1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ የሩጫ ዝግጅት እና የፀጥታ ስጋት 

Merga Yonas Bula
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 27 2010

የአሮሚያ አትሌቲክስ ማሕበር በመጪዉ ሳምንት እሁድ ከኦሮምያና ከኢትዮጵያ ሶማሊ ክልሎች አዋሳኝ ድንበሮች ለተፈናቀሉት የመርጃ ገንዘብ ለመሰብበ የሩጫ ዝግጅት ለማድረግ ማቀዱን አመላክቷል። በዚህ  የሩጫ ውድድርም ከ150 ሺህ በላይ ቲሸርቶች ታትመዉ ለሽያጭ እየቀረቡ እንደሆነ ዝግጅቱን የሚያስተባብሩት ለዶይቼ ቬሌ ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/2qPX6
Äthiopien Flüchtlinge vor ethnischer Gewalt
ምስል DW/J. Jeffrey

Running Event for Charity in Oromia - MP3-Stereo

ከኦሮሚያ እና ከኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ ድንበሮች በሺህዎች ለሚቆጠሩ ተፈናቃዮች መርጃ የሚሆን ገንዘብ በተለያዩ መንገዶች እየተሰበሰበ እንደሚገኝ ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል። የኦሮሚያ አትሌቲክስ ማሕበር በበኩሉ ለተፈናቀሉት መርጃ የሚሆን ገንዘብ ለመሰብሰብ ጥር 6 ቀን 2010 ዓ.ም. የሩጫ ዉድድር ለማካሄድ መዘጋጀቱን ለመረዳት ተችሏል።

የሩጫ ዉድድሩ የተዘጋጀዉ በአሮሚያ አትሌቲክስ ማሕበር እንደሆነና እሱንም የሚያቀናጅ ኮሚቴ መቋቋሙን ከኮሚቴዉ አባላት አንዱ አቶ ገመዳ ኦልአና ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። በዋናነት የሩጫ ውድድሩ አላማ ያደረገዉ ወደ 600 ሺህ የሚገመቱትን ተፈናቃዮች ለመርዳት እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ገመዳ ወደ 150 ሺህ ቲሸርቶች ለዚሁ ሲባል እስካሁን መታተማቸዉንም ገልፀዋል።

በፌስቡክ ገፃቸዉ ላይም አቶ ገመዳ የአንዱ ዋጋ 200 ብር መሆኑን አመልክተዋል። የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸዉ ረቡዕ ዕለት በፌስቡክ ገጻቸዉ ቲሸርቱ ፊንፊኔ ላይ በ200 ብር፤ በክልሉ ዞኖች ዉስጥ ደግሞ በ150 ብር እንደሚሸጥ ጠቅሰዋል። 

የኮሚቴዉ አባል የሁኑት የኦሮሚያ አትሌቶች ማሕበር ፕሬዝዳንት አትሌት ኢብራህም ጄላን የቲሸርቶቹን ዋጋ፣ የተሳታፊዎችን ቁጥር እና ለመሰብሰብ ስለታቀደ ገንዘብ ለዶይቼ ቬሌ አብራርተዋል። 

Leichtathletik WM Moskau 2013 Ibrahim Jeilan
አትሌት ኢብራህም ጀዕላን ምስል DW/H.Turuneh

ገንዘቡ ከተሰበሰበ በኋላ የተፈናቀሉትን ለመርዳት ለተቋቋመ ለሌላ ኮሚቴ እንደሚሰጥ አቶ ገመዳ ይናገራሉ። የሩጫ ውድድሩም በ19ኙም የኦሮሚያ ዞኖች በሚገኙት 22 ከተሞች ላይ እንደሚካሄድም አክለዉ አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ ሩጫዉ እንዲካሄድ ከታቀደባቸዉ 22 ከተሞች ዉስጥ ቢያንስ ስምንት በሚሆኑት ከተሞች ላይ በፀጥታ ስጋት ምክንያት ውድድሩ ይካሄድ፤ አይካሄድ በሚለዉ ጉዳይ ኮሚቴዉ እና የፀጥታ አካላት ዉይይት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ከዉስጥ የደረሰን መረጃ ያመለክታል። አትሌት ኢብራሂም ግን ሩጫው በአንድ ከተማ ተካሂዶ በሌላው የሚቀርበት ምክንያት የለም ይላሉ።

አዲስ አበባ ላይ ባለፈዉ እሁድ ለማካሄድ ታቅዶ እንደነበረ እና የሩጫው ቲሸርቶች በግዜዉ ስላልደረሱ ቀኑ መራዘሙንም አትሌት ኢብራሂም ተናግረዋል።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሠ