1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በወላይታ ተቃውሞ የሰው ሕይወት ጠፋ

ሰኞ፣ ሰኔ 11 2010

በወላይታ ሶዶ ከተማ የተጀመረ ተቃውሞ ወደ ረብሻ ተቀይሮ ሁለት ሰዎች ሲሞቱ፣ የመንግሥት ተቋማትና ባንክ ጉዳት እንደደረሰባቸው ነዋሪዎች ገለጹ። የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ታዘዋል። በሐዋሳ ከተማ ከተለያዩ አካባቢው የተፈናቀሉ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መስቀል አደባባይ በተባለ ቦታ መጠለላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/2zhIN
Äthiopien Busbahnhof in Soddo
ምስል Imago/Loop Images

በደቡብ ክልል በሐዋሳ ከተማ በወላይታ ተወላጆች ላይ ተፈጽሟል የተባለን ግድያ እና ጥቃት በመቃወም በወላይታ ሶዶ ከተማ ዛሬ ጠዋት በተካሄደ ሰልፍ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱን የከተማዋ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ወደ ረብሻ ተለወጠ በተባለው ሰላማዊ ሰልፍ ንብረት መውደሙን እና መዘረፉንም ነዋሪዎች ገልጸዋል። 
 
ሰልፈኞቹ አደባባይ የወጡት የሲዳማ የዘመን መለወጫ የፊቼ ጫምባላላ በዓል በሚከበርበት ዕለት እና ከዚያ በኋላ በነበሩ ቀናት በሐዋሳ ከተማ በወላይታ ተወላጆች ላይ ተፈጽሟል ያሉትን ጥቃት ለመቃወም ነው። ስሙ እንዳይገለፅ የፈለገ አንድ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በዛሬው ተቃውሞ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን ተናግሯል። ተማሪው በከተማዋ ከተካሄደው ሰልፍ በኋላ በግቢው ማደር እንደማይችሉ ተነግሯቸው ወደየመጡበት ለመጓዝ ተሽከርካሪ ፍለጋ ላይ መሆናቸውን አስረድቷል።

"ግቢው ውስጥ ነው ያለነው። መኪና የለም። ግቢው ውስጥ ደግሞ አታድሩም ተብሏል።  ከመሸ ነው እየወጣን ያለነው። ሴቶችም በየቦታው እየሔዱ እያለቀሱ ነው ያሉት። ዛሬ ግቢ ማደር የለባችሁም ውጡ ብለው ነግረውናል። በግቢው ስፒከር ነው የተነገረን። መኪናዎች በየቦታው ተቃጥለዋል። ግቢ በር ላይ ያሉ ፎቆች ተቃጥለዋል፤ ንብረት ወድሟል። ሰልፍ ነበረ፤ ሁለት ሰው ደግሞ ሞቷል" ሲል ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።  
ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ ግን የሞተው አንድ ተማሪ ብቻ ነው ይላሉ። ነዋሪው "የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሲቪል ሰው ገብቶ እነሱም ትንሽ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ከዩኒቨርሲቲ አንድ ተማሪ ሞቷል" ብለዋል።
ማርያም ሰፈር፣ ኢነጊዶ ቀበሌ፣ አራዳ ክፍለ ከተማ፣ መርካቶ ክፍለ ከተማ በተለምዶ አበበ ፈለቀ ሆቴል በተባሉ የከተማዋ አካባቢዎች የተነሳው የዛሬ ጠዋቱ ሰልፍ አጀማመሩ ሰላማዊ ቢሆንም በግለሰቦች ምክንያት ወደ ረብሻ መቀየሩን አስረድተዋል። በረብሻው "የወላይታ ሶዶ የትራንስፖርት ቢሮ እንዳለ ወድሟል፤ ብርም ተዘርፏል፤ ፋይናንስ ቢሮ ባይቃጠልም ሰነዶች እና ሞተሮች ተቃጥለዋል፤ ከአጂፕ ወረድ ብሎ ማርያም ሰፈር አካባቢ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ እንዳለ ከጥቅም ውጪ ሆኗል" ሲሉ በንብረት ላይ ስለደረሰው ጉዳት አብራርተዋል።

ሁለቱም የአይን እማኞች በሐዋሳ ከተማ ከተፈጠረው ግጭት በኋላ የወላይታ ሶዶ ከተማ ውጥረት ውስጥ እንዳለች አስረድተዋል። በሐዋሳ ከተማ እስከ ትናንት ድረስ በነበረ ግጭት 10 ሰዎች መገደላቸውን የደቡብ ክልል የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታውቋል። ጽህፈት ቤቱ በትናንትናው ዕለት በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ "በድንጋይ መወራወርና በስድብ" ተጀመረ ያለው ግርግር "ቀስ በቀስ ብሔር ወይም ዘር ተኮር ጥቃት የመፈፀም አዝማሚያ" እንደታየበት ገልጿል። በጽህፈት ቤቱ መግለጫ መሰረት 80 ሰዎች ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን 2500 ተፈናቅለዋል።

Karte Sodo Ethiopia ENG

አንድ የሐዋሳ ነዋሪ ከመኖሪያ ቤታቸው ቤታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ዛሬም ድረስ በከተማዋ ወደሚገኘው አደባባይ እየተመሙ መሆኑን አስረድተዋል። እንደ የአይን እማኙ ገለጻ ከሆነ ሞኖፖል እና አዲስ ከተማ ከተባሉ የሐዋሳ ዳርቻ አካቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎች በተለምዶ አይሱዙ እየተባለ በሚጠራው ተሽከርካሪ እየተጫኑ ወደ መስቀል አደባባይ ይደርሳሉ። "እጅግ በጣም ብዙ ናቸው። ሕፃናት እየያዙ፤ ትንሽ ፔስታል እያንጠለጠሉ ነው የሚመጡት። በጣም ብዙ ሺህ ናቸው" የሚሉት ግለሰብ የማፈናቀሉ ተግባር ወደ መካከለኛው የከተማዋ ክፍል እየተሸጋገረ እንደሆነ ገልጸዋል። "ከጫፍ ጫፍ አካባቢ እንደዘመኑ ቋንቋ መጤ የሚባለው እየተፈናቀለ ወደ መሐል ይመጣል። አሁን ደግሞ ምን ተጀምሯል? መሐል አካባቢ ያለ የሌላ አካባቢ ተወላጅ የሚባለውንም እየተዘረፈ ይባረራል" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።  

የሐዋሳው ነዋሪ በከተማዋ በተለምዶ ባጃጅ ተብለው የሚጠሩ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎችን የመንጠቅ፣ ነዋሪዎችን የመዝረፍ ድርጊቶች መመልከታቸውን አስረድተዋል። ከተማዋ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ብትገኝም የተጠናከረ የጸጥታ ጥበቃ አለመኖሩንም ገልጸዋል። በመንገዶች ላይ የሚታዩት የጸጥታ አስከባሪዎችም ቢሆኑ "ተዘርፈው ወይም ደግሞ የተፈናቀሉ ሰዎችን ሳናግር እያዩ ምንም እርምጃ አይወስዱም" ሲሉ በሁኔታው ግራ መጋባታቸውን ይገልጻሉ። "ባይኔ ሰው ሲደበደብ አይቻለሁ፣ ሲዘረፍ ባይኔ አይቻለሁ። ከጸጥታ አስከባሪዎች ግን ምንም እርምጃ አላየሁም። ይልቁንስ ሰው በየመንደሩ እየተሰበሰበ እየተደራጀ መንደሩን ሲጠብቅ ይውላል፤ ሲጠብቅ ያድራል" የሚሉት የሐዋሳ ነዋሪ የጸጥታ ጥበቃውን ከዚህ ቀደም ከነበረው "የላላ" ሲሉ ገልጸውታል።

"ተጠቂዎች አሉ፣ ቂም አለ፣ በየአካባቢው ጥርስ መነካከስ አለ። ወንጀለኞቹን መያዝ እና መጠየቅ ካልተቻለ፤ ማረጋጋት ካልተሰራ ወደ አስጊ ሁኔታ ሊያመራ ይችላል" ሲሉም ሥጋታቸውን አጋርተዋል። ችግሩ ከሥር ከመሰረቱ መፍትሔ ያሻዋል የሚሉት ግለሰቡ ግጭቱ እንዲረጋጋ የማይፈልጉ ወገኖች እንዳሉ ያስረዳሉ። "በጣም ውድ በሆነ መኪና፣ ሕዝብ በሚቀሰቅስ መልኩ እየጨፈሩ የሚያልፉ ሰዎች ታያለህ። ይኼ ደግሞ ሌላ አላማ አለው። ትንሽ የተረጋጋ ሲመስል እንዳይረጋጋ የሚፈልጉ ሰዎች እንዳሉ ነው የምታየው" የሚሉት ነዋሪው ችግሩ ከምንጩ ካልተፈታ ለውጥ አይመጣም የሚል ስጋት አላቸው።

የደቡብ ክልል የኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኃይሉ በሐዋሳ ከተማ የነበረው ሁኔታ መረጋጋት ቢያሳይም "በአንዳንድ የከተማ ዳርቻዎች ላይ አልፎ አልፎ የሚታዩ በዘረፋ መልክ፣ በትንኮሳ መልክ" የሚገለጹ ነገሮች አሉ ሲሉ ዛሬ ለብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል። ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ ትናንትናው ማምሻውን በሰጡት መግለጫ በችግሩ ላይ ከየከተሞቹ ነዋሪዎች ጋር ለመነጋገር በቀጣዩ ሳምንት ወደ አካባቢዎቹ እንደሚሄዱ ጠቁመዋል።

እሸቴ በቀለ

ተስፋለም ወልደየስ