1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የአክሲዮን ድርሻዎቹን ለመግዛት የቻይና ኩባንያ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየተደራደረ ነው

ረቡዕ፣ ጥር 10 2009

ከተመሰረተ ከ50 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው እና ለአገሪቱ የሎጂስቲክስ አገልግሎት በብቸኝነት የሚያቀርበው ተቋም ላይ የተወሰነው ውሳኔ በበርካቶች ዘንድ አነጋጋሪ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/2W0mp
Dschibuti Hafen
ምስል DW/J. Jeffrey

አነጋጋሪው የኢትዮጵያ መንግሥት የአክስየን ሽያጭ ውሳኔ

የኢትዮጵያ መንግግሥት የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አክሲዮንን ለውጭ ኩባንያ ሊሸጥ ተዘጋጅቷል። ጠቅላይ ምኒሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የኩባንያውን የተወሰኑ አክሲዮኖች ለአንድ ኩባንያ ለማዘዋወር ጥረት እያደረግን ነው ሲሉ ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒሥትሩ መንግሥታቸው እርምጃውን የሚወስደው በገንዘብ እጥረት ሳይሆን ኩባንያውን በቴክኖሎጂ እና ብቁ አስተዳደር ለማዘመን እንደሆነ ገልጠዋል። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ለየትኛው ኩባንያ ምን ያክል ድርሻ እንደሚሸጥ የገለጹት ነገር የለም። የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በጉዳዩ ላይ መረጃ እንደሌለው ተናግሯል። ጉዳዩ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተለያየ ምላሽ አግኝቷል።

ጉዳዩን በይፋ በመተቸት ቀዳሚ የሆኑት የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ክቡር ገና በፌስቡክ ገፃቸው የማይታመን ብለውታል። አቶ ክቡር ገና የኢትዮጵያ መንግሥት በሦስት ትውልድ ቅብብሎሽ የተገነባውን እና ከፍተኛ ዋጋ ያለውን ንብረት ለመሸጥ እንደወሰነ እንዴት አንድ ሰው ማስረዳት ይችላል? ሲሉ ያጠይቃሉ። ለሕዝብ በይፋ ሳይገለጥ ክርክር እና ውይይት ሳይደረግበት ውሳኔው ገቢራዊ ሊደረግ መሆኑም አቶ ክቡር ገናን አሳስቧቸዋል። እንደ አቶ ክቡር ገና የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ኤኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን የጸጥታ ጠቀሜታ ጭምር ካላቸው መዋዕለ ንዋዮች መካከል አንዱ ነው። ለአቶ ጌታቸው ውሳኔው የዘገየ ቢሆንም መልካም ነው። አቶ ጌታቸው ውሳኔው ውስብስብ ችግሮች ላሉበት የሎጂስቲክስ ዘርፍ መንግሥት ሊወስደው የተዘጋጀው እርምጃ ሁነኛ መፍትሔ ነው ብለው ያምናሉ።

 

Dschibuti Hafen
ምስል DW/J. Jeffrey

በቻይና፤ ሖንግ ኮንግ፤ ታይዋን እና ዓለም አቀፍ ደረጃ በወደብ ማስተዳደር ሥራ ላይ የተሰማራው ቻይና ሜርቻንትስ ፖርት ሆልዲንግስ የተሰኘው ኩባንያ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየተደራደረ መሆኑን አዲስ ፎርቹን ከዚህ ቀደም ዘግቧል። ጋዜጣው ለድርድሩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ነገሩኝ ብሎ እንደፃፈው ድርድሩ ከተሳካ የቻይናው ኩባንያ ከኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት 40 በመቶ ድርሻ ባለቤት ይሆናል። ቻይና ሜርቻንትስ ግሩፕ የተሰኘው ግዙፍ ኩባንያ ቅርንጫፍ የሆነው እና በሖንግ ኮንግ የተመዘገበው ኩባንያ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅትን ዋጋ የመተመን ሥራ እያፋጠነ መሆኑ ከተሰማ ከአንድ ወር በላይ አለፈ።

 የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ አክሲዮን ማሕበር፤ የባሕርና ትራንዚት አገልግሎት እና የደረቅ ወደብ አልግሎት ድርጅቶች ተዋሕደው የተቋቋመ ነው። ድርጅቱ የገበያም ሆነ የኪሳራ ችግር ያለበት አይመስልም። ባለፈው የበጀት ዓመት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አዲስ ፎርቹን የተሰኘው የቢዝነስ እና ኤኮኖሚ ጋዜጣ ዘግቦ ነበር። ወደ 260 መዳረሻዎች አስራ አንድ መርከቦች እና 400 ተሽከርካሪዎች የሚያስተዳድረው ተቋም የተቋቋመው በጎርጎሮሳዊው 1964 ዓ.ም. በኢትዮጵያ መንግሥት እና ታሩንስ ኢንቨስትመንት በተሰኘ የዩናይትድ ስቴትስ ኩባንያ ጥምረት ነበር። ከሦስት አመታት በኋላ ንጉሣዊው መንግሥት የታሩንስ ኢንቨስትመንት ኩባንያን 51 በመቶ ድርሻ በመግዛት ጠቅልሎታል። 

በዓለም ባንክ የሎጂስቲክስ አፈፃጸም አመልካች (Logistics Performance Index (LPI)  ኢትዮጵያ በ126ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ባንኩ በቅርቡ ይፋ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ዘርፉ በውስብስብ የጉሙሩክ እና የየብስ ማጓጓዣ ችግሮች የተበተበ መሆኑን ገልጧል። ለአቶ ጌታቸው በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የሚደረግ ለውጥ ለኤኮኖሚውም የሚያበረክተው አስተዋፅዖ ከፍተኛ ነው። 
በኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ዘርፍ ላይ የተሰሩ ጥናታዊ ፅሁፎች የኢትዮጵያ መንግሥት የግሉ ዘርፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን ማሻሻያ እንዲያደርግ ሲወተውቱ ቆይተዋል። የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የአክሲዮን ባለቤት መሆናቸው ሥጋት የጫረባቸውም ግን አልጠፉም። ዋንኛ ዓላማው ማትረፍ የሆነ የውጭ ኩባንያ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ እቃዎች ላይ የማጓጓዣ ዋጋ ጭማሪ እንዲኖር ያስገድዳል የሚል ሥጋት። አቶ ጌታቸው ግን አሁን የማጓጓዝ ሥራውን በብቸኝነት የተቆጣጠረው የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ባሉበት ውስብስብ ችግሮች አሁን ለሸቀጦች ማጓጓዣ የሚከፈለው ዋጋ ራሱ ውድ ነው ሲሉ ይናገራሉ። የኤኮኖሚ ባለሙያው በድርጅቱ ላይ የሚደረጉ ማሻሻያዎች ምን አልባት የዋጋ ቅናሽ ሊያስከትሉ ይችላል የሚል ተስፋ አላቸው።

Dschibuti Containerhafen und Rotes Meer
ምስል Getty Images/AFP/S. Maina

ከኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የአክሲዮን ባለድርሻ የሚሆኑት የውጭ ኩባንያዎች ማንነት እሳካሁን በግልጽ አልታወቀም። ጠቅላይ ሚኒሥትሩም ጉዳዩን በምስጢር መያዙን መርጠዋል። ጌታቸው ከውጭ ኩባንያዎቹ ጋር የሚደረገው ድርድር በሦስት መሰረታዊ ጉዳዮች ያሳስቧቸዋል። ድርድሩ ከመጋረጃ ጀርባ መካሔዱ፤ የተዳራዳሪዎቹ አቅም እና የአክሲዮን ድርሻዎቹ የሚሸጡበት ዋጋ።


እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ