1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሁለት ዘመን ፈርጦች፦ አሊ ቢራ ፤ ሃጫሉ ሁንዴሳ

Merga Yonas Bula
እሑድ፣ ጥር 13 2010

በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ በኪነ-ጥበብ ሥራዎቻቸዉ ለህዝባቸው አስተዋፅዖ ላደረጉና እያደረጉ ያሉ ሰዎችን   የሚያበረታታና በሥራዎቻቸዉ እዉቅና የሚሰጥ «ኦዳ አዋርድ» የተሰኘዉ የሽልማት ዝግጅት ጥር 5 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሚገኘው የኦሮሚያ የባህል ማዕከል አዳራሽ ዉስጥ በደመቀ ሁኔታ ተካሂዷል።

https://p.dw.com/p/2rDjH
Äthiopien Addis Ababa Odaa Award Zeremonie
ምስል Odaa Award

«ተፅዕኖ ፈጣሪ»ና «የሕይወት ዘመን» ተሸላሚ ድምፃዊያን 

በዓይነቱ የመጀመሪያ ነው በተባለዉ በዚህ ዝግጅት ላይ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ምሁራኖችና ወጣቶች ታደመዋል። የኦዳ አዋርድ ወይም የሽልማት ሥነ-ስርዓቱ በድራማ፣ በፊልምና በሙዚቃ ኪነ-ጥበብ 15 ምድብ እንደነበረዉ የሽልማቱ መስራችና ጋዜጠኛ በሻቱ ቶለማርያም ተናግራለች። ይሁን እንጅ በሻቱ ከእነዚህ 15 ምድቦች መካከል ሁለቱ ምድብ «ለየት ያለ» መሆኑን ነዉ የገለፀችዉ።

የኦዳ አዋርድ «የሕይወት ዘመን ተሸላሚ» ለመሆን የበቃዉ አንጋፋዉና ተወዳጁ ድምፃዊዉ ዶክተር አሊ ቢራ እድሜዉ 13 ሳለ ነዉ ወደ ሙዚቃዉ ዓለም የተቀላቀለዉ። አሊ ቢራ ዘመን ተሻጋሪ የሙዚቃ ሥራዎቹን በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ያዜመ ሲሆን በሃደርኛ፣ በሶማሊኛና በአረብኛም ቋንቋ ዘፍኗል። የሙዚቃ ሥራዎቹም ፍቅርን የሚያዜም፣ ተፈጥሮን የሚያደንቅና ትግልን የማጠናክር (ሬዚስታንስ) ይዘቶች ያላቸዉ ናቸዉ።

አንጋፋዉ ድምፃዊዉ ዶክተር አሊ ቢራ በመስከረም ወር በሙዚቃዉ ዓለም የዘለቀበትን የ70 ዓመት ኢዩቤልዩ አክብሯል። ዛሬ ላይ ሆኖ የወጣትነቱን ወይም የጎልማሳነቱን ዘመን የሚያስታዉሱት ከአሁኑ ዘመን የኦሮሞ ድምፃዊያኖች ዉስጥ እነማን ናቸው? በሚል ለቀረበለት ጥያቄ፣ ከወጣት ዘፋኞች ሃጫሉ ሁንዴሳና እና የአቡሽ ዘለቀን የሙዚቃ ሥራዎች መሆኑን ገልጿል።

Äthiopien Addis Ababa Odaa Award Zeremonie
አንጋፋዉ ድምፃዊዉ ዶክተር አሊ ብራ (ቀኝ) ከቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ከዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ሽልማት ስቀበልምስል Odaa Award

ሃጫሉ ሁንዴሳ በሙዚቃ ሥራዎቹ በአጭር ግዜ ዉስጥ ዝናን እና እዉቅናን ያተረፈ ወጣት ድምፃዊ ነዉ። «ተፅኖ ፈጣሪ» በሚል የኦዳ አዋርድ ሽልማት የተበረከተለት ድምፃዊ ሃጫሉ አብዛኛዉ የሙዚቃ ስራዎቹ የማኅበረሰቡን ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ባህላዊ ዉጣ ዉረዶችን የሚዳስስ ዜማዎችን ለአድማጮች ጆሮ እያደረሰ ይገኛል። እንደ ድምፃዊዉ ሃጫሉ ሁሉ በኦሮሞ ትግል ዉስጥ በኪነ-ጥበብ ሥራዎቻቸዉ አስተዋጽዖ ያደረጉ ብዙ ድምፃዊያን ቢኖሩም ሃጫሉ በሰሜን አሜሪካ በሚኔሶታ ግዛት ነዋሪ የሆነዉን ታዋቂዉ ድምፃዊ ዳዊት መኮንን እንደ አርአያዉ አድርጎ ይመለከተዋል። «እድሜዉን ከሰጠኝ ግን አንድ ቀን እንደ አሊ ቢራ ለመሆን ምኞት አለኝ» ይላል።

Äthiopien Addis Ababa Odaa Award Zeremonie
ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ በኦዳ አዋርድ ዝግጅት ላይምስል Odaa Award

ድምፃዊዉ ሃጫሉ እንደ  ዶክተር አሊ ብራ ሁሉ በሙዚቃ ሥራዎቹ የፍቅር፣ የተፈጥሮንና የትግል ይዘት ያላቸዉን ይጫወታል። የሙዚቃ ሥራዎቹን አንዱን ከአንዱ ለይቶ «ይሄን ብቻ ነዉ የምወደዉ» ብሎ ለመምረጥ ቢከብድም የአሊ ቢራ የ«ባሬዳ ኡማ» ዘፈን በአጭር ደቂቃ ዉስጥ እንዴት ተፈጥሮን  እንዳደነቃት በጣም እንደሚገርመዉ ድምፃዊዉ ሃጫሉ ይናገራል። የዘፈኑም ጭብጥ በአጭሩ፣

                                                        «የተፈጥሮ ዉበት፣ የዓለም ጌጥ

                                                          ቀልብ ሳቢ፣ የሕይወት ብርኃን

                                                          ተነግሮልህ አያልቅም፣ ነገርን ማርዘም ነዉ

                                                          የተፈጥሮን ዉበት፣ ራቢ ይጠብቅልን»

ድምፃዊ ዶክተር አሊ ቢራ ከ60ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት የዘመናዊ የኦሮሞ ሙዚቃ ዋነኛ ተወካይ በመሆኑ ይታወቃል። የኦሮሞን ባህል ማበረታታት አስቸጋሪ በነበረበት ወቅት አሊ ቢራ በኪነ-ጥበብ ሥራዉ ትልቅ ሚናን ተጫዉተዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙ ቁጥር ያላቸዉ ወጣት ድምፃዊያን በአገሪቱ በተለይም ኦሮሚያ ክልል ዉስጥ ያለዉን ነባራዊ ሁኔታን መሠረት በማድረግ በትግል (ሬዝስታንስ) ዘፈኖቻቸዉ የብዙዎችን ቀልብ እየሳቡ ይገኛሉ። በሙዚቃ ስራዎች የአንድን ማህበረሰብ ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ አጠቃላይ ሕይወቱን የሚዳሰስበት መሣሪያ መሆኑን ድምፃዊ ሃጫሉ ያምናል። ድምፃዊ ሃጫሉ ካቀነቀናቸዉ የተቃዉሞ ወይም የትግል ዜማዎች ዉስጥ «ማላን ጅራ እና ጅራ» የተሰኘዉን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።

ሙሉውን ዝግጅቱን ለማዳመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

መርጋ ዮናስ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ