1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቄለም ወለጋ ጥቃት የተፈጸመባቸው የአማራ ተወላጆች

ዓርብ፣ ሰኔ 15 2010

ዶቼቬለ ዛሬ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በምሬት እንዳሉት በዚህ ሳምንት ሰኞ በተነሳ ግጭት የሰዎች ህይወት ሲጠፋ የአካል ጉዳትም ደርሷል። ትናንትም  ረብሻ ተነስቶ ሰዎች ተጎድተዋል። ትናንት እና እና ዛሬ  ዝርፊያ ተፈጽሟል። 

https://p.dw.com/p/3073D
Karte Äthiopien Amhara, Tigray, Oromia Englisch

በኦሮምያ ክልል ፣ በቄለም ወለጋ ዞን፣ በሀዋ ገላን ወረዳ በመቻራ ከተማ ነዋሪ የሆኑ የአማራ ተወላጆች ለዓመታት ከኖርንባቸው መንደሮች «ውጡ እየተባልን እየተገደለን የአካል ጉዳት እየደረሰብን እየተዘረፍን እና እየተፈናቀለን ነው» ሲሉ ሮሮአቸውን በማሰማት ላይ ናቸው። ይህ ሁሉ በደል ሲፈጸምብንም የአካባቢው የፀጥታ ኃይላት እላስጣሉንም ሲሉ በምሬት ይናገራሉ። የአማራ ክልል ሁኔታውን እያጠናና በጉዳዩ ላይም ከኦሮምያ ክልል ባለሥልጣናት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ለዶቼቬለ አስታውቋል። የአማራ ተወላጆች በቄለም ወለጋ ዞን በሚገኙ መንደሮች የሰፈሩት ከዛሬ 33 ዓመት በፊት ነው። በዚያን ጊዜው ረሀብ ምክንያት ከወሎ ተነስተው መቻራ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ መንደሮች መኖር የጀመሩት እነዚህ ነዋሪዎች ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር ክፉውንም ደጉንም አብረው አሳልፈዋል። ይሁን እና ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ከነዚህ መንደሮች ውጡ እየተባሉ ልዩ ልዩ ጥቃቶች ሲፈጸሙባቸው መቆየታቸውን ይናገራሉ። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ችግሩ መባባሱን ነው ዶቼቬለ ዛሬ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በምሬት ያስረዱት ። ነዋሪዎቹ እንዳሉት በዚህ ሳምንት ሰኞ በተነሳ ግጭት የሰዎች ህይወት ሲጠፋ የአካል ጉዳትም ደርሷል። ትናንትም  ረብሻ ተነስቶ ሰዎች ተጎድተዋል። ትናንት እና እና ዛሬ በመንደር 10  ዝርፊያ ተፈጽሟል። 

«እኛ ላይ ብዙ ጉዳት ደርሷል። ሰውም የሞተ አለ። የቆሰለ አለ። ብዙ ችግር እየተፈጠረ ነው። ትናንትም 12 በሬ ወሰዱ።ደግሞ አሁንም ወሰዱ።የወረዳ ወታደሮች መጥተው ስብሰባ ሰብስበው እያሉ ነው ከስብሰባ ሳንበተን ከነርሱ ጋር እያለን ከብቶቹን ወሰዱ ማለት ነው።»የትናንቱ ግጭት የተካሄደበት የመንደር 10 ነዋሪ መሆናቸውን የተናገሩት እኚሁ አባወራ ግጭቱ እንዴት እንደተቀሰቀሰ አስረድተዋል።
«በደርግ ጊዜ የተመራነው እርሻ ላይ መጥተው እርሻ ጠመደው እርሻችን ነው አሉ። እኛ ደግሞ እርሻችን ነው ተዉት ስንል በቃ በዚህ መንስኤ መሬታችን ነው አገራችን ልቀቁ ሁሉንም አንፈልግም አማራ ልቀቁ አሉ።»

በግጭቱ ከባድ ጉዳት የደረሰበት የ23 ዓመት ገበሬ በአካባቢው መታከም እንዳልቻለም ነው አባወራው የገለጹት። ሌላው የአካባቢው ነዋሪ ደግሞ ከሦስት ቀናት በፊት በመንደር ሀያ በተነሳ ግጭት የሰዎች ህይወት ማለፉን የአካል ጉዳትም መድረሱን ገልጸዋል።
«ከ3 ቀናት በፊት እዚያ ሁለት ሰው ሞቷል። አንደኛው ወዲያው ሞቷል።አሊ አበጋዝ ይባላል።አንደኛው ደግሞ ሆስፒታል ደርሶ ነው ትናንትና የሞተው አንደኛውን የቀበርነው እሮብ ነው። መጀመሪያ የሞተውን በጦር ነው የወጉት ሁለተኛውንም እንደዚሁ በጦር ነው።ደክሟል ብሎ ነበር ህዝቡ አዋጥቶ የላከው አሁን ሞቷል የሚል መረጃ ነው የደረሰኝ ።»
የመንደር አስሩ ነዋሪም ይህንኑ አረጋግጠው የደረሰልን ግን የለም ነው የሚሉት።
«ቀበሌዎች ለፖሊስ ሲደውሉ አንሰራም አትደውሉ አሉ ቅርብ ነን 15 ደቂቃ ነው የሚርቀው። በቃአልመጣም አሁን እንደገና ከወረዳ አድማ በታኞች አብረው መጡ።እንደገና ህዝቡ ከሞተ ካለቀ በኋላ ማለት ነው። የወረዳው አድማ በታን ወታደሮች ትናንትናውኑ በ12 ሰዓት አካባቢ መጡ በቃ ችግሩን ነግረዋቸው ከበላይ አካል ይምጣና እንነጋገር ችግራችን ፍትህ የለውም አሁን እናንተ ብትመጡ አለን። ዛሬም እንዲሁ ነው ያልነው።»

እነዚህ በደሎች ደርሰውብናል የሚሉት የመንደር 10 ነዋሪ የአማራ ተወላጆች ትናንት በወቅቱ ለአካባቢው ፖሊስ ቢደወልም ዘግይቶ መምጣቱን ነው የተናገሩት። ዛሬ ጠዋት ግን አድማ በታኞች ያሏቸው አካላት ከወረዳ መጥተው አነጋግረዋቸዋል። ሆኖም ከነርሱ ጋር እየተነጋገሩ  ባሉበት ወቅት ከብቶቻቸውን የተዘረፉት እነዚሁ ነዋሪዎች ለህይወታቸውንም ሆነ ለንብረታቸው ዋስትና እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ።
«ዋስትና ይሰጠን መንግሥት አንድ ነገር ያድርገን ወይ ያንሳን ወይ ጥበቃ ያድርግልን ወታደር ይመደብልን ያው የኢትዮጵያ ወታደር ማለት ነው። ችግሩ ከመከሰቱ መጀመሪያ ከሁለቱም ወገን ሰው ሳይሞት የሚጠብቀን አካል ይቁም ነው በቃ።»
በቄለም ወለጋ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች  ችግሩ ተባብሶ ተጨማሪ የሰዎች ህይወት እንዳይጠፋ ከወዲሁ የመከላከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እና ዋስትና እንዲሰጣቸውም ይጠይቃሉ።
ዶቼቬለ ቄለም ወለጋ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ስለሚያሰሙት ሮሮ የአማራ ክልል የኮምኒኩሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁንን ክልሉ ምን እያደረገ እንደሆነ ጠይቋቸው ነበር። ችግሩን ለማስቆም ከኦሮምያ መንግሥት ጋር ከዚህ ቀደም የጀመረውን ሥራ መቀጠሉን ተናግረዋል።
«አሁን በቄለም ወለጋ በተጨባጭ ግጭቶች እንዳሉ መረጃ ደርሶኛል። በተጨባጭ ምን ያህል ጉዳት ደረሰ ፣የደረሰውን ጉዳት ለመቀነስ አካባቢው ላይ ምን እየተሰራ ነው?የሚለውን ከክልሉ መንግሥት ጋር ከእነ ዶክተር ነገሪ ጋር መረጃ እየተለዋወጥን ነው። የተጣራውን መረጃ እንደሚሰጡን፣ በየአካባቢው ያሉ ችግሮችን የመቅረፍ ሥራ ላይ እንደሆነ እና ይህንኑም ግጭት በተከሰተባቸው ቦታዎች የማረጋጋት እንቅስቃሴዎች ላይ እንደሆኑ ተነጋግረናል። በተጨባጭ እዚያው አካባቢ ያለውን መረጃ ከክልሉ መንግሥት ጋር በመተባበር የምናገኘው ነውና»

አዜብ ታደሰ