1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቡሩንዲ ያልታጠቀ ፖሊስ እንዲሰማራ የተ.መ.ድ. ውሳኔ አሳለፈ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 24 2008

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ግድያ እና ማሰቃየት ተስፋፍቶባታል ባላት ቡሩንዲ ፖሊሶችን ለማሰማራት በሙሉ ድምጽ ውሳኔ አስተላለፈ።

https://p.dw.com/p/1IOXe
Symbolbild UN Mission Soldat
ምስል imago/blickwinkel

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ግድያ እና ማሰቃየት ተስፋፍቶባታል ባላት ቡሩንዲ ፖሊሶችን ለማሰማራት በሙሉ ድምጽ ውሳኔ አስተላለፈ። የውሳኔ ኃሳቡን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን የቡሩንዲን መንግሥት አማክረው እና የአፍሪቃ ሕብረትን አስተባብረው የፖሊስ ኃይሉ የሚሰማራበትን አማራጭ በአስራ አምስት ቀናት ውስጥ እንዲያቀርቡ ኃላፊነት ሰጥቷል። በቡሩንዲ የሚሰማራው የተ.መ.ድ. ፖሊስ የሀገሪቱን የጸጥታ ሁኔታ የሚከታተል፤ የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚያበረታታ እና የሕግ የበላይነት እንዲከበር የሚሠራ ነው መባሉን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። ፕሬዝዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ለሦስተኛ የስልጣን ዘመን ለምርጫ ለመወዳደር በመወሰናቸው ምክንያት በቡሩንዲ የተቀሰቀሰውን ኹከት እና አለመረጋጋት ለመቆጣጠር የአፍሪቃ ሕብረት ያቀረበው የሰላም አስከባሪ ወታደሮች የማሰማራት ሃሳብ ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱ አይዘነጋም። በተ.መ.ድ. የቡሩንዲ አምባሳደር አልበርት ሺንጊሮ መንግሥታቸው ስለ ተልዕኮው አይነት፤ ብዛት እና ስለሚኖረው ኃላፊነት ለመወያየት ፈቃደኛ መሆኑን መናገራቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። የተ.መ.ድ. የውሳኔ ኃሳብ በቡሩንዲ ይፈጸማሉ ያላቸውን ግድያ፤ ወሲባዊ ጥቃት፤ ማሰቃየት፤ በሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ላይ የሚፈጸም ማዋከብ እና የጋዜጠኞችን መሠረታዊ መብት ማፈንን አውግዟል።

Burundi Bujumbura Proteste gegen Präsident Pierre Nkurunziza
ምስል Heinrich-Böll-Stiftung/Igor Rugwiza

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ