1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአዲስ አበባ ሰልፍ የቦምብ ጥቃት ሰዎች ሞቱ 115 ቆሰሉ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 16 2010

ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ የሞቱ እና የቆሰሉ ሰዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፤ ጥቃቱ "በተጠና" እና "በታቀደ" መልኩ የተፈጸመነው ብለዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር 115 ሰዎች መቁሰላቸውን አረጋግጠዋል። የአይን እማኞች ሶስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/307zZ
Äthiopien Kundgebung Premierminister Abiy Ahmed in Addis Ababa | Explosion
ምስል Oromo Media Network

በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ በመስቀል አደባባይ በነበረው የድጋፍ ሰልፍ በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት ሰዎች መሞታቸውን እና መቁሰላቸውን ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ምኒስትሩ ጥቃቱ ከተፈጸመ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ ቀርበው በሰጡት መግለጫ ጥቃቱ "በተጠና" እና "በታቀደ" መልኩ የተፈጸመነው ብለዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ የጥቃቱ ፈፃሚዎች "ሙያን ታግዘው ይኸን ደማቅ ሥነ-ሥርዓት ለማደፍረስ ለማበላሸት የሰው ሕይወት ለመቅጠፍ፤ ደም ለማፍሰስ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል" ሲሉ አክለዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር 115 ሰዎች መቁሰላቸውን አረጋግጠዋል

Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed in Addis Ababa | Demonstration mit Anhängern
ምስል Reuters

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አርማ ያለበትና በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የተሰራጨ ምስል እንዳሳየው ከሆነ ጠቅላይ ምኒስትር አብይ ንግግራቸውን አጠናቀው በተቀመጡበት የፍንዳታ ድምፅ ሲሰማ ጠባቂዎቻቸው አስነስተው ወስደዋቸዋል። የጠቅላይ ምኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ፍጹም አረጋ ከፍንዳታው በኋላ በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት "ልባቸው በጥላቻ የተሞላ የተወሰኑ የቦምብ ጥቃት ሞክረዋል" ብለዋል።

Äthiopien Demonstration Untersützung für Premierminister Abiy Ahmed in Addis Ababa
ምስል picture-alliance/Anadolu Agency/M. Wondimu Hailu

የአይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት የቦምብ ጥቃቱን ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሁለት ሴቶች እና አንድ ወንድ በአጠቃላይ 3 ሰዎች ተይዘዋል።ተጠርጣሪዎቹ  የተያዙት ለሰልፍ በወጣው ሰው ርብርብ መሆኑን በሥፍራው የነበሩ ተናግረዋል።  "ሶስት ናቸው አፈንጂዎቹ፤ ሁለቱ ሴቶች ናቸው አንዱ ወንድ ነው። የጎዳና ተዳዳሪ ይመስላሉ። እና እጃቸውም ላይ ቦምብ ተገኝቷል" ሲሉ ፍንዳታው በደረሰበት ወቅት በቦታው የነበሩ አንድ የአይን እማኝ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አንዷን አጓጉዟል የተባለ እና የፖሊስ መለያ ሰሌዳ የለጠፈ ተሽከርካሪ በድንጋይ የተደበደበ ሲሆን ቆየት ብሎ በእሳት ጋይቷል።

የዓይን እማኙ በፍንዳታው ከቆሰሉት በተጨማሪ አጥር ሲዘሉ የተጎዱ ሰዎችን መመልከታቸውን ገልጸዋል። "የቆሰሉ በርካቶች አይቻለሁ። ወደ ሰባት ሰዎች በስትሬቸር ሲሔድ አይቻለሁ። እዚያው መድረኩ አካባቢ የፈሰሰ ደም አይቻለሁ" ብለዋል። ቁስለኞችን ወደ ሆስፒታል የሚወስዱ አምቡላንሶች እስከ ቀኑ አምስት ሰዓት ይታዩ እንደነበርም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በቴሌቭዥን መግለጫቸው ጉዳዩ በፖሊስ እየተመረመረ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን የዓይን እማኞች ከፖሊስ ጋር እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የዛሬው የድጋፍ ሰልፍ በደሴ፣ ደብረ ማርቆስ እና ጎንደር ከተሞችም ተካሒዷል። በአዲስ አበባው ሰልፍ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ምኒስትሩ "ገና ኃላፊነት ከተረከብን መንፈቅ ሳይሞላን ፊት ለፊታችን እንደተራራ የተቆለለውን ግርዶሽ ሳንገፍ ፊት ለፊታችሁ ቆመን ምሥጋናን ለመቀበል የሚያስችል አቅም አላደረጀንም" ብለው ነበር።

እሸቴ በቀለ

ተስፋለም ወልደየስ