1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ በሀገር ዉስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች ጉዳይ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 3 2009

ዓለም አቀፉ በሀገር ዉስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች ተከታታይ ማዕከል በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተዉ የተፈጥሮ አደጋና ግጭቶች መንስኤ 450,000 ሰዎች ከቀያቸዉ መፈናቀላቸዉን ባለፈዉ ሳምንት ባወጣዉ ዘገባ አመልክቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት የተጠቀሰዉን ቁጥር አለመቀበሉን መገናኛ ብዙሃን ጠቅሰዋል።

https://p.dw.com/p/2UA4b
Flüchtlinge Äthiopien
ምስል AP

IDP in Ethiopia - MP3-Stereo

ይህ «ለመጀመርያ ግዜ የተቀነባበረ» ዘገባ መሆኑን የሚናገሩት በዓለም አቀፉ በሀገር ዉስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች ተከታታይ ማዕከል በግጭትና በጥቃት ጉዳይ ላይ ከፍተኛ የስልት አማካሪ ኤሊዛቤት ራሽንግ፣ የተፈናቃዮችን መብት ለማስጠበቅ በአፍሪቃ ኅብረት የወጣዉን የካምፓላ ስምምነት ምክንያት መማድረግ ዘገባዉ ይፋ መደረጉን ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል። እንደ ዘገባዉ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተዉ የተፈጥሮ አደጋና ግጭቶች መንስኤ 450,000 ሰዎች ከቀያቸዉ ተፈናቅለዋል።

በምሥራቅ አፍሪቃም ከሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ከሶማሊያ ቀጥላ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸዉ የተፈናቀሉት ኢትዮጵያ ተቀምጣለች። ራሽንግ በኢትዮጵያ ለዚህ መንሴ ነዉ ያሉትን እንዲህ ያብራራሉ፣ «በሀገር ዉስጥ ለተፈናቀሉ ሰዎች መንስኤ የሚሆኑትን ሁኔታዎች ለያይቶ ማየት ይከብዳል። ለምሳሌ በኢትዮጵያ የምናየዉ ድርቅን ተከትሎ የመጣ ጎርፍ የብዙ ሰዎችን የኑሮ ዘይቤ በመረበሹ ምክንያት የምግብ እጥረት እንዲጨምር አድርጓል። ለምሳሌ 150,000 ሰዎች ከድርቅ ጋር ተያይዞ በመጣ የምግብ እጥረት ቄያቸውን ጥሎ ተሰደዋል። ድርቅ በመከሰቱም ግጦሽና ዉኃን ያማከለ ዉድድር ፈጥሯል። በዚህም ምክንያት 250,000 የሶማሊ አርብቶ አደሮች ቀዬቸዉን ጥሎ ተሰደዋል።»

ከአፍሪቃ ኅብረትና ከኖርዌይ የስደተኞች ምክር ቤት ጋር በመተባበር ይህ ዘገባ እንደተዘጋጀ የስልት አማካሪዋ ራሽንግ  ገልጸዉ፤ በጥናቱ ለኢትዮጵያ መንግሥትና ለረጅ ድርጅቶች ያስተላለፈዉን መልዕክት እንደሚከተለዉ አብራርተዋል፣ «እኛ በዘገባዉ ያስተላለፍነዉ መልዕክት ሁሉም የመንግሥት አጋሮች አሁን ያለዉን የሀገር ዉስጥ የተፈናቀሉ ሰዎችን ቀዉስ መፍታት እንዳለባቸዉ ነዉ። የቀዉሱን መነሻና የሚያመጣዉን ጉዳት በጥልቀት የመረዳት አቅማችንን ማሻሻል አለብን። በዚህ ጉዳይ ላይ አጠቃላይ ገፅታ ሊሰጠን የሚችለዉንና ለዉሳኔዎች ሊረዱን የሚችሉ በቂ መረጃ ማግኘት እንዳለብንም በመልዕክታችን ጠቅሰናል። በተለይም በዚህ በድርቁ የተጎዱት አካባቢዎችን ቶሎ የማዳን ሥራዎች የግድ መሥራት አለብን። ካልሆነ ግን ድርቅና በአካባቢ የአየር ለዉጥ የሚመጡ ቀዉሶች ሊያባብሱት ይችላሉ። ይህ ደግሞ ያሉት ተቋማትን አድክሞ የተፈጥሮ መመናመንን ያስከትላል።»

በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የሚመለከታቸዉን ለማነጋገር ያደርግነዉ ሙከራ አልተሳካም። ይሁን እንጅ የኢትዮጵያ መንግሥት የተጠቀሰዉን ቁጥር አለመቀበሉን በአገር ዉስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በአህጉር አቀፍ ደረጃ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2015 ብቻ 3,5 ሚልዮን በሀገር ዉስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች እንዳሉ ራሽንግ ተናግረዉ ይህ ማለት በየቀኑ 9500 ሰዎች አካባቢያቸዉን ጥለዉ ይሰደዳሉ ማለት እንደሆነ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል። የ2016ቱም ከዚህ የተሻለ አይደለም ነዉ ያሉት።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ  ለገሠ