1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ«HIV» መከላከያ ክትባት

ሐሙስ፣ ኅዳር 22 2009

ደቡብ አፍሪቃ በዓለማችን በ«HIV» የተያዙ በርካታ ሰዎች የሚኖሩባት ሃገር ናት። በጥናት በተገኘ መረጃ መሠረት አሁንም በቀን ከ 1.000  ሰዎች በላይ በቫይረሱ ይያዛሉ። በአሁኑ ወቅት የፀረ HIV ተሐዋሲ መድኃኒት የሚጠቀሙ ሰዎች በመበራከታቸዉ የበሽታዉ ገዳይነት የቀነሰ ይመስላል። 

https://p.dw.com/p/2Tagq
Symbolbild Forschung und Wissenschaft
ምስል picture-alliance/dpa/K.J. Hildenbrand

Hoffnung für Generationen: HIV-Impfstoff wird in Südafrika getestet - MP3-Stereo


እንድያም ሆኖ   የ «HIV» ስርጭትን በክትባት መግታት ይቻላል ሲሉ የሕክምና ባለሞያዎች ያምናሉ። የዚህን ክትባት ስኬት ለመፈተሽም በአሁኑ ወቅት ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ ጥናት ተጀምሮአል። የHIV ቫይረስን በመድሐኒት ለመከላከል ይህ የመጀመርያ ጥረት ባይሆንም ፤ ሙከራዉ ከአሁኑ ብዙ ተስፋ የተጣለበት መሆኑ ተመልክቶአል።

በዓለማችን  እንደ ደቡብ አፍሪቃ በኤድስ ቫይረስ ስርጭት ክፉኛ የተጠቃ ሃገር የለም። አንዳንድ ምሑራን የቫይረሱ ስርጭት በሃገሪቱ ሰብዓዊ ፍጡርን እንዳያጠፋ ስጋት እንዳላቸዉ ይገልጻሉ። በደቡብ አፍሪቃ ኬፕታዉን ዩንቨርስቲ ዉስጥ የሚገኘዉን ጥናት የሚመሩት ሊንዳ ጋይል ቤከር እንደሚሉት ጉዳዩ አሳሳቢ እየሆነ ነዉ።   

« ከባድ ፈተና ነዉ። ቫይረሱን የሚገታ አንድ የክትባት መድሐኒት መፈለግ ማለት መንፈስ ቅዱስን እንደማግኘት ነዉ።  ቫይረሱን ጨርሶ በቁጥጥር ስር ማዋል አልያም ማጥፋት እንደማንችል እናዉቃለን። ሰዎች በቫይረሱ እንዳይያዙ የሚስችል ክትባትም የለንም። ግን ይህ ክትባትን ካገኘን፤ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ትልቅ አብዮት እንዳካሄድን ያህል ይሆን ነበር»

Symbolbild Forschung Labor Reagenzgläser Chemie
ምስል Fotolia/Tom

በደቡብ አፍሪቃ ይህን የኤድስ መከላከያ ክትባት  ፍቱንነት ለመፈተሽ የሚደረገው ሙከራ በስፋት እየተካሄደ ነው ። በሃገሪቱ ፕሪቶርያና ኬፕታዉን ከተሞችን ጨምሮ በ 15 ቦታዎች ላይ የክትባቱን ፍቱንነት ለማረጋገጥ ሙከራዉ እየተደረገ ነዉ። በአሁኑ ወቅት ሦስተኛ ደረጃ ላይ የደረሰዉ ሙከራ እስካሁን ከ 18 እስከ 35 ዓመት እድሜ ክልል ዉስጥ የሚገኙ 5,400 ሰዎች ለሙከራ ክትባቱን ተወግተዋል።  ሙከራዉን ከሚያደርጉት ከነዚህ ሰዎች መካከል ደግሞ ሁለት ሦስተኛዉ ሴቶች ናቸዉ።  ሴቶች በብዛት በሙከራዉ ላይ እንዲሳተፉ የተደረገበት ምክንያት ደግሞ በቫይረሱ በቀላሉ የሚጠቁት እነርሱ በመሆናቸዉ ነዉ።  ደቡብ አፍሪቃ ሙከራ እንዲካሄድባት የተመረጠችበት ምክንያትም ግልጽ ነዉ ያሉት ሊንዳ ጋይል ቤከር በመቀጠል፤

« ምክንያቱ ደቡብ አፍሪቃ ከልክ ባለፈ መጠን የቫይረሱ ስርጭት በመታየቱ ነዉ። እዚህ የምርምር ሂደቱን የምናካሂድበት መዋቅሩ ፤ ምሑራኑ እንዲሁም በሙከራዉ የሚሳተፉ ሰዎች አሉን። በሙከራዉም «HIV»ን ድል ስናደርግ ማየት  እንሻለን።»  

ይህ በሙከራ ላይ የሚገኘዉ «HIV»ን የሚከላከለዉ ክትባት መጠርያ « HVTN 702» ይሰኛል።  መድሐኒቱ ከሰባት ዓመት በፊት ታይላንድ ዉስጥ የተሰራና ለሙከራ የቀረበ ሲሆን በአለፉት ዓመታት ተሻሽሎ በመቅረቡ ቫይረሱን ለመቆጣጠር ያስችላል የሚል ተስፋን አጭሮአል።  በዩኤስ አሜሪካ የአለርጂ እና ቁስለት የሚያስከትሉ በሽታዎች ብሔራዊ ተቋም ሃላፊ አንቶኒ ፋዉስ «HIV»ን ለመከላከል የተጀመረዉን የክትባት ጥናት አስፈላጊ ነው ሲሉ ጥሩ ተስፋ እንዳለ ይገልጻሉ።  አንቶኒ ፋዉስ የ«HIV» ቫይረስን ለመከላከል የሚረዳዉን ክትባት ማግኘታችን  ፤ ዉጤቱ «HIV»ን  ወደ መቃብር ለመክተት የመጨረሻ እርምጃችን ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል ። «HIV»ን ለመከላከል ክትባት ሊገኝ ይችላል ብለዉ የዘርፉ ባለሞያ ምሁራን ሲናገሩ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ መሆኑ ነዉ። በደቡብ አፍሪቃ ኬፕታዉን ዩንቨርስቲ ዉስጥ የሚገኘዉን ጥናት የሚመሩት ሊንዳ ጋይል ቤከር ትልቅ ክስተት እንደሚሰማ ተስፋ አላቸዉ።  ደቡብ አፍሪቃዉያን ወጣቶች ስለ «AIDS» መስማት ስለማይፈልጉ ይህ አንድ ትልቅ ርምጃ ይሆን ነበር ሲሉ ሊንዳ ጋይል ቤከር ይገልፃሉ።

Grippeschutzimpfung Flash-Galerie
ምስል picture-alliance/ dpa

« አንድ የሆነ ነገር መከሰት ይኖርበታል። ስለዚህ ተላላፊ በሽታ ጉዳይ አስፈላጊዉን ነገር ካላደረግን፤ መንኮታኮታችን አይቀሪ ነዉ። ይህ ደግሞ እጅግ ያሳስበኛል። በደቡብ አፍሪቃ አንድ አዲስ ነገርን ይዘን ብቅ ማለታችን እጅግ አስደሳች ነዉ። እጅግ ተጎድተናል ፤ ግን መፍትሄ ማግኘታችን ምnm ጥርጥር የሌለዉ ነዉ።  »

እንድያም ሆኖ ምሑራኑ የ «HIV» ስርጭትን ለመግታት የጀመሩት የምርምር ሥራ ዉጤትን ለማግኘት ግዜ ያስፈልጋቸዋል። የምርምሩ ስራ ዉጤት በጎርጎረሳዉያኑ 2020 ዓ,ም ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።

አዜብ ታደሰ / ያና ጌንዝ

ኂሩት መለሰ