሚነጋገር እና የሚወስንባቸዉ ጉዳዮች አይደሉም።

ሠላምና ደሕንነት ወይም ፀጥታ። ከቅኝ አገዛዝ እና ከዘር መድሎ ሥርዓት መላቀቅ ለአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የዕድሜ ልክ ትኩረት እንደነበረ ሁሉ፤ ድርጅቱን የተካዉ የአፍሪቃ ሕብረት የእስካሁን ትኩረት አንድ ነዉ።ሠላምና ደሕንነት።እንደገና አቶ ሐሌሉያ ሉሌ።

የምዕራባዊ ሳሕራ፤ የላይቤሪያ፤የኮትዲቯር፤ የምዕራብ ሱዳን (ዳርፉር) ሠላም የሚጠበቀዉ በዉጪ ጦር ሐይል ነዉ።ማሊ፤ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ፤ ፤ ደቡብ ሱዳን፤ አብዬ፤ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፤ ሶማሊያ በሳላም ማስከበር ሥም የዘመተዉ የዉጪ ጦር አንድም ከየአካባቢዉ አማፂያን ጋር ይዋጋል አለያም ሴቶችን እና ላካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናትን በመድፈር ይወነጀላል።ወይም ከወደ ኪስማዩ እንደሰማነዉ ጠላት ከሚባሉ አማፂያን ጋር እየተመሳጠረ ይነግዳል፤ ያስገብራል፤ይመዘብራል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመላዉ ዓለም ካዘመተዉ ሠራዊት ሰማንያ በመቶዉ የሠፈረዉ አፍሪቃ ዉስጥ ነዉ።በአብዛኞቹ የአፍሪቃ ሐገራት የሚፈለገዉን ያክል ሠላም ግን የለም።አቶ ሐሌሉያ ሉሌ ግን ሁሉም ተልዕኮ አልከሸፈም ባይ ናቸዉ።

የአፍሪቃ መሪዎችን ትናንት እኩለ ሌት ድረስ ሲያከራክር የነበረዉ ጉዳይ ግን እስካሁን የዉጪ ጦር በዘመተባቸዉ በአብዛኞቹ የአፍሪቃ ሐገራት የተሟላ ሠላም አለመስፈኑ አልነበረም።የዘመተዉ ጦር ቅይጥ ዉጤትም አይደለም።ጦር ማዝመት፤ ጠላት የሚባል ሐይልን አንዴ አሸባሪ ሌላ ጊዜ ዘር አጥፊ እያሉ መግፋት፤ መዉጋት ማሳደዱ በዉይይት አማራጭ ይተካ የሚልም አልነበረም።ተጨማሪ ጦር ወደ ተጨማሪ ሐገር እናዝምት-አናዝምት ክርክር እንጂ።ወደ ቡሩንዲ።

የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ጌታቸዉ ተድላ ሐይለ ጊዮርጊስ እንደታዘበዉ።የአፍሪቃ የሠላምና የፀጥታ ምክር ቤት አምስት ሺሕ ሠላም አስከባሪ ጦር እንዲዘምት ወስኖ ነበር።መሪዎቹ ይሕን ዉሳኔ አላፀደቁትም።ምክንያቱ ብዙ ነዉ።አንዱ ቡሩንዲ ያቀረበችዉ አቤቱታ ነዉ።እንደገና ጌታቸዉ።

የአፍሪቃ ሕብረት የሠላምና የፀጥታ ኮሚሽን ከአንድ ሐገር መንግሥት ፍቃድ እና ይሁንታ ዉጪ ጦር ለማዝመት ሲወስን ያሁኑ የመጀመሪያዉ ነዉ።የቡሩንዲ መንግሥት ጦሩ የሚዘምትበት ከሆነ እንደ ወረራ ቆጥሮት እንደሚዋጋዉ ሲያስጠነቅቅ ነበር።

Äthiopien Gipfel Afrikanische Union - Ban ki-Moon
ምስል Getty Images/AFP/T. Karumba

በዚሕም ምክንያት የፖለቲካ ተንታኝ ሐሌሉያ ሉሌ እንደሚሉት የአፍሪቃ ሕብረት የሠላምና የፀጥታ ኮሚሽን መጀመሪያዉኑ ጦር ለማዝመት መወሰኑ ተገቢ አልነበረም። ጦር ለማዝመት ከመጣደፍ ይልቅ የድርድርና የፖለቲካ መፍትሔ መቅደም አለበት የሚሉ የሕብረቱ አባላት ነበሩ።

የመሪዎቹ ጉባኤ የቡሩንዲን ተቀናቃኝ ሐይላት ከዚሕ ቀደም ለማደራደር የሞከሩት የዩጋንዳዉ ፕሬዝደንት ማደራደራቸዉን እንዲቀጥሉ ተስማምቷል።የቡሩንዲዉ ፕሬዝደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ጦር እንዲዘምትባቸዉ የተወሰነዉ ሕገ-መንግሥት ጥሰዉ ለሰወስተኛ ዘመን-ሥልጣን በመያዛቸዉ ነዉ።ጦር እንዲዘምት ከፍተኛ ግፊት ከሚያደርጉት መሪዎች አንዱ ደግሞ ንኩሩንዚዛ በሐገሬ ጉዳይ ጣልቃ ይገባሉ የሚሏቸዉ የሩዋንዳዉ መሪ ፖዉል ካጋሚ ናቸዉ።

የቀድሞዉ የአማፂ ቡድን መሪ ፖዉል ካጋሚ ከ1995 እስከ 2000 እንደ ምክትል ፕሬዝደንት፤ ከ2000 እስካሁን እንደ ፕሬዝደንት ያቺኝ ትንሽ ሐገር እየገዟት ነዉ።እንደ ንኩሩንዚዛ ሁሉ ዘመነ-ሥልጣናቸዉን ለማራዘም የሩዋንዳ ሕገ-መንግሥት እንዲቀየር አስወስነዋል።ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክን ለሚያተራምሰዉ ግጭት ከካጋሚ እኩል ተጠያቂ የሚሆን መሪ ካለ የዩጋንዳዉ አቻቸዉ ናቸዉ።ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ።

ሙሴ ቬኒ ራሳቸዉ ዩጋንዳን ለሠላሳ ዓመት ገዝተዉ ለተጨማሪ ዘመን -ለመግዛት «ምርጫ» ላሉት ትርዒት እየተዘጋጁ ነዉ።ሙሴቬኒ የሚመሩት ሽምግልና በቡሩንዲ ሠላም እና ፍትሕን ለማስፈን ምን ያሕል ይታመናል ነዉ ጥያቄዉ።

የፕሬዝደንት ንኩሩንዚዛ መንግሥትም ቢሆን ጦር ሊያዘምትበት ሲዝትበት የነበረዉ ማሕበር አሁን አደራዳሪ ሲልክለት በፀጋ መቀበሉም አጠራጣሪ ነዉ።ይሁንና ሐሌሉያ ሉሌ እንደሚሉት የንኩሪንዚዛ መንግሥት እስካሁን ሰበብ አስባብ እየፈጠረ ያጎለዉን ድርድር እንዲቀጥል የአፍሪቃ ሕብረት ላደረገዉ እና ለሚያደርገዉ ግፊት መንበርከኩ አይቀርም።

Äthiopien Gipfel Afrikanische Union - Raymond Chibanda
ምስል Getty Images/AFP/T. Karumba

ጉባኤዉ በቅርቡ ዘመነ-ሥልጣናቸዉ የሚያበቃዉን የሕብረቱን ኮሚሽን ፕሬዝደንት ድላሚኒ ዙማን ሥለሚተካዉ ዲፕሎማት ወይም ፖለቲከኛ በግልፅ ያለዉ ነገር የለም።ደቡብ አፍሪቃዊቱ ፖለቲከኛ ሐገራቸዉ በሚደረገዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ለመፎካከር ሥለሚፈልጉ የሕብረቱን ኮሚሽን ለሁለተኛ ዘመነ ሥልጣን መምራት አይፈልጉም።

የኮሚሽኑን የወደፊት መሪ ለማወቅ እስከ መጪዉ ሰኔ መጠበቅ አለብን።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሠ