1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተቃዉሞ በኢትዮጵያ

Merga Yonas Bulaማክሰኞ፣ ነሐሴ 3 2008

ሰሞኑን በኦሮሚያና በአማራ ክልል በተካሄደዉ ተቃዉሞ ላይ የመንግስት የፀጥታ ኃይል በወሰደዉ ርምጃ የብዙ ሰዉ ህወት እንዳለፈ እና በመቶዎች የሚቆጠሩ እንደታሰሩም ዘገባዎች ያሳያሉ።

https://p.dw.com/p/1Jep9
Äthiopien Regierung Soldaten ARCHIV
ምስል picture alliance/AP Photo/ltomlinson

[No title]

ተቃዋሚዎች የሚያካሂዱት ሰልፍ ሠላማዊ መሆኑን፣ ለሚመለከተዉ አካልም የሰብዓዊም ሆነ የድሞክራሲያዊ መብት ጥያቄያቸዉን ለማቅረብ እንደሚፈልጉ ነው የሚናገሩት። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግስት ሰልፈኞቹን «ፀረ-ሰላም» ወይም «ፀረ-ልማት ኃይል» እንዲሁም «ሁከት ፈጥሮ ህገ መንግስቱን በሃይል ለመናድ» የሚሞክሩ ሲል ይወንጅላል።


«ማንኛዉም ዜጋ ጥያቄ ካለዉ ህገመንግስቱ በሚፈቅደዉ አግባብ በሰላማዊ መንገድ ሰልፍ አካሄዶ ለመንግስት ጥያቄዉን ማቅረብ እንደሚችል፣ ግን ጦር መሳርያ ይዞ በመዉጣት፣ ቤት በማቃጠል፣ ፈንጅ በመወርወር ወይም የሰዉ ህወት በማጥፋት አይደልም» ሲሉ በመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የህዝብ ግኑኝነት ሐላፍ አቶ መሃመድ ሳይድ ለዶቼ ቬሌ ይናገራሉ። የመንግስት ተችዎች መንግስት ከመግደል እና ከማሰር አደባባይ ለወጣው ህዝብ ጥያቄ መልስ መስጠት የተሳነዉ ለምን ይሆን? ብለዉ የሚጠይቁ አሉ።


ይህ «የአንድ ወቅት ግርግር ነዉ፣ ያልፋል» የሚሉት አቶ መሃመድ መንግስት ከህዝቡ ጋር እየተወያየ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን ከማህበረሰቡ ጠይቀን ነበር። በአድስ አበባ ነዋሪ የሆኑት ግን ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የጠየቁት የመንግስትን ዉንጀላና የአቶ መሃመድ መልስን ይተቻሉ።

Äthiopien Protest
ምስል Reuters/T. Negeri

የወሎ አከባቢ ነዋሪ ነኝ ያሉትም ስማቸዉ እንዲያዝ ጠይቀዉ ህዝብ ስለ ተቃዉሞዉ ግንዛቤ የለዉም ካሉ በዋላ መንግስት ለጥያቄዉ መልስ ለመስጠት ግዜ ያስፈልጋል ይላሉ።

ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የጠየቁት ሌላኛዉ በምስራቅ ሃራርጌ የበዴሳ ነዋሪ የሆኑት የዛሬ ሳምንት አምስት ሰዎች በአከባቢያቸዉ በፀጥታ ሃይል መገደላቸዉን ጠቅሰዉ ጥያቄያችን የተቀበለ አካል የለም ይላሉ።

በፌስቡክ ደረ ገፃችን ላይም ይሄን ጉዳይ በተመለከተ አስተያየት ከሰጡን ዉስጥ ሰላማዊ ሰልፍ መሳርያ ይዞ፣ ንብረት እያቃጠሉና ባንድራ እየረገጡ አይደልም የሚሉ በአንድ ጎራ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ መንግስት አፍ እንጅ ጆሮ የለዉም፣ «መንግስት ህጋዊ የሆነ ሰላማዊ ሰልፍ እስካልፈቀደ ህዝቡ ህጋዊ ያልሆነ ሰልፍ እንደሚያደርግ የታወቀ ነው» ሲሉ አስተያየታቸዉን ሰንዝረዋል።

መርጋ ዮናስ

ሕሩት መለሰ