1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በተገን ጠያቂዎች መኖሪያዎች ላይ የተባባሰው ጥቃት

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 21 2007

የጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው በሃገሪቱ በተገን ጠያቂዎች የመኖሪያ ህንፃዎች ላይ የሚጣሉ አደጋዎች መጠን እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው።የችግሩ መንስኤና ለመፍትሄው የሚደረጉ ጥረቶች የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው ።

https://p.dw.com/p/1G5XY
Symbolbild Deutschland Flüchtlinge kommen an
ምስል picture-alliance/dpa/D. Bockwoldt

በተገን ጠያቂዎች መኖሪያዎች ላይ የተባባሰው ጥቃት

ጀርመን ለስደት አዲስ የምትባል ሃገር አይደለችም።ጀርመናውያንም በተለያዩ ሃገራት ተሰደው የሚኖሩ ህዝቦች እንደመሆናቸው ስደትን አያውቁትም ማለት አይቻልም ። ሆኖም ለስደተኞችም ሆነ ለስደት አዲስ ባልሆነችው በጀርመን በውጭ ዜጎች ላይ በተለያዩ ጊዜያት ጥቃቶች ይፈፀማሉ ። ከቅርብ ወራት ወዲህ ጀርመን ውስጥ በተገን ጠያቂዎች የመኖሪያ ህንፃዎች ላይ ተከታታይ ቃጠሎዎች ደርሰዋል። የጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ባለፈው ሳምንት እንዳስታወቀው ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በተገን ጠያቂዎች ህንፃዎች ላይ 202 የተመዘገቡ ጥቃቶች ተፈፅመዋል ። ይህም በጎርጎሮሳውያኑ 2014 ዓመተ ምህረት ከተመዘገቡት ጥቃቶች በልጦ ነው የተገኘው ። በአጠቃላይ በዚሁ ዓመት የተመዘገበው ጥቃት መጠን 198 ነበር ። ጀርመን ውስጥ እነዚህን መሰል አደጋዎች ሲደርሱ ግን አዲስ አይደለም ። በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1990ዎቹ በተለይ በምሥራቅ ጀርመን በውጭ ዜጎች ላይ ተመሳሳይ ጥቃቶች ደርሰዋል ። ከዚያን ወዲህም በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚደርሱ እነዚህን የመሳሰሉ የዘረኞች ጥቃቶች ሰለባ የሆኑ የውጭ ዜጎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም ። ከቅርብ ወራት ወዲህ በተለይ ለተገን ጠያቂዎች መቀበያ በተዘጋጁ ቤቶች ላይ የሚፈፀሙት ጥቃቶች ተጠናክረው መቀጠል እዚህ ጀርመን ከሰሞኑ አነጋጋሪ ጉዳዮች አንዱ ነው ። በጀርመን ዘረኝነትን የሚታገለው ባብል ኤ ፋው የተባለው ድርጅት መሥራች እና ስራ አስኪያጅ ዶክተር መኮንን ሽፈራው ለዚህን መሰሉ ጥቃት መባባስ አንዱ ምክንያቱ ቀኝ አክራሪዎች ለህብረተሰቡ የሚነዙት የተሳሳቱ መረጃዎች ናቸው ይላሉ ። በጀርመን በተገን ጠያቂዎች የመኖሪያ ህንፃዎች ላይ በአሁኑ ጊዜ ጥቃቱ የተጠናከረበት ሌላው ምክንያት ካለፈው ዓመት ወዲህ ጀርመን የሚገቡት ተገን ጠያቂዎች ብዛት ከቀድሞው ከፍ እያለ መሄዱ ነው ።በዶክተር ሽፈራው አስተያየት ቀኝ አክራሪዎች ህብረተሰቡ ተገን ጠያቂዎች ጀርመን መግባታቸውን እንዲቃወም ልዩ ልዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ ።ጀርመን የምትቀበላቸው ተገን ጠያቂዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄድ እዚህ ሁሌም የሚያነጋግር ጉዳይ ነው ። የስደተኞች ቁጥር ባደገ መጠን እነርሱን ለማስተናገድ የሚወጣው ገንዘብም ማከራከሩ አልቆመም ። በጎርጎሮሳውያኑ 2015፣ 16ቱ የጀርመን ፌደራል ግዛቶች ለተገን ጠያቂዎች ጉዳይ የሚውል ተጨማሪ 5 ቢሊዮን ዩሮ ያወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ። ይህ ገንዘብም ሃገሪቱ በ2014 ለዚሁ ለተገን ጠያቂዎች ከመደበችው በጀት በእጥፍ የሚበልጥ ነው ። በዚህ ዓመት ጀርመን እንድትቀበላቸው ማመልከቻ ያስገቡ ተገን ጠያቂዎች ቁጥር ከ179 ሺህ ይበልጣል ። የአመልካቾቹ ቁጥር በዚሁ ዓመት ከ400 ሺህ በላይ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል ። ጀርመን ይህን ያህል መጠን ያላቸውን ተገን ጠያቂዎች መቀበሏን የሚቃወሙ ወገኖችና አንዳንድ ፖለቲከኞች ሃገሪቱ ጫናው በዝቶባታል ሲሉ ይከራከራሉ ። ዶክተር መኮንን ግን በዚህ አይስማሙም ።በጀርመን ተገን ጠያቂዎች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንቃኝ ባለፈው ዓመት የደረሱት አደጋዎች መጠን ከዚያ በቀደመው በጎርጎሮሳውያኑ 2013 ከተፈፀሙት በሶስት እጥፍ የሚበልጡ ሆነው እናገኛቸዋለን ። ከጥቃቶች አብዛኛዎቹ ጀርመን ለጀርመናውያን ብቻ የሚል አስተሳሰብ በሚያራምዱ ቀኝ አክራሪዎች ና ደጋፊዎቻቸው የሚፈፀሙ መሆናቸው ይታመናል ። ለምሳሌ ባለፉት ስድስት ወራት ከደረሱት አደጋዎች 85 በመቶው በቀኝ አክራሪዎች የተፈፀሙ መሆናቸው ተነግሯል ። አሁን አሁን ከነዚህ ወገኖች ጋር ግንኙነት የሌላቸው ጀርመናውያንም የቀኝ አክራሪዎቹን አመለካከት እንደያዙ ዶክተር መኮንን ያስረዳሉ ።ባለፈው ዓመት በጀርመን የቀኝ አክራሪዎች ጥቆቶች ተደጋግሞ ከደረሰባቸው አካባቢዎች በቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን ስር የነበሩት 4 የጀርመን ፌደራዊ ክፍላተ ሃገር ማለትም ብርንድንቡርግ ፣በርሊን ፣ቱሪንንገን እና ሜክለንቡርግ ፎርፖመርን በዋነኛነት ይጠቀሳሉ ። ሆኖም በንፅፅር የተሻለ ሲባል በቆየው በምዕራብ ጀርመንም በቀን አክራሪዎች የሚፈፀሙ ጥቃቶች እየተባባሱ መሆኑ ነው የተነገረው ። እንደገና ዶክተር መኮንን
ዶክተር መኮንን እንደሚሉት የጀርመን ፖለቲካው የተቀበለውን የተገን ጠያቂዎች ጉዳይ አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚቃወሙት ስለ ተገን ጠያቂዎች የሚደርሳቸው መረጃ የተዛባ በመሆኑ ነው ። በርሳቸው እምነት ይህን ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ብዙ ይቀረዋል ። እስከዚያው ግን ጀርመን የሚገኙ ተገን ጠያቂዎችም ሆኑ የውጭ ዜጎች ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል በጥንቃቄ እንዲንቀሳቀሱ ከዚሁ ጎንም ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው ለመኖር እንዲጥሩ ይመክራሉ ።

Symbolbild Rechtsextremismus
ምስል imago/Rüdiger Wölk
Mekonnen Shiferaw Geschäftsführer Babel e.V.
ዶክተር መኮንን ሽፈራውምስል DW/Y. Hinz

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ