1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በርሊን፤ ማከራከር የቀጠለው የመንገዶች ስም ጉዳይ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 17 2010

በበርሊን ከብዙ ንትርክ በኋላ በአፍሪቃዊ ሰፈር በሚባለው አካባቢ የሚገኙ  ሶስት በጀርመናውያን ቅኝ ገዢዎች ስም የሚጠሩ መንገዶች ስም አሁን እንዲቀየር ባለፈው ሳምንት  ተወሰነ። ይህን ውሳኔ ያሳለፈው የአንድ የከተማይቱ ወረዳ ምክር ቤት ነው። ይሁንና፣ ውሳኔው አንዳንድ የአፍሪቃዊውን ሰፈር ነዋሪዎች አስቆጥቷል።

https://p.dw.com/p/2weJj
Berlin Kolonialgeschichte Afrika
ምስል Imago/Jürgen Ritter

« መንገዶች በቀድሞ ቅኝ ገዢዎች ስም ሊጠሩ አይገባም። » ጆሴፊን አፕራኩ

በበርሊን አፍሪቃዊው  ሰፈር የሚገኝበት ወረዳ ምክር ቤት አከራካሪ የሆኑ የመንገድ ስሞች እንዲቀየሩ ውሳኔ በሚያሳልፍበት ጊዜ  ሁሉ ፀረ ቅኝ አገዛዝ ቡድኖች በዚሁ አካባቢ  አደባባይ በመውጣት ድጋፋቸውን ያሳያሉ።
ምክር ቤቱ ሶስት የመንገድ ስሞች እንዲቀየር ውሳኔ ላይ የደረሰው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ፣ በምህፃሩ ኤስፔዴ፣ የአረንጓዴዎች እና የግራ ክንፍ ፓርቲዎች ያስገቡትን ማመልከቻ መነሻ በማድረግ ነው። ሶስቱ ፓርቲዎች በማመልከቻቸው አንዳንድ የመንገድ ስሞች አሁንም የጀርመን ቅን አገዛዝ ዘመንን እና በዚያን ጊዜ የተፈፀሙ ወንጀሎችን የሚያከብሩ በመሆናቸው የበርሊንን ገፅታ ለዘለቄታው ያበላሻል በሚል ያሰሙትን ቅሬታ ምክር ቤቱ ካጤነ በኋላ ነበር ቅን አገዛዝ ተወካዮች ሆነው በሚታዩ ጀርመናውያን ስም የሚጠሩን መንገዶች ስያሜ ለመቀየር የወሰነው።

Berlin Kolonialgeschichte Afrika
ምስል Imago/Klaus Martin Höfer

በውሳኔው መሰረት፣ የናማ ብሄረሰቦችን መሬት በወሰደው አዶልፍ ሉደሪትስ ስም የሚጠራውን መንገድ ሉደሪትስሽትራሰን በቀድሞው ፀረ የጀርመን ደቡባዊ አፍሪቃ ግዛት ታጋይ ኮርኔልዩስ ፍሬዴሪክስ ስም፣ ቶጎላንድ እና ካሜሩን የጀርመን ቅኝ ግዛት ለሆኑበት ድርጊት ዋና ሚና በተጫወተው ጉስታብ ናኽቲጋል ስም የሚጠራው ናኽቲጋልፕላትስ የተባለው አደባባይ ደግሞ በ1914 ዓም በተረሸኑት የካሜሩን ንጉሥ ሩዶልፍ ማግና ቤል ክብር ቤል አደባባይ ተብሎ ይጠራል። የጀርመን ምሥራቅ አፍሪቃ ቅን ግዛት ዋና አራማጅ ካርል ፔተርስ ስም የሚጠራው ፔተርስአሌም ለሁለት ተከፍሎ ግማሹ በቀድሞ የናሚቢያ ነፃነት ታጋይ አና ሙጉንዳ፣ ሌላው ግማሽ ደግሞ በቀድሚ ፀረ የጀርመን ምሥራቅ አፍሪቃ ንቅናቄ ማጂ ማጂ ተብሎ ተሰይሟል። ይህ የወረዳው ምክር ቤት ውሳኔ አስደሳች መሆኑን ለቅኝ አገዛዝ ተወካዮች ክብር እንዳይሰጥ የሚታገሉት ጆሴፊን አፕራኩ ገልጸዋል።
አንዳንድ የአፍሪቃ ሰፈር ነዋሪዎች የቅን አገዛዝ ወንጀሎችን የሚያስታውሱ መንገዶች መጥፋት እንዳለባቸው ሲናገሩ፣ ሌሎች ግን  የመንገድ ስም ከመቀየራቸው ይልቅ አስቀድመው በስም አሰጣጥ ወቅት ሊያስቡ ይገባ ነበር፣ ወይም የለመድነው ስም ለምን ይቀየራል ወይም አሁን እንዳዲስ አድራሻ፣ አለብን በማለት ለውጡ እንዳላስደሰታቸው ገልጸዋል። በአንፃራቸው የመፍቀሬ አፍሪቃዊ ሰፈር ተሟጋቾች  የመንገዶች ስም ቅየራን ይቃወማሉ። ይኸው የሀሳብ ልዩነት በሰፈሩ ነዋሪዎች ዘንድ መጥፎ ስሜት መፍጠሩን የመፍቀሬ አፍሪቃዊ ሰፈር ባልደረባ ካሪን ፊሉሽ አስታውቀው ውሳኔው ለነዋሪዎቹ ቢተው መልካም እንደሚሆን ገልጸዋል። ይህን አሰራር ተሟጋች ጆሴፊን አፕራኩ ግን  ማንኛውንም ዓይነት  ለቅኝ አገዛዝ ተወካዮች የሚደረግ ማንኛውንም ክብር ይቃወማሉ።
የበርሊን መሀል ወረዳ ምክር ቤት አሁን ያሳለፈው ውሳኔ አሁንም በበርሊን እና በሌሎች የጀርመን ከተሞች  ያሉ ለቅኝ አገዛዝ ተወካዮችን  ክብር የሰጡ የመንንገድ ስሞች እንዲለወጡ አርአያ እንደሚሆን ተስፋ አድርገዋል። የአፍሪቃ ሰፈር መንገዶች ስማቸውን እንደያዙ እንዲቀጥል የሚሟገተው ቡድን ባልደረባ ካሪን ፊሉሽ በፀረ ቅኝ አገዛዝ ተወካይ ካርል ፔተርስ ስም ይጠራ የነበረው  የፔተርስአሌ ከ1986 ዓም ወዲህ በናዚ ስርዓት አንፃር በታገሉት ሀንስ ፔተርስ ስም ስለሚጠራ አሁን ስሙን እንደገና ለመቀየር የተወሰደውን ውሳኔ ሕግን የጣሰ አድርገው ተመልክተውታል።  ስለዚህ በመንገዶች ስም ሰበብ የሚሰማው ንትርክ በቅርቡ የበርሊን ፍርድ ቤቶችንም ማነጋጋሩ የማይቀር ይሆናል። በናኽቲጋል አደባባይም  ሰላም እስሊወርድ ድረስም ብዙ ጊዜ መውሰዱ የማይቀር ነው።

Europäische Erinnerungskultur | Afrikanische Straßennamen in Berlin
ምስል picture-alliance/dpa/M. Skolimowska

 አርያም ተክሌ/ዳንየል ፔልስ

ነጋሽ መሀመድ