1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢሬቻ በዓል በርካቶች ሞቱ

እሑድ፣ መስከረም 22 2009

ደብረዘይት ውስጥ ዓመታዊው የኢሬቻ በዓል ዛሬ ወደ ጸረ-መንግሥት ተቃውሞ ተቀይሮ ፖሊስ በተኮሰው አስለቃሽ ጢስ እና ጥይት እንዲሁም ከዚህ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ግርግር በርካቶች ተረጋግጠው መሞታቸውን የተለያዩ የዜና ምንጮች ዘገቡ።

https://p.dw.com/p/2Qoly
Äthiopien Anti-Regierungs-Protesten
ምስል REUTERS/T. Negeri

ተቃውሞና ግድያ በኢሬቻ

ደብረዘይት ውስጥ ዓመታዊው የኢሬቻ በዓል ዛሬ ወደ ጸረ-መንግሥት ተቃውሞ ተቀይሮ ፖሊስ በተኮሰው አስለቃሽ ጢስ እና ጥይት እንዲሁም ከዚህ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ግርግር በርካቶች ተረጋግጠው መሞታቸውን የተለያዩ የዜና ምንጮች ዘገቡ። ሮይተርስ የዜና ምንጭ የተቃዋሚ ፓርቲን ጠቅሶ ቢያንስ 50 ሰው መሞቱን ዘግቧል። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ቁጥር ሳይጠቅስ በርካቶች መገደላቸውን አትቷል። እንደ ማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች፣ ተቃዋሚዎች እና የመብት ተሟጋቾች ከሆነ ደግሞ የሟቾቹ ቁጥር እስከ 300 ይደርሳል። በቦታው ላይ የነበረው ዘጋቢያችን የላከልን ምስል በርካታ ታዳሚዎች ለተቃውሞ እጆቻቸውን ከፍ አድርገው አግድም እንዳነባበሩ ያሳያል።

Äthiopien Tote bei Anti-Regierungs-Protesten in Bishoftu
ምስል DW/Y. Gegziabher

ሕዝቡ ወደ ሆራ ሐይቅ ሲያመራ ከአንድ ሰአት በላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ያሰማ እንደነበረም ዘጋቢያች አክሎ ገልጧል። ለመንግሥት ቅርበት ያላቸው የመገናኛ አውታሮች «በተፈጠረ መረጋገጥ እና መገፋፋት ምክንያት የ52 ሰዎች ሕይወት አልፏል» ሲሉ ዘግበዋል።

አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ምንጭ በበዓሉ ላይ ወደ ሁለት ሚሊዮን ታዳሚዎች እንደነበሩ ገልጧል።

መንግሥት በበኩሉ ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጦ ለሞቱ መንስዔ ግን «ችግር ለመፍጠር ተዘጋጅተው የነበሩ» ያላቸውን ሰዎች ተጠያቂ ማድረጉን የዜና ምንጩ አክሎ ጠቅሷል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ/ ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

ልደት አበበ