ትራምፕ በአፍሪካውያኑ ካርቱኒስቶች ዕይታ
አወዛጋቢ ጉዳዮችን የሚፈልጉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራንፕ፤ በተደጋጋሚ የሰዎች እና ሃገራትንክብር የሚነኩ አገላለጾችን ይጠቀማሉ። ይህን የሚከታተሉ አፍሪቃዉያን ካርቱኒስቶች በፖለቲካዊ ስላቅ በተለያየ መልኩ ነጥቦቹን ያነሳሉ።
ባለጭቃ ጅራፉ ትራምፕ
በሥነ-ጥበባዊ ብዕሩ የዩኤስ አሜሪካዉ ፕሬዚዳንት ከጭንቅላታቸዉ በአፍሪቃ እና ሄይቲ ላይ ቆሻሻን ሲገለብጡ የሚያሳየዉ አፍሪቃዊዉ ካርቱኒስት ሰኢድ ሚሼል «ትራምፕ ከቀለማችን ጋር ችግር አለባቸዉን?» ሲል ያጠይቃል።
ወደ ክበቡ መግባት
አፍሪቃዊዉ ካርቱኒስት ጋዶ፤ ዶናልድ ትራምፕ የገቡበት ክለብ ምንነትን ሳይገልጽ፤ ክለቡ ምን እንደያዘ ያሳያል። በክለቡ ዶናልድ ትራምፕ ከሁለት ፈላጭ ቆራጭ አፍሪቃዉያን መሪዎች ማለትም ከዩዌሪ ሙሴቪኒ እና በገዛ ፈቃዳቸዉ ሥልጣናቸዉን ከለቀቁት ከሮበርት ሙጋቤ ንግስናን መቀበላቸዉን ቁልጭ አድርጓል።
የናምቢያስ ግኝት
ባለፈዉ መስከረም ወር ትራምፕ ከአፍሪቃዉያን መሪዎች ጋር ባካሄዱት ስብሰባ ወቅት የ«ናምቢስ» ን የጤና ጥበቃ ሁኔታ አወድሰዋል። በጣም አሳፋሪዉ ጉዳይ ግን በዓለማችን በዚህ ስያሜ የሚጠራ ሐገር አለመኖሩ ነዉ። ለዚህ ስህተታቸዉ ካርቱኒስት ዛፒሮ አንድ መፍትሄን አስቀምጦአል።
ዶናልድ ትራምፕ እና የኪም ጁንግ ኡን ፍጥጫ
ከወራቶች ጊዜ አንስቶ ዶናልድ ትራምፕ እና የሰሜን ኮርያዉ መሪ ኪም ጁንግ ኡን አንዱ አንዱን በአቶም ጦር መሳርያ እያስፈራሩ ይገኛሉ። ካርቱኒስት አብዱልካሪም ባባ አሚኑ በስዕሉ እንዳስቀመጠዉ ሁለቱም የሐገር መሪዎች ተመሳሳይ ናቸዉ።
…ቆሻሾቹ ሐገሮች
ባለፈዉ ጥር ወር ዶናልድ ትራምፕ አፍሪቃዉያን ሐገራትን ጨምሮ አንዳንድ ሐገሮችን ቆሻሻ ሲሉ ጠያፍ ቃል ተናግረዋል። ካርቶኒስት ዛፒሮ ትራምፕን በሥነ-ጥበባዊ ብዕሩ መልስ አጎናፅፎአቸዋል።
ዩኤስ አሜሪካን ጥሎ ሽሽት
ሐገር ጥሎ ሽሽትን በብዕሩ ያስቀመጠዉ አፍሪቃዊዉ አብዱልካሪም ባባ አሚኑ ከሥነ-ጥበባዊ ሥራዉ ጎን ባስቀመጠዉ ጽሑፍ ዶናልድ ትራምፕ ስለጥቁሮች ያላቸዉን አስተሳሰብ አሳይቷል «ሐገራቸዉን ጥለንላቸዉ እንሄዳለን። ከዛ የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ» ይላል።
ኦፕራን የሚቃረኑት ትራምፕ
በዩኤስ አሜሪካ በምታዘጋጀዉ የቴሌቭዝን ዉይይቷ ታዋቂነትን ያተረፈችዉ የንግድ ድርጅት ባለቤት ታዋቂዋ ጥቁር አሜሪካዊት ኦፕራ ዊንፍሬ በአሚሪካኑ የፊልም ሥራ ሽልማት «ጎልደን ግሎብስ» መድረክ ቀርባ አስደማሚ ንግግር ካደረገች በኋላ ኦፕራ ምናልባት ለፕሬዚዳንታዊ እጩነት ትቀርብ ይሆናል ሲሉ በርካታ ታዛቢዎች ግምታቸዉን አስቀምጠዋል። ካርቱኒስት ጋዶ በስዕሉ ትራምፕ በትዊተራቸዉ ኦፕራን ምን ሲሉ ሊሰይሟት እንደሚችሉ ያጠይቃል። «አጭበርባሪዋ ኦፕራ፤ ቅርፀ ቢስዋ ወፍራም ኦፕራ አልያም ክፍት አፍዋ ወይም እንደ ዉሻ የምትጮኸዋ ኦፕራ?»