1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«አንድ ቀን ለወገኔ»

ረቡዕ፣ ሰኔ 29 2008

ኢትዮጵያን በመታው ድርቅ ምክንያት ለምግብ እጥረት የተጋለጡ ከ10 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎችን ለመርዳት ዜጎች በያሉበት የአቅማቸውን እያደረጉ ነው ።ለዚሁ ዓላማ በሃገር ውስጥ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚያበረክቱት አስተዋጽኦም ቀላል የሚባል አይደለም ።

https://p.dw.com/p/1JJio
Deutschland, Ein Tag für Äthiopien in Köln
ምስል DW/H. Melesse

«አንድ ቀን ለወገኔ»

ባለፈው ቅዳሜ እዚህ ጀርመን ኮሎኝ ውስጥ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለዚሁ ዓላማ የእርዳታ ማሰባሰቢያ ዝግጅት አካሂደው ነበር ። በድርቅ ለተጎዱ ኢትዮጵያውያን ወገኖች መርጃ በምዕራብ ጀርመንዋ በኮሎኝ ከተማ ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ ለተገኙ ታዳሚዎች ከመድረክ የተላለፈው ጥሪ ነበር ።«አንድ ቀን ለወገኔ »ሲሉ የሃሳቡ ጠንሳሾች ባስተላለፉት ጥሪ መሠረት የወገን ችግር እረፍት የነሳቸው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወደጅ የሆኑ ጀርመናውያን ተገኝተው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል ። ዝግጅቱ በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የኮሎኝ ርዕሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አሳሳቢነት በኮሎኝና በሌሎችም የጀርመን ከተሞች በሚገኙ በኢትዮጵያውያን የንግድ እና የማህበራዊ አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች ፣ማህበራት ፣በኪነጥበብ ባለሞያዎች እና በሌሎችም በጎ ፈቃደኞች ትብብር እና ተሳትፎ ነበር የተሰናዳው። ሊቀ ካህናት ዶክተር መርአዊ ተበጀ በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እና የኮሎኝ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሃላፊ እንዳስረዱት ቤተ ክርስቲያኗ ከአሁኑ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት አስቀድሞ የድርቁ ዜና ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ ባስተላለፈችው ጥሪ መሠረት እርዳታ ስታሰባስብ ቆይታለች ። በልገሳው የተሳተፉትም ኢትዮጵያውያን ብቻ አይደሉም ።
በዚሁ ዝግጅት ላይ ከዚህ ቀደም ለድርቁ እርዳታ ለቀረበው ጥሪ እጁን የዘረጋው የኮሎኝ ከተማ የአብያተ ክርስቲያናት ህብረት በጀርመንኛው ምህፃር ACK ሊቀመንበር ራይነር ፊሸርም በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር አድርገዋል ። ኢትዮጵያን በቅርብ የሚያውቁት ፊሸር እንዳሉት ማህበራችው ለጥሪው ተባበረው ሰብዓዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ነው ።
«በጥር ወር ከሁሉም አብያተ ክርስቲያናት እርዳታ ሰብስበናል ያሳባሰብነውን ይህን ጥቂት ገንዘብም አስተላልፈናል ። የኢትዮጵያ ታሪክ ይመስጠኛል ። ከዚህ ቀደም ከኛ ማህበር አንድ አነስተኛ የልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ሄዶ ነበር ። ያኔ በሃገሪቱ ያለው ድህነት ስሜቴን ቢነካም የህዝቡ ርስ በርስ የመረዳዳት መንፈስ ደግሞ አስገርሞኛል ።እኛ ባሰባሰብነው ገንዘብ አደጋውን በሙሉ ልናቃልል አንችልም ግን ምንም ባናደርግ ደግሞ ይበልጥ አደገኛ ነው የሚሆነው የእና ሃላፊነት የምንችለውን ያህል መርዳት ነው »
በዝግጅቱ አስተባባሪዎች እና በክብር እንግዶች ንግግር በተጀመረው በኮሎኙ የርዳታ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ የኮሎኝ ቅዱስ ሚካኤል መዘምራንን ያቀረቡት መዝሙር ነበር ።ከዚህ ሌላ የሰርከስ እና የፋሽን ትርኢቶች ግጥሞች እና ልዩ ልዩ አዝናኝ ዝግጅቶችም ቀርበዋል። ለገቢ ማሰባሰቢያ የምግብ የመጠጥ እና የቡና ሽያጭም ተካሂዷል ።ጨረታም ነበረ ።በመርሃ ግብሩ በቀረቡት ዝግጅቶችም ላይ ከተሳተፉት መካከል ያነጋገርኳቸው እንዳሉኝ ጥሪው ሲደርሳቸው በዝግጅቱ ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኝነታቸውን የገለጹት ካለ አንዳች ማንገራገር ነበር ። ከመካከላቸው የፋሽን ትርዒት ላይ የተካፈለው አቤል ታደሰ አንዱ ነው ።እነ አቤል ታደሰ የተካፈሉበትን የፋሽን ትርዒት ያስተባበረው ወይዘሮ ትዕግስት ላቀው በሊቀ መንበርነት የሚመሩት ማህበር ተመሳሳይ የእርዳታ መርሃ ግብር ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ነበር ። በዝግጅቱ ገጣሚ ሃና ወንድምስሻ ችግሩን አጉልቶ
የሚያሳይ ግጥም አቅርባለች ። እርስዋም ጥሪው ሲደርሳት ሳታመንታ ነበር ፈቃደንነትዋን የገለጸችው ።በዝግጅቱ ላይ ከታደሙት አንዷ ጀርመናዊቷ የኮሎኝ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ናት ።
«ሊዮኒ ቴተር እባላለሁ የኮሎኝ ዩኒቨርስቲ የቋንቋ ተማሪ ነኝ ።ስለ ዝግጅቱ የተበተነ ወረቀት አግኝቼ ነው የመጣሁት ኢትዮጵያን ስለማውቅ ነው የመጣሁት በ2014 ኢትዮጵያ ነበርኩ ። ከዝግጅቱ እንደረተዳሁት በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ብዙ ገንዘብ መዋጣት አለበት »የአንድ ቀን ለወገኔ ዝግጅት አስተባባሪ ኮሎኝ የሚገኘው የፋሲካ ሬስቶራንት ባለቤት አቶ ዳዊት ካሳሁን ለወገን ችግር መድረስ የሁሉም ሰብዓዊ ሃላፊነት ነው ይላሉ ።በርሳቸው ሆነ በሌሎች ታዳሚዎችች አስተያየት ይህን መሰሉ ዝግጅት በዚህ ብቻ የሚያበቃ መሆን የለበትም ።ከዚህ ቀደም ከምዕመናንና ከጀርመን በጎ አድራጊዎች በተሰባሰበው እንዲሁም በቅዳሜው ዝግጅት በተገኘው ገንዘብ ቋሚ እርዳታ ለማበርከት ነው የታቀደው።

Deutschland, Ein Tag für Äthiopien in Köln
ምስል DW/H. Melesse
Deutschland, Ein Tag für Äthiopien in Köln
ምስል DW/H. Melesse

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ