1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት

ሐሙስ፣ የካቲት 16 2009

አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሞሀመድ አብዱላሂ ሞሀመድ ሶማሊያን ለማረጋጋት የተለያዩ እርምጃዎችን ለመውሰድ ቃል ገቡ። ፕሬዝዳንቱ ትናንት በበዓለ ሲመታቸው ስነስርዓት ላይ ባሰሙት ንግግር የሶማሊያን መንግሥት ለሚወጋው ለአክራሪው ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብ አባላት የሰላም ጥሪም አስተላልፈዋል።

https://p.dw.com/p/2Y9RF
Somalia Mohamed Abdullahi Farmajo
ምስል Getty Images/AFP/M. Haji Abdinur

Somalia's President appeal - MP3-Stereo

ፕሬዝዳንቱ የሰላም ጥሪ ቢያስተላልፉም ዶቼቬለ ያነጋገረው ሶማሊያዊ ጋዜጠኛ እንዳለው ሀገሪቱ በአሸባሪነት ላይ የያዘችው አቋም ግን አልተቀየረም። ኂሩት መለሰ ዘገባ አላት ።
የዘጠነኛው የሶማሊያ ፕሬዝዳንት የሞሀመድ አብዱላሂ ሞሀመድ በዓለ ሲመት መቅዲሾ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ትናንት የተካሄደው በከፍተኛ የፀጥታ ጥበቃ ነበር። የጎረቤት ሃገራት መሪዎች በተገኙበት በዚሁ ስነ ስርዓት ላይ ፕሬዝዳንቱ ባሰሙት ንግግር በሥልጣን ዘመናቸው የሀገሪቱን ጸጥታ ለማስከበር ፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ሙስናን ለመዋጋት እና እርቀ ሰላም ለማውረድ እንደሚጥሩ ቃል ገብተዋል። ትኩረታቸው ሀገሪቱን ማረጋጋት እንደሚሆን ያሳወቁት ፕሬዝዳንቱ  ለሽምቅ ተዋጊው ቡድን አሸባብም መልዕክት አስተላልፈዋል። እጅ ስጥ የሚል። ፕሬዝዳንቱ  በተለይ  ተታለው አሸባብን የተቀላቀሉ ወጣቶች ወደ መንግሥታቸው የሚመለሱ ከሆነ እጃችንን ዘርግተን እንቀበላችኋለን ብለዋል። አሸባብ በቅርቡ በሰጠው መግለጫ  አዲሱን ፕሬዝዳንት በ4ት ዓመቱ የስልጣን ዘመናቸው እንወጋዋቸልን ሲል ጦርነት አውጆባቸዋል። መቀመጫውን ለንደን ያደረገው ሶማሊያዊ ጋዜጠኛ ሊበን አህመድ ፕሬዝዳንቱ ለአሸባብ አባላት የሰላም ጥሪ ቢያስተላልፉም መንግሥታቸው ግን በሽብር እና አሸባሪዎች ላይ የያዘው አቋም ተለውጧል ማለት አይደለም ይላል። 
«ባለፈው ጊዜ አሸባብ ለሰላም የሚቆም ከሆነ ምህረት እንደሚያደርጉ አስታውቀው ነበር። በመርህ ደረጃ ግን ትናንት የተሰየሙት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከአሸባሪነት ጋር ፈጽሞ አንደራደርም ነው ያሉት። ከቡድኑ ጋር ወደፊት አብረው ሊሰሩ የሚችሉት አሸባብ ትጥቁን ፈቶ አዲሱን የሶማሊያ ፖለቲካ ሲቀላቀል ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል።»
ጋዜጠኛ ሊበን ፕሬዝዳንቱ ለወጣቶች ያቀረቡት ጥሪ ግልጽ ነው ይላል። መልዕክቱ ሰዎችን ቦምብ እያፈነዳ የሚገድል አሸባሪ ድርጅት አገልጋይ ከመሆን የተሻሉ እድሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚጠይቅ ነው። አሸባብ አሁን ተዳክሟል ቢባልም የደፈጣ ጥቃቱ ግን አልቆመም። ከቅርብ ጊዜዎቹ የአሸባብ ጥቃቶች ውስጥ ባለፈው እሁድ 38 ሰዎች የተገደሉበት የመቅዲሾው ቦምብ ፍንዳታ አንዱ ነው። አዲሱ ፕሬዝዳንት በተመረጡበት እለት ፕሬዝዳንታዊ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ ቡድኑ በጣለው ጥቃትም ሁለት ተገድለዋል። አሸባብ የደፈጣ ጥቃቱን በቀጠለበት በአሁኑ ጊዜ የፕሬዝዳንት መሀመድ አብዱላሂ ጥሪ ሰሚ ያገኝ ይሆን ? እንዴትስ ሊሳካ ይችላል። ጋዜጠኛ ሊበን 
«ይህ በሶማሊያ የፀጥታ ኃይሎች ብቃት የሚወሰን ነው የሚሆነው። እነዚህ ወታደሮች ሁሌም ገንዘብ አያገኙም። ሶማሊያ ከዘመተው የአፍሪቃ ኅብረት ጦር ጋር ሲነጻጸር የሶማሊያ የፀጥታ ኃይሎች በቂ ገንዘብ አይከፈላቸውም። የሶማሊያ የፀጥታ ኃይሎች አቅም እንዲያድግ ከተደረገ ግን አሸባብ የሚያስከትላቸውን ስጋቶች ሊከላከሉ እንደሚችሉ ማሳየት ይቻላል። ምክንያቱም ይህ ከሆነ ከጊዜ በኋላ በደቡባዊ ሶማሊያ የአሸባብን እንቅስቃሴ አስቸጋሪ ያደርገዋልና። ይህ ፕሬዝዳንቱ ዓላማቸውን ሊያሳኩ የሚችሉበት አንዱ ዘዴ ነው። ሌላው ደግሞ ከአሸባብ ጋር መነጋገር ነው።» 
የሶማሊያን እና የዜጎቿን ክብር ለማስመለስ እንደሚጥሩ ያሳወቁት አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት በስልጣን ዘመናቸው በሶማሊያውያን መካከል እርቀ ሰላም ማውረድ አንዱ ትኩረታቸው መሆኑንም ተናግረዋል። ጋዜጠኛ ሊበን እንደሚለው እርቀ ሰላም ሶማሊያን እንደገና ለማረጋጋት ከሚረዱት መንገዶች አንዱ ነው። ይህ ከዚህ ቀደምም መሞከሩን አስታውሶ የአሁኑ ፕሬዝዳንት ያሰቡት ግን ከቀደመው ይለያል ይላል። 
« ባለፉት ዓመታት የእርቀ ሰላም ጥረቶች የተደረጉት ከሶማሊያ ውጭ ነው። ይህ የመጀመሪያው አጠቃላይ እርቀ ሰላም ደግሞ በሶማልያውያን ለሶማልያውያን በሶማሊያ ውስጥ ነው የሚካሄደው። የእርቀ ሰላሙ ጥረት ሶማሊያ ውስጥ እንዲካሄድ ነው የሚፈልጉት።»
እንደ ጋዜጠኛ ሊበን አህመድ ፕሬዝዳንቱ ተሰሚነት ያላቸው ሶማልያውያንን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን የሲቪክ ማኅበራትን እና የሃይማኖት መሪዎችን እንዲሁም ምሁራንን በእርቀ ሰላሙ ጥረት ለማሳተፍ አቅደዋል።

Somalia Al-Shabaab Kämpfer
ምስል picture alliance/AP Photo/F. A. Warsameh
Somalia Präsidentschaftswahl
ምስል Reuters/F. Omar

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ