1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተቃውሞ የበዛበት ‘ኡበር’

ረቡዕ፣ ነሐሴ 27 2007

ባደጉት አገሮች የቴክኖሎጂ ውጤቶችና የሳይንስ ትሩፋቶች የሰው ልጅን የዕለት ተለት የኑሮ እንቅስቃሴ እየለወጡት ነው። ኡበር የተሰኘ የተንቀሳቃሽ ስልክ አፕልኬሽን የታክሲ አገልግሎት ከፍተኛ ተቀባይነት ቢያገኝም በተለምዷዊው ስርዓት አገልግሎት አቅራቢዎች ግን ከፍተኛ ትችት ሲሰነዘርበት ይደመጣል።

https://p.dw.com/p/1GQGi
Symbolbild Uber
ምስል picture-alliance/dpa/J. Büttner

ተቃውሞ የበዛበት ‘ኡበር’

ጻህፍት በሳይንሳዊ ልቦለዶች የፊልም ባለሙያዎች በስራዎቻቸው ይመጣሉ ብለው የተነበዩላቸው ሮቦቶች ባደጉት አገራት ብቅ ብለዋል። የሰው ልጅ የለት ተለት የስራ እንቅስቃሴን የሚያግዙት፤ውስብስብ እና አሰልቺ ተግባራትን የሚከውኑት ማሽኖች በዓለም የኢኮኖሚ መስተጋብር ላይ ያላቸው ተጽዕኖ ከፍተኛ ሆኗል። አመጣጣቸው ቀድሞ እንደተተነበየው የሰው ቁመና ተላብሰው ብቻ ግን አይደለም። የማይታዩ፤የማይዳሰሱ ግን ደግሞ በቀላሉ ከሰው ልጅ እንቅስቃሴ ጋር የተዋሃዱ ሆነዋል።

ጆን ማርኮፍ በሮቦት ቴክኖሎጂ ፍቅር የተነደፈ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ጋዜጠኛ ነው።ላለፉት ሁለት አስርት የቴክኖሎጂውን ሙከራዎች ስኬቶችና ተግዳሮቶች ለኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ የዘገበዉ ማርኮፍ ‘Machines of Loving Grace’ የተሰኘ መጽሃፍ ለህትመት አብቅቷል። «ለሮቦት ሰፋ ያለ ትርጓሜ ሰጥቻለሁ።» የሚለዉ ጆን ማርኮፍ «ሮቦት በእግሩ የሚጓዝ፤የሚሸከምና የሚቆፍር ጠንካራ ማሽን ሊሆን ይችላል። በዕለት ተለት የሰው ልጅ እንቅስቃሴ ውስጥ እገዛ የሚያቀርቡ የኮምፒውተርና የተንቀሳቃሽ ስልክ ሶፍትዌሮች ግን ለጊዜው ቀዳሚ ናቸው።» ይላል። ማርኮፍ የጉግል መፈለጊያን፤በተንቀሳቃሽ ስልክ የአቅጣጫ ጠቋሚ አፕልኬሽኖችን በምሳሌነት ያነሳል።

Bildergalerie Metropolen der Welt
ምስል Fotolia/Delphotostock

በዓለም አቀፉ የኢንተርኔት አገልግሎት አማካኝነት በተሽከርካሪዎች፤ተንቀሳቃሽ ስልኮች፤የመዝናኛና የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች ላይ በቀላሉና በአነስተኛ ክፍያ የሚጫኑት አፕልኬሽኖች (APPS) ባደጉት አገሮች ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝተው ኑሮ ማቀላጠፉን ተያይዘውታል።

ኡበር የተሰኘው አፕልኬሽን ስራ ላይ ከዋለ አራት አመታት ተቆጠሩ። በአሜሪካን አገር ስራውን የጀመረው ኩባንያ መስራቾች ትራቪስ ካላኒክና ጋሬት ካምፕ የተባሉ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ናቸው። ይህ የኡበር አፕልኬሽን በአንድሮይድና አፕል ኦፕሬቲንግ ሲስተም በሚጠቀሙ ስልኮች ላይ የሚጫን ሲሆን ዋንኛ አገልግሎቱ የታክሲ አገልግሎት ፈላጊና አቅራቢን ማገናኘት ነው። የኡበር አፕልኬሽን በቀዳሚነት ይዞ የመጣው አዲስ ነገር ቀድሞ በነበረው የታክሲ አገልግሎት ፈላጊና ሰጪ የሚገናኙበትን መንገድ መቀየሩ ነው።

በአሜሪካን ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ነዋሪ የሆነው ዮሴፍ ጎሹ የኡበር አሽከርካሪ ወይም ሾፌር ነው። ዮሴፍ የኡበር አፕልኬሽን ቀድሞ የታክሲ አገልግሎት ፈላጊና የአገልግሎቱ አቅራቢ ይገናኙበት የነበረውን መንገድ ሙሉ በሙሉ መቀየሩን ይናገራል።

ኡበር ቴክኖሎጂውና ኩባንያው ውልደቱ አሜሪካን ይሁን እንጂ በአውሮጳና እስያ ገበያ ስራውን ጀምሯል። ፋቢያን ኔስማን በጀርመን የኩባንያው ተወካይ ናቸው።

«ስልኬን በማስነሳት ወደ ተጫኑት አፕልኬሽኖች እሄዳለሁ። አፕልኬሽኑ በጂፒኤስ አማካኝነት ያለሁበትን ቦታ ይመዘግባል። በኡበር አፕልኬሽን መሰረት በአስር ደቂቃ ርቀት ላይ የኡበር ተሽከርካሪ ይገኛል። ጉዞ የምጀምርበትን ቦታ በማሳወቅ ለመጓዝ መፈለጌን አሳውቃለሁ።»

የትራንስፖርት አገልግሎት ለሚፈልጉት መንገደኞች ኡበር ከታክሲ አገልግሎት የተለየ ባይሆንም በርካታ ጥቅማጥቆች ግን አሉት። አገልግሎት ፈላጊና አቅራቢ ቀድመው ይተዋወቃሉ። የክፍያ አገልግሎቱ በቀጥታ ኩባንያው ባዘጋጀው የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ካርድ የሚፈጸም ሲሆን የእጅ በጅ የገንዘብ ዝውውርን ቀንሷል። ኩባንያው ደንበኛና አገልግሎት አቅራቢውን ላገናኘበት ከ5-20 በመቶ በመቁረጥ ቀሪውን ወደ አሽከርካሪው ባንክ ሂሳብ ያስተላልፋል። የኡበር የክፍያ ስርዓት «የጥሬ ገንዘብ ዝውውር አስቀርቷል።» የሚለው ዮሴፍ የአከፋፈል ስርዓቱ «ለሾፌሩም ለተገልጋዩም ጊዜ ይቆጥባል።» ሲል ይናገራል። የጥሬ ገንዘብ ዝውውር አለመኖሩ ደግሞ በስራ ዘርፉ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እንዲቀነሱ አስችሏል።

የአገልግሎት ፈላጊዎች ከተለመደው የታክሲ አገልግሎት ኡበርን የሚመርጡባቸው በርካታ ምክንያቶች አሏቸው። ቀዳሚው ለአገልግሎት ቀላል መሆኑና ከሌሎች የታክሲ አገልግሎቶች እስከ 40 በመቶ በሚደርስ ቅናሽ አገልግሎቱን ማቅረቡ ናቸው።

Frankreich Ausschreitungen Protest Taxifahrer
ምስል picture-alliance/dpa/I. Langsdon

ኡበር ኩባንያ የራሱ መኪኖች የሉትም። የግል መኪኖቻቸውን በመጠቀም ከኡበር ጋር መስራት የሚፈልጉ አሽከርካሪዎች በኩባንያው አጋር ተብለው ይጠራሉ። ተሽከርካሪው የመድህን ዋስትና ሊኖረው የሚገባ ሲሆን አሽከርካሪዎቹ በአጋርነት ከኩባንያው ጋር ለመስራት እንደሚገኙበት አገር ሁኔታ የተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል። ቅድመ ሁኔታዎቹ ግን በተለመደው የታክሲ አገልግሎት ለመሰማራት ከሚጠየቁት እጅጉን ያነሱ ናቸው። ለፋቢያን ኔስማን ኡበር የሚያቀርበው አገልግሎት ሳይሆን ማህበረሰቡ ያለውን ሃብት በጋራ የሚጠቀምበት መንገድ ነው።

«ኡበር አገልግሎት ስለማቅረብ አይደለም። ያለንን ንብረት በጋራ የመጠቀምን መንገድ ነው። እኔም አንተም መኪና አለን። ስለዚህ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መጓጓዝ ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር ብጋራው ችግር የለብኝም። ለዚያም ነው አዲስ አወቃቀር የምንከተለው። እነዚህ የግል ንብረቶቼ ናቸው። እናም ሌሎች ሰዎች እንዲገለገሉበት ፈቃዴ ነው።»

የኡበር ቴክኖሎጂ በ60 አገራት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። የቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ ተመሳሳይ በመሆኑ ጉዞ ለሚበዛባቸው ሰራተኞችና የአገር ጎብኚዎች ተመራጭ የመጓጓዣ አገልግሎት ሆኗል። በ200,000 ዶላር የተመሰረተው ኩባንያ በዚህ አመት ያለዉ ሐብት እስከ 50 ቢሊዮን ዶላር ድረስ ተገምቷል። በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም ብቻ እስከ 2 ቢሊዮን ድረስ ገቢ እንደሚያስገባ ይጠበቃል።

ኩባንያውም ሆነ ቴክኖሎጂው ግን በሄደበት ሁሉ አልቀናውም። በሰሜን አሜሪካ ዛሬም ድረስ አከራካሪነቱ እንደቀጠለ ነው። በጀርመን እና የፈረንሳይ የታክሲ አገልግሎት ማህበራት ኩባንያውን ፍርድ ቤት ወስደው እስከ ማሳገድ ደርሰዋል። ስቴፋን ቤርንድት የጀርመን ታክሲ ማህበር ኃላፊ ናቸው።

«ኡበር በማህበረሰቡ ተቃባይነት የሌላቸው የራሱን አዳዲስ ህግጋትና መመሪያዎች ነው ይዞ የመጣው። ለዚያም ነው በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ህግጋት የሚያጸድቀው ማን ነው ብለን የምንጠይቀው። ማህበረሰቡ ራሱ ወይስ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች? »

China Taxi App Proteste
ምስል imago/R. Wölk

የፍራንክ ፈርት ፍርድ ቤት የኡበር አገልግሎትን ከጀርመን ገበያ አግዶት ቆይቷል።። ኩባንያው አሊያም በኩባንያው ስር የሚንቀሳቀስ አሽከርካሪ የፍርድ ቤቱን እግድ ቢጥስ የ250,000 ዩሮ ቅጣት ይጠብቀዋል ተብሎ ነበር። ፍርድ ቤቱ ኡበርን ካገደባቸው ምክንያቶች አንዱ በቴክኖሎጂው አማካኝነት ግልጋሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎች አስፈላጊው የንግድ ፈቃድ የላቸውም የሚል ነው።

ኡበር በጀርመን የተጣለበት ገደብ ተነስቶለታል። ይሁንና አሁንም በርካታ ወቀሳ እየተሰነዘረበት ይገኛል። በበርሊን ከተማ ታክሲ የሚያሰማሩት በኡበር ላይ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ያስተባበሩት ሪቻርድ ሊዮፖልድ አሁንም ወቀሳቸውን አላቆሙም።

«የአውቶቡስና ታክሲ አገልግሎቱን የሚያቀርበው የግል ኩባንያም ይሁን የመንግስት ተቋም የመጓጓዣ ተመኑ ሊወሰን ይገባል ብሎ ብሎ የወሰነው ማህበረሰቡ ነው። የጀርመን መንግስት የታክሲ አገልግሎት ፍላጎቱ በሚበዛበት ወቅት የመጓጓዣ ተመኑ እንደማይወደድ ማረጋገጥ አለበት። ውድድሩ ፍትሐዊ የሚሆነው ኡበር እኛ የምንከፍለውን ክፍያ እኩል ሲከፍል ነው።»

ፋቢያን ኔስትማን «አንዳንድ ሰዎች ኡበርን እንደ ስጋት መቁጠራቸው እሙን ነው። ይሁንና እንደአለመታደል ሆኖ ይህ የቀደመውን አሰራር ሰብረው ለመግባት የሚሞክሩ አዳዲስ የስራ ሃሳቦች ሁሉ የሚገጥማቸው ፈተና ነው። ተቃውሞው ከባህላዊው አሰራር የሚመነጭ ነው።»ሲሉ የገበያ ትንቅንቁን ያስረዳሉ።

Taxifahrer Streik wegen Handy-Apps 11.06.2014 Paris
ምስል Reuters

ፈረንሳይ፤ሆላንድና ስፔን በመሳሰሉ አገሮች አሁንም የኡበር ቴክኖሎጂ የተወሰኑ አገልግሎቶች እግድ ላይ ናቸው። ጀርመንን ጨምሮ ኩባንያው የስራ ፈቃድ ባገኘባቸው አገሮች ደግሞ በርካታ ፈተናዎች ተጋርጠውበታል። ፈጽሞ ከስራ የተከለከለባቸውም አልጠፉም።

ኡበር በተገልጋዮቹ ዘንድ ከፍ ያለ ተቀባይነት አግኝቶ ትርፋማ ቢሆንም ለዘመናት ከተዘረጉ ህግጋት፤ስርዓቶች እና የአሰራር ዘይቤዎች ጋር እየተላተመ ነው። ኩባንያውም ሆነ ቴክኖሎጂው ከሚሰራባቸው አገራት ህግጋት ጋር ለማጣጣም በመታገል ላይ ነው። ሁነቱን በትኩረት ለሚከታተሉ የሰው ልጅ የስራ ውጤቶች ከራሱ የአኗኗር ዘይቤ ጋር ሲጋጭ ለመታዘብ ኡበር ሁነኛው ምሳሌ ነው።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ