1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮምያ የተጠራዉ አድማ

Merga Yonas Bula
ሰኞ፣ የካቲት 5 2010

በኦሮሚያ ክልል ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚዘልቀዉ የንግድ ወይም የግብይት እንቅስቃሴ ላይ የተጠራው አድማ ተግባራዊ መሆን መጀመሩን ከተለያዩ ቦታዎች በመደወል ያሰባሰብናቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።

https://p.dw.com/p/2sYTl
12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

አድማዉ የተዘጋጀዉ «ቄሮ እና ቃሬ» በመባል በሚታወቁት የክልሉ ወጣቶች መሆኑ ሲነገር፤ የፖለቲካ እስረኞች ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ፣ በክልሉ ያለዉ የመከላከያ ሠራዊት ለቅቆ እንዲወጣ፣ የዜጎች ግድያ እንዲቆም የሚሉ እና ሌሎችም ጥያቄዎች መቅረባቸውን ለመረዳት ተችለዋል።

የማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ አድማዉ በክልሉ ያሉትን 19ኙንም ዞኖች አካልሏል። በዚህም ከአዲስ አበባ በአራቱ መዉጫዎች ማለትም በአዳማ፣ በሱሉልታ፤ ሰበታ እና አምቦ መስመሮች የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ መቋረጡን ከአካባቢው ነዋሪዎች ለመረዳት ተችለዋል። የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ አንድ አድማጭ በዋትስ አፕ በላኩልን ጥቆማ መሠረት ሚስታቸዉ አምቦ ዩኒቨርሲቲ እንደሚማሩ ጠቅሰው ዛሬ ጥዋት ግን ወደዚያ ለመሄድ መጓጓዣ እንዳላገኙ ገልፀዉልናል። በተመሳሳይም በሌሎች ቦታች የሚኖሩ ግን ስማቸዉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ግለሰቦች ያዩትን እና የሰሙትን እንዲህ አጋርተውናል።

ወጣቶቹ ያነሱት ጥያቄ የክልሉ መንግሥት አምኖ ተቀብሎ ለመፍታት እየሞከረ መሆኑን የሚናገሩት በኦሮሚያ ክልል በፍትህ ቢሮ የኮሙኒኬሼን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ታዬ ዳንዳኣ አድማዉ ትክክል ነዉ ብለን አናስብም ይላሉ። አቶ ታዬ: «በማይፈለግ መንገድ ተኬዶ የግብይት አድማ መጥራት ትክክል ነዉ ብለን አናስብም። ይሁን እንጅ አድማዉ ከተጠራ፣ ሰዉ ይሄን ለማድረግ መብቱ ስለሆነ፣ ጉዳዩ ወደ ያልተፈለገ አቅጣጫ እንዳያመራ የፀጥታ አካሎች በሰላም ጠብቆ፣ አረጋግቶ፤ በሰላም እንዲጠናቀቅ እንፈልጋለን።»

የኦሮምያ እና የኢትዮጵያ ሶማሊ አዋሳኝ ድንበሮች ላይ በተፈጠረዉ ግጭት ምክንያት ከቄያቸዉ ተፈናቅለዉ በሐረሪ ክልል ስር ብትገኝም በምሥራቅ ሐርሬጌ ዞን በኦሮሚያ ክልል የሚተዳደረው የሐማሬሳ ካምፕ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙት ላይ የመከላክያ ሠራዊት ትናንት ወስዷል በተባለው የኃይል ርምጃ ሰዎች መሞታቸው እና መቁሰላቸው ተገልጿል። ዛሬም ወጣቶች መንግሥት ቃሉን እያከበረ አይደልም የሚል እና ሌሎች ተቃዉሞች ሲያሰሙ እንደነበረ የዓይን እማኞች ይናገራሉ። የኦሮሚያ የፍትህ ብሮ የኮሙኒኬሼን ጉዳዮች ኃላፊ የሐማሬሳዉ ክስተት ኅብረተሰቡን አያናድድም ማለት እንደማይቻል አስረዳሉ።

አቶ ታዬ: « ትላንት የሆነ ጉዳይ እኛ እንደ መንግሥት ወንጀል መሆኑን እናምናለን። በመጀመርያ ደረጃ በሕግ እንደምናዉቀዉ መከላከያ ድንበር እንጅ ከተማ አይጠብቅም። በአከባቢዉ የተፈጠረ ትልቅ ችግር የለም። ሕህል የጫነ መኪና እዚህ ካምፕ ይግባ ብሎ ያዙት የሚባል ነገር አለ። በባዶ እጃቸዉ የወጡ ሰዎችን ግንባር ላይ መትቶ እስከመግደል ደረጃ ደርሰዋል። ጭካኔ በተሞላ የተደረገ ድርጊት ነዉ፣ ይህ ትክክል አይደልም። በፍትም እንድህ አይነት ድርግት ተፈፅመዋል። ይጠየቃሉ ተብሎ ሳይጠየቁ እስካሁን አሉ። የክልሉ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ አጠናክሮ በመከታተል ይህን ድርጊት የፈፀሙ ተለይተው  እንዲጠየቁ ያደርጋል። በእርግጥ እንዲህ አይነት ወንጀል ሲፈፀም ማህበረሰቡን አያናድድም ማለት አይቻልም፤ ይህ አሳፋሪና ሆድን የሚያቃጥል ስለሆነ።»

የግብይት አድማዉን ተከትሎ እየተካሄደ ባለዉ ተቃዉሞም የፀጥታ አካሎች በወሰዱት ርምጃ የሰዉ ሕይወት መጥፋቱንም የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እየገለጹ ነው።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሰ