1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

በኢትዮጵያ ቴሌግራም አፕልኬሽን ተወዳጅ ሆኗል  

ረቡዕ፣ የካቲት 21 2010

በቅርቡ ይፋ የተደረገ አንድ የዳሰሳ ጥናት ዋትስ አፕ የተሰኘው የመልዕክት መላላኪያ አፕልኬሽን በአብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ተወዳጅ እና በርካታ ተጠቃሚ ያለው መሆኑን አመላክቷል፡፡ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተለየ ግን በኢትዮጵያ ይበልጥ ተጠቃሚዎችን እያፈራ የመጣው ቴሌግራም የተሰኘው አፕልኬሽን መሆኑን ጥናቱ ጠቁሟል፡፡

https://p.dw.com/p/2tU4O
Telegram messenger
ምስል picture-alliance/dpa/Sputnik/N. Seliverstova

በኢትዮጵያ ቴሌግራም አፕልኬሽን ተወዳጅ ሆኗል  

የ21 ዓመቱ ኢብራሒም አህመድ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ውስጥ ባለችው አቀስታ ከተማ ነዋሪ ነው፡፡ የኮሌጅ ትምህርቱን ጨርሶ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ የሚገኘው ኢብራሂም ለወቅታዊ መረጃዎች ቅርብ ነው፡፡ የሀገር ውስጥም ሆነ የባህር ማዶ መረጃዎችን ማግኘት ሲፈልግ በዋናነት የሚገለገለው ተንቀሳቃሽ  ስልኩን ነው፡፡ ስልኩን ከኢንተርኔት ጋር አገናኝቶ ከእግር ኳስ እስከ መዝናኛ፣ ከዕለታዊ ዜና እስከ ቪዲዮዎች ያስሳል፡፡  

በኢትዮጵያ ያለው የኢንተርኔት ፍጥነት እንኳን እንደ አቀስታ ባለች ትንሽ ከተማ ይቅርና በመዲናይቱ አዲስ አበባም ዘገምተኛ ነውና ኢብራሂምም ለዚህ መፍትሄ አማራጭ ማፈላለጉ አልቀረም፡፡ የዛሬ ዓመት ግድም እንደተለመደው የኢንተርኔቱን ዓለም ሲያስስ ከአዳዲስ አፕልኬሽኖችን ጋር ይገጣጠማል፡፡ 

App Telegram
ምስል picture-alliance/AP Photo

“ስልኬን አንዳንዴ እጎረጉር ነበርና [የጉግል] ፕሌይ ስቶር አፕልኬሽን ላይ ኢንስታግራም፣ ቴሌግራም ምናምን አገኘሁ፡፡ ኢንስታግራም ስልክን በጣም ቢዚ ያደርጋል ሲቀጥል ደግሞ በጣም ተጠቃሚም የለውም፡፡ ግን ቴሌግራም የኢትዮጵያ ገጾች ስታገኝ በዚያ ላይ ደግሞ ሴቭ የምታደርጋቸው የስልክ [ቁጥሮች በዝርዝር] ሲመጡልህ ቴሌግራምን የተሻለ አድርገህ ትጠቀማለህ፡፡ እንዲያውም ዝቅተኛ ኔትወርክ ያንቀሳቅሰዋል፡፡ ለምሳሌ ስልክህ ላይ ኔትወርክህን የሚያሳዩ እስከ አምስት ቁጥር ድረስ ይደረደራሉ፡፡ ሁለት፣ ሶስት ሆኖ ይሰራል፡፡ ሲቀጥል ደግሞ የስልክ ግንኙነትህ 3G እና 2G ሆኖ እና E ሆኖም ይሰራል” ይላል ኢብራሒም፡፡

ኢብራሒም በዓለም ላይ ወደ 200 ሚሊዮን ገደማ ተጠቃሚ ያለውን የቴሌግራም አፕልኬሽን በስልኩ ላይ ከጫነ በኋላ ለሁለት ወር ያህል ሳይጠቀምበት ቆይቷል፡፡ ከቴሌግራም ጋር ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡት ዋትስአፕ እና ኢሞ በስልኩ ላይ ስለነበሩ ቀድሞ የሚያውቃቸውን አነርሱኑ መጠቀም ቀጥሎ ነበር፡፡ ቴሌግራም ተጠቃሚ ወዳጆቹ የሚነግሩትን ከሰማ በኋላ ግን አፕልኬሽኑን መሞከር ያዘ፡፡ ከዚያ በኋላ ደንበኝነቱን አጸና፡፡ 

“ዘመዶችን ለመጠየቅ ኢሞ እና ዋትስ አፕ እጠቀማለሁ፡፡ አዳዲስ ነገሮች ለማግኘት ደግሞ ቴሌግራምን እጠቀማለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ ድምጾችን አጋራበታለሁ፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ የተለቀቁ ቪዲዮዎችን እና እንዲሁም ደግሞ በድምጽ የወረዱ ነገሮች ማገናኛቸው (ሊንካቸው) ስለሚላክ አብሮ ሊንካቸውን አውርድበታለሁ” ይላል ኢብራሒም፡፡

እንደ ኢብራሂም ሁሉ በኢትዮጵያ ያሉ ተጠቃሚዎች በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ካሉ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር ለመገናኘት ከአንድም፣ ሁለት፣ ሶስት የመልዕክት መላላኪያ አፕልኬሽኖችን በስልኮቻቸው ይጭናሉ፡፡ አንዱ ለግንኙነት ሲያስችግር በሌላው ይሞከራሉ፡፡ ባለፉት ጥቂት  ዓመታት በብዙ ኢትዮጵያውያን አፍ ስማቸው ተደጋግሞ የሚነሳው ቫይበር እና ዋትስ አፕ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እንደ ኢሞ፣ ቴሌግራም እና ፌስ ቡክ ሜሰንጀር አፕልኬሽኖች በርካታ ተጠቃሚዎች እያገኙ መጥተዋል፡፡

የቴሌግራም አፕልኬሽን ከሌሎቹ በላቀ በአጭር ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያውያን ተጠቃሚዎች ዘንድ ተመራጭ እየሆነ መምጣቱ ግን የዘርፉን ጥናት አድራጊዎች ቀልብ ስቧል፡፡ ከጉግል ፕሌይ ስቶር ላይ በተሰበሰበ መረጃ ላይ ተመስርቶ ባለፈው ወር ይፋ የተደረገ አንድ የዳሰሳ ጥናት እንዳመለከተው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ብቸኛዋ በርካታ የቴሌግራም ተጠቃሚዎች ያሉባት ሀገር ሆናለች፡፡ በአፍሪካ ዋትስ አፕን በጥቂቱም ቢሆን የሚገዳደረው ፌስ ቡክ ሜሰንጀር እንኳ ተወዳጅነቱ በሰሜን አፍሪካ ሀገራት፣ በኤርትራ እና በሶማሊያ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ነው፡፡ 

Telegram Messenger
ምስል Imago/TASS/K. Kuhkmar

ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከእነ ኢራን እና ኡዜቤክስታን ተርታ ያሰለፋት የቴሌግራም ተወዳጅነት ምስጢር በሀገሪቱ ካለው የኢንተርኔት አገልግሎት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተጠቃሚዎችም ሆነ ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡ ከሌሎቹ የመልዕክት መላላኪያዎች ይልቅ ቴሌግራምን የሚያዘወትረው የ28 ዓመቱ ነቢያት ኃይሌም ለኢትዮጵያ ዘገምተኛ የኢንተርኔት ፍጥነት የተመቸ መሆኑን በዋና ምክንያትነት ይጠቅሳል፡፡ 

“እኔ ዋትስ አፕም ቫይበርም አለኝ ነገር ግን ቴሌግራም ያለው ጠቀሜታ ፍጥነቱ እና በተለይ ደግሞ ሚዲያ ፋይሎችን፣ የምስል እና የድምጽ መረጃዎችን ስትላላክ ከኢንተርኔት ግኝኙቱ አንጻር በደንብ ትላላካለህ፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ አሁን ያለሁት ክፍለ ሀገር ነው፤ ግንባታ የሚካሄድበት ቦታ ላይ ነው የምሰራው፡፡ ፎቶዎችን ወደ ዋናው ቢሮ ቶሎ ለመላክ፣ አንዳንድ የቪዲዮ ፋይሎችን ሪፖርት ለማድረግ  እጠቀመበታለሁ፡፡ አዲስ አበባ ሆነህ ቴሌግራም ሆነ ሌሎቹን [አፕልኬሽኖች] ብትጠቀም አይገርምህም ግን ክፍለ ሀገር ሆነህ ቴሌግራም መጠቀምህ አነስተኛ በሆነ የኢንተርኔት ግንኙነት መረጃዎችን መላላክህ ጠቃሚ ነው የሚሆነው፡፡ ቴሌግራም ለእኔ ተመራጭ የሆነበት ምክንያት እርሱ ነው” ይላል ነቢያት፡፡

ካለፈው ሐምሌ ጀምሮ ለስራ ወደ ኮምቦልቻ የሚመላለሰው ነቢያት የቴሌግራም ጥቅም ከአዲስ አበባ ይልቅ ጎልቶ የታየው በከፍለ ሀገር ቆይታው ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሲቪል ኢንጂነሪንግ የማስተርስ ትምህርቱን እየተከታተለ ያለው ተመስገን አብይ ግን  በመዲናይቱ ላለው የኢንተርኔት ፍጥነት ቢሆን ቴሌግራም ፍቱን መድኃኒት ነው ያላል፡፡ 

“እኔ አሁን ተማሪ ነኝ፡፡  ቫይበርም ሆነ ዋትስ አፕ አማራጭ ነበረን፡፡ ከፍጥነቱ አንጻር የትምህርት ክፍላችንን ቡድን ያደረግነው በቴሌግራም ነው፡፡ ፋይሎችን ቶሎ የመላክ አቅም አለው፡፡ በቫይበር የሆነ ሰው አንድ ፎቶ ቢልክልኝ እርሱ እስኪጭን በጣም ነው የሚቆይብኝ፡፡ ስለዚህ አልመርጠውም፡፡ እንዳልኩህ ተማሪ ነኝ፡፡  ፋይሎችን፣ ፈተናዎች ወይም የትምህርት ነገሮች መላላክ ስላለ የዚያን ጊዜ ራሱ የምመርጠው ቴሌግራምን ነው፡፡ ስለዚህ በቀላሉ ፋይሉን ይልክኛል ማለት ነው፡፡ ማንኛውንም ዓይነት መረጃ በቀላሉ ይልካል፤ አንተም ስትቀበል እንደዚያው ማለት ነው፡፡ ሌሎቹ ግን ትንሽ የአሰራራቸው ሊሆን ይችላል ስትቀበልም ሆነ ስትልክ ያስቸግራል” ሲል ያነጻጽራል።   

Telegram Messenger
ምስል picture-alliance/dpa/TASS/S. Konkov

በኢትዮጵያ እንደ ዋትስ አፕ አይነቶቹ የመልዕክት መላላኪያዎች ተነጥለው አገልግሎት እንዳይሰጡ ሲደረጉ እንደሚስተዋል የሚናገሩት ተጠቃሚዎች በእነዚያ ወቅቶች ቴሌግራም ተተኪ ሆኖ እንዳገለገላቸው ይመሰክራሉ። አሁን ከአዲስ አበባ ውጭ በተለያዩ ቦታዎች እንደሚስተዋለው የተንቀሳቃሽ ስልክ የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ሲቋረጥም አገልግሎቱ ምን ያህል እንዳጎደላቸው መረዳታቸውን ይገልጻሉ። አልፎ አልፎም ቢሆን የገመድ አልባ የኢንተርኔት ግንኙነት ወዳለባቸው ቦታዎች በመሄድ በቴሌግራም አማካኝነት የመረጃ ጥማቸውን ለመቁረጥ እንደሚሞክሩ ያስረዳሉ።   

የ26 ዓመቱ ተመስገን ቴሌግራም ከፍጥነቱ እና ያለ ገደብ ከመገኘቱ ሌላ ለእንደእርሱ ዓይነት ወጣቶች የተመቹ ይዘቶች አሉት ባይ ነው፡፡ ምሳሌዎቹን እንደሚከተለው ይዘረዝራቸዋል፡፡ 

“አሁን ለምሳሌ ብዙ ሰው በቴሌግራም ገጽ ከፍቷል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አማርኛን የሚጠቀሙ መገናኛ ብዙሃን አሉበት፡፡ የታወቁ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ ናቸው፡፡ ብዙ ተከታታይ አሏቸው፡፡ የአንዳንዶቹ እስከ 15 ሺህ እስከ 20 ሺህ ናቸው፡፡ እነዚያን ቡድኖች ከተቀላቀልክ ቡድኑን ለሰው መላክ ትችላለህ እና እነዚያ ቡድኖች ውስጥ ሰው በቀላሉ መግባት ይችላል፡፡ ለምሳሌ የሀገርኛ ቀልዶች ያሉባቸው አስቂኝ ገጾች አሉ፡፡ አንዳንድ ደግሞ ዲሽ ሰሪዎች አሉ፡፡ እነርሱ የራሳቸውን ቻናል ይከፍታሉ እና ዲሽ ማስገባት ከፈለግህ ከእነርሱ ጋር መነጋገር ትችላለህ፡፡ ሌላ ደግሞ ተጨማሪ ሽያጮች አሉ፡፡ አሁን ዕቃዎችን መግዛት ብትፈልግ ራሱ ቴሌግራም ላይ ገጾች አሉ፡፡ ከእነዚያ ጋር ቁጥጥር ተለዋውጠህ በየጊዜው የምትፈልጋቸው ጫማ፣ ልብሶች፣ ስልኮችንም ይለቃሉ፡፡ ስለዚህ በቀላሉ የገጹን ባለቤቶች ስትጠይቃቸው ቁጥራቸውን ይነግሩሃል፤ በዚያ መሰረት ተደዋውለህ መግዛት ትችላለህ፡፡ በፍጥነት ስለሚገባ በቀላሉ ብዙ ነገር ማግኘት ትችላለህ” ሲል ተመስገን በቴሌግራም የሚገኙ አገልግሎቶቹን ያስረዳል፡፡ 

ቴሌግራምን ተወዳጅ ካደረጉት ነገሮች አንዱ ሀገርኛ ይዘቶች ማካተቱ መሆኑን ነቢያትም ይስማማል፡፡ ተጠቃሚው በራሱ እንደ ስቲከር ዓይነቶቹን የስሜት መግለጫ ምስሎች እንዲፈጥር ዕድል መስጠቱንም በተጨማሪነት ያነሳል፡፡ “ስቲከሮች አሉ አይደል? ሀገራዊ የሆኑ፣ የሚያስቁ ስቲከሮች ሰዎች ይለጥፋሉ፡፡ በፈለግኸው መልኩ ደግሞ ታሻሽለዋለህ” ይላል።  የአሌክትሪካል ኢንጂነር ባለሙያው ፍሬው ግርማ ቴሌግራም ይበልጥ ተወዳጅ የሆነው በሃያዎቹ ውስጥ ባሉ ወጣቶች ዘንድ እንደሆነ አስተውሏል፡፡ ለምን በወጣቶች ዘንድ ተወዳጅ እንደሆነ ምክንያቶቹን ያብራራል፡፡

Telegram Messenger
ምስል picture-alliance/dpa/TASS/S. Konkov

“ቴሌግራም በቻናል በቻናል ነው። ከእኛ ማህበረሰብ ጋር የሚስማሙ፣ የራሳችን የሆኑ፣ በራሳችን የተፈጠሩ ቻናሎቹ አሉ። ያ ነገር ይበልጥ ተወዳጅ ያደረገው ይመስለኛል። ለምሳሌ ወጣቶች የሚፈልጉት ሃያዎቹ ውስጥ እና ሃያዎቹ መጀመሪያ ላይ ያሉ ወጣቶች አንደኛ በነጻ መገናኘት ይችላሉ፣ ቻት ያደርጉበታል በጣም፣ ሁለተኛ ነገር ደግሞ የራሳቸውን ቻናል እየከፈቱ የራሳቸውን ፍላጎት ማራመድ ይችላሉ። ወጣቶች የተሰራላቸውን ብቻ መጠቀም አይደለም። የፈጠራ ችሎታቸውን መጠቀም ይፈልጋሉ። የራሳቸውን መጠቀም የሚያስችላቸውን ሲያገኙ በዚያ ላይ ይበልጥ ፍላጎታቸው ያድራል። ለዚህ ደግሞ ኢንስታግራም እንደልብ መጠቀም ያስችላል። ወጣቱ የፈጠራ ችሎታውን መጠቀም ስለሚፈልግ ተከታታዮቹን እያሰፋ የተሻለ ማህበራዊ ተጽዕኖ ማምጣት ይችላል። ይሄ ትልቁ ነገር ነው” ይላል ፍሬው።    

በኢትዮጵያ ያሉ የቴሌግራም ተጠቃሚዎች ከዜና እስከ ሙዚቃ፣ ከቪዲዮ እስከ ፎቶ፣ ከቻት እስከ  ውይይት መድረክነት አፕልኬሽኑን እየተገለገሉበት እንዳሉ የተመለከቱ ባለሙያዎች “ራሱን የቻለ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ሆኗል” ይላሉ።  

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ