1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በታንዛንያ ስጋት ያጋጠመው ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 13 2010

በፕሬዚደንት ጆን ጉፉሊ የምትመራ ታንዛንያ በኢንተርኔት የሚወጡ ጽሁፎች ሊከተሉት ይገባል በሚል የወጣ አንድ አወዛጋቢ ረቂቅ ደንብ አጸደቀች። የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚገምቱት፣ ይህ ሕዝቡ ሀሳቡን የሚገልጽባቸው ሌሎች ኅቡዕ መንገዶችን እንዲያፈላልግ ያደርገዋል።

https://p.dw.com/p/2wPoY
Tanzania We need freedom of press
ምስል DW/A. Juma

አወዛጋቢው የኤሌክትሮኒክ እና የፖስታ ግንኙነት መመሪያ 2018

በታንዛንያ ኮሚዩኒኬሽን ደንብ አውጪ ባለስልጣን የተረቀቀው የኤሌክትሮኒክ እና የፖስታ ግንኙነት መመሪያ 2018  የሚል  ስያሜ የተሰጠው ደንብ ባለፈው መጋቢት አጋማሽ ነበር የጸደቀው። በአዲሱ መመሪያ መሰረት፣ ታንዛንያውያን የአምደ መረብ ጸሀፍት እና የኦንላይን ራድዮ እና ቴሌቪዥን አገልግሎት የሚሰጡ ታንዛንያውያን  በኢንተርኔት ማንናውንም ጽሑፍ ከማውጣታቸው በፊት ፈቃድ ለማግኘት ማመልከቻ ማስገባት እና በዓመትም $900 መክፈል ይጠበቅባቸዋል። አዲሱ መመሪያ የኢንተርኔት መድረኮች እና የማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ተጠቃሚዎችንም ይነካል። መንግሥት አንድ ድረ ገጽ  የማይመቸው  ወይም የሕዝብ ዓመፅ ሊቀሰቅስ ይችላል የሚል ጽሑፍ ካወጣ ፈቃድ ሊከለክለው ይችላል፣  ጽሑፉን ያወጣውን አምደ መረበኛም እስከ 2,200 ዶላር ሊቀጣ ይችላል።   ተቺዎች ይህ ክፍያ ለብዙ ታንዛንያውያን እጅግ ብዙ መሆኑን ገልጸዋል። የፖለቲካ ተንታኙ ጀነራሊ ኡሊምዌንጉ እንደሚሉትም፣ ፕሬዚደንት ጆን ማጉፉሊ ተቃውሞን ለማፈን የወሰዱት ሌላ ርምጃ ተደርጎ ነው የታየው።«  በዚች ሀገር ውስጥ ሀሳብን በነፃ የመግለጽ ሁኔታ ቀስ በቀስ እየተዘጋ፣ እየጠበበ እና አሳሳቢ በሆነ ደረጃም  እየተወሰነ ነው ለማለት እንችላለን። »
የሀገሪቱ መንግሥት የፕሬስ እና ሀሳብን የመግለጽ ነፃነትን ለማፈን በቀጣይ ምን ሊያደርግ ይችላል በሚል በብዙዎች ዘንድ ስጋት መኖሩን ነው ያስታወቁት ተንታኙ። አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች ባለፉት ጊዚያት ለብዙ ጊዜ ተዘግተው ቆይተዋል። በ2017 ዓም  ብቻ  ስዋሂሊ ደይሊ ታንዛንያ ዳይማን የመሰሉ ዕለታዊ ጋዜጦች ተዘግተዋል። ብዙ ጋዜጠኞችም ታስረዋል ወይም ጠፍተዋል።   ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተው ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ አዲሱን መመሪያ አውግዟል። በ2015 ስልጣን የያዙት  ፕሬዚደንት ማጉፉሊ የፕሬስ ነፃነትን የሚያረጋግጡ ሕጎችን ለማጥበብ ጠንከር የወሰዷቸው ርምጃዎች እንዳሳሰበው የድርጅቱ የአፍሪቃ ክፍል ኃላፊ አርኖ ፍሮዤ ገልጸዋል።  በፖለቲካ ተንታኙ ኡሊምዌንጉ አስተያየት፣ ሰዎች ሀሳባቸውን ለመግለጽ ሕጋዊው መንገድ ከተዘጋባቸው ሌሎች አማራጮች መፈለጋቸው አይቀርም ይህ ደግሞ ጎጂ ሊሆን ይችላል። 
 ሰዎች ሀሳባቸውን ለመግለጽ ሕጋዊው መንገድ ከተዘጋባቸው ሌሎች አማራጮች መፈለጋቸው አይቀርም ይህ ደግሞ ጎጂ ሊሆን ይችላል። 
« ባለስልጣናት ሀሳባቸውን ለመግለጽ እና ቅሬታቸውን ለመግለጽ የሚፈልጉ ሰዎችን  በጣም በሚያፍኑበት ጊዜ፣  ኅቡዕ፣ ድብቅ እና ግልጽ ባልሆኑ ዘዴዎች የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ይሄዳል። »በተከተሉት ጥጥር አመራር  በታንዛንያውያን ዘንድ ዳምጠው የሚል ቅጽል ስም የተሰጣቸው ማጉፉሊ በሀገሪቱ ባነቃቁት ተሀድሶ በሙስና እና በብቃት አልባነት ሰበብ ብዙ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ከስራ አባረዋል። ለዚሁ ውሳኔአቸው ሞገስ ቢያገኙም፣ ሀሳብን በነፃ መግለጽን ካለፉት ጥቂት ጊዚያት ወዲህ እያፈኑ የመጡበት ፈላጭ ቆራጭ አሰራራቸው  ብዙ  ትችት አፈራርቆባቸዋል። የፖለቲካ ተንታኙ ኡሊምዌንጉ እንደሚሉት፣ ማጉፉሊ በፀረ ሙስና ትግላቸው ያተረፉትን ጥሩ ስም በፈ/ቆራጭ አመራራቸው በማበላሸታቸው በአሁኑ ጊዜ  ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው የሚደግፏቸው። በሳቸው አመራር ብዙ የታቃዋሚ ቡድኖች አባላት ታስረዋል፣ ሰዎች ፕሬዚደንቱን ሰድበዋል በሚልም  ይታሰራሉ ፣ በማይረባ ነገር እየተከሰሱም መጉላላት ይደርስባቸዋል።  ማጉፉሊ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትዕይንተ ሕዝብ እንዳያደርጉ እና ደጋፊዎቻቸውን እንዲያነቃቁ  ከልክለዋል። ባጠቃላይ፣ በኡሊምዌንጉ አስተያየት፣  ሕዝቡ መፈናፈኛ ያጣ ያህል ተሰምቶታል። ማጉፉሊ ይህን ጥጥር አመራር እንዲቀይሩ የመብት ተሟጋቾች ግፊት አሳርፈዋል፣ ዩኤስ አሜሪካ፣ የአውሮጳ ህብረት እና በታንዛንያ የሚገኙ የምዕራብ አውሮጳ ሀገራት ኤምባሲዎችም ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ የሚፈፀም የኃይል ተግባር እና የመብት ጥሰት እንዳሳሰባቸው ባለፈው ወር  አሳውቀው ነበር።

Tansania Medienfreiheit verbotene Zeitung Mawio
ምስል Zuberi Mussa
John Magufuli Präsident Tansania
ጆን ማጉፉሊምስል picture-alliance/AA/B. E. Gurun

አርያም ተክሌ/ዩኒስ ዋንጅሩ

እሸቴ በቀለ