1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በመፈራረስ አፋፍ ላይ የምትገኘዉ ኢራቅ

ማክሰኞ፣ የካቲት 1 2008

ከፍተኛ ዉጥረትና ብጥብጥ ዉስጥ የተዘፈቀችዉ ኢራቅ ቢያንስ ለሦስት መከፈልዋ ይነገራል። አንደኛዉ በኩርዶች የሚተዳደረዉ ሰሜናዊ ኢራቅ ሲሆን፤ ማዕከላዊዉ ባግዳድ የሚገኘዉ የኢራቅ መንግሥት ሁለት፤ እንዲሁም ና ሦስተኛዉ ራሱን « እስላማዊ መንግሥት » ብሎ በሚጠራዉ ቡድን የተያዘዉ የኢራቅ ግዛት መሆኑ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1HsBC
Irak Zitadelle in Erbil
ምስል DW/B. Svensson

[No title]

የኢራቅ ጦር ሠራዊት ባለፈዉ ሳምንት በሰሜናዊና ምዕራባዊ ባግዳድ በኩል ወደ ከተማዋ ሊሰነዘር የሚችለዉን የ«IS» ቡድንን ጥቃት ለመከላከል ግንብ እንደሚገነባ አስታዉቋል። ይህን እቅድ ግን የኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይዳር ኧል አባዲ አልተቀበሉትም። እንደ አባዲ ባግዳድ የመላዉ ኢራቃዉያን መዲና በመሆንዋ ማንኛዉም ዜጋ ሊታገድ አይገባም።

Irak Peschmerga-Kämpfer in der Nähe von Erbil
ምስል DW/F. Neuhof

የጀርመን ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትና የአረንጓዴዉ ፓርቲ አባል ክላዉዲያ ሮት ኢራቅን ለስድስት ቀናት ጎብኝተዋል። ሮት በኢራቅ ቆይታቸዉ ከሀገሪቱ የተለያዩ ፖለቲከኞች ጋር ባደረጉት ዉይይት ያገኙትን አስደንጋጭ ፍሬ ሃሳብ በጥቅሉ እንዲህ ነዉ የገለፁት። « በአሁኑ ወቅት ኢራቅ የምትባለዋ ሀገር ኢራቅ አይደለችም። በመፈረካከስ ላይ ያለች ሃገር ናት,,,»

የኢራቅ መንግሥት ያለዉን የአስተዳደር ኃይል ከቀን ወደቀን እያጣ ነዉ። ለበርካታ አስርተ ዓመታት የኢራቅን በትረ ስልጣን ጨብጠዉ የነበሩት የሳዳም ሁሴን መንግሥት በጎርጎሮሳዊዉ 2003 ዓ,ም በዩኤስ አሜሪካ ከተገረሰሰ በኋላ፤ አዲሲትዋን ኢራቅ ለመመሥረት ተሞክሮ ነበር። ግን ይህ ሙከራ ገና ከጅማሮዉ ስኬት የራቀዉ ሆነ። በሀገሪቱ የሃይማኖት ወገንተኝነትን ያማከለ ሙስና እንዲሁም በዝምድና ኃብት የማካበት ስርዓት ተንሰራፋ። በሀገሪቱ «ማን የየትኛዉ እምነት ተከታይ ነዉ?» የሚለዉ ጥያቄ በመጨረሻ ኢራቅን ኧልቃይዳና አጎራባች አገሮች የሚያቀጣጥሉት የእርስ በርስ ጦርነት ዉስጥ ነዉ የከተታት። የሳዳም ሁሴን መንግሥት ከተገረሰሰ ከ 13 ዓመታት በኋላ ዛሬ ፤ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የመንግሥታቱ ድርጅት እንዲሁም የሀገሪቱ ከፍተኛ ፖለቲከኞች ኢራቅ በመፈረካከስ ጠርዝ ላይ እንደሆነች ይናገራሉ። በሀገሪቱ ከነበረዉ ችግር ሌላ አዲስ ችግር መምጣቱንም ይገልፃሉ። በነዳጅ ዘይት ንግድ ለምትተዳደረዉ ኢራቅ በዓለም ላይ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ከቀነሰ በኋላ በሀገሪቱ ኤኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አደጋም ደቅኖአል። በሌላ በኩል ሀገሪቱ ራሱን «እስላማዊ መንግሥት » ብሎ የሚጠራዉን አሸባሪ ቡድን ለመዋጋት የምታወጣዉ ወጪ ቀላል የሚባል አይደለም። ኢራቅን የጎበኙት የጀርመን ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ክላዉዲያ ሮት እንደሚሉት የኢራቅን ወቅታዊ ጉዳይ ያስተዋለዉ የለም።

Deutschland Irak Bundestag Vizepräsident zu Lage der Jesiden
የጀርመን ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትና የአረንጓዴዉ ፓርቲ አባል ክላዉዲያ ሮትምስል Reuters

«ከኔ ሁለተኛ አማራጭ መፍትሄ መፈለግያ ንድፍ መጠየቁ የተሳሳተ ነዉ። እኔ የማምነዉ ኢራቅ ዉስጥ ያለዉ ጉዳይ ማንም ሰዉ እንዳላስተዋለዉ ነዉ። በጣም የሚገርመዉ ደግሞ የሶርያን ጉዳይ በሚመለከት እንዲሁም በስደተኞች ጉዳይ እንዴት አድርጎ ሊባኖስ ዮርዳኖስ እና ቱርክን ማጠናከር እንደሚቻል በለንደኑ የሶርያ ለጋሾች ጉባዔ ላይ ለዉይይት ሲቀርብ የኢራቅ ግን አለመነሳቱ ነዉ። ኢራቅ ላይ ይህ ነዉ የማይባል ትልቅ ችግር መኖሩ እሙን ነዉ።»

ለምሳሌ ለጦርነቱ የሚወጣ ከፍተኛ ወጭና ከነዳጅ ዘይት ሽያጭ የሚገኝ ያልተመጣጠ ገቢ ተጠቃሽ ነዉ። በዚህም ምክንያት ከአምስት ወራቶች ጀምሮ የኢራቅ የመንግሥት መሥርያ ቤት ተቀጣሪዎች ምንም አይነት ደምወዝ አልተቀበሉም። ከዚህ በተጨማሪ ሀገሪቱ ከሌሎች ሰብዓዊ ችግሮች ጋር ተጋፍጣለች። ከሩብ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሶርያዉያን የሀገራቸዉን የርስ በርስ ጦርነት ሸሽተዉ ወደኢራቅ ገብተዋል። ከዚህ ሌላ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ኢራቃዉያን ራሱን «እስላማዊ መንግሥት» ብሎ የሚጠራዉን አሸባሪ ቡድን በመሸሽ እዚያዉ በሀገር ዉስጥ ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዋል። ኢራቅ ዉስጥ የተፈናቀሉት ዜጎችም ሆኑ ሶርያዉያን ደግሞ የሚገኙት በኢራቅ ኩርድ ራስ ገዝ ግዛት ዉስጥ ነዉ ። እነዚህ ሰዎች በኢራቅ ሁኔታዉ ካልተስተካከለ በቀጣይ በአዉሮጳ እድላቸዉን ለመሞከር ዝግጁ ናቸዉ።

« ደግመን ደጋግመን እንደሰማነዉ ኩርድ ላይ ሂደታችን እና ኑሮአችን ምንም ተስፋ የማያመጣ ከሆነ መንገዳችንን እንጀምራለን ነዉ የሚሉት። »

Irak Krieg Kurden Peschmerga Islamischer Staat Sindschar
ምስል Getty Images/J. Moore

የመልከዓምድሩ አቀማመጥ ከኢራቅ ወደ አዉሮጳ ለመጓዝ በጣም ቀላል ነዉ። በኢራቅ የሚገኙ አብዛኞች ስደተኞች በሰሜናዊ የኢራቅ ግዛት ወደምትገኛዋ የቱርክ አዋሳኝ ወደ ዶሁክ ይመጣሉ። በዶሁክ ወደ 1,4 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖር ሲሆን ከነዚህ መካከል 700 ሺዉ ስደተኞች ናቸዉ። ይህም ከኗሪዉ ገሚሱ ማለት ነዉ፤ አብዛኞቹም የሶርያና የኢራቅ ዜጎች ናቸዉ።

በኢራቅ የተፈጠረዉ ምስቅልቅ ያስከተለዉን መዘዝ የተረዱት የኢራቅ የኩርዲስታን ፕሬዚዳንት አንድ ዉሳኔ ላይ ደርሰዋል። ፕሬዚዳንቱ ባለፈዉ ሳምንት ዉስጥ ይፋ እንዳደረጉት በኢራቅ የስደተኞችን ጉዳይ በተመለከተ ማዕከላዊዉ የኢራቅ ባግዳድ መንግሥት ምንም ያደረገዉ ነገር ባለመኖሩ የኢራቅ የራስ ገዝ የሆነዉ የኩርድ ግዛት ነፃነቱን እንዲያገኝ ሕዝበ ዉሳኔ ያካሂዳሉ። ይህም በመፈረካከስ ላይ ያለችዉ የቀድሞዋ ኢራቅ በቅርቡ ከዓለም ካርታ ላይ ያጠፋታል የሚል ስጋት አለ።

ዮርን ብላሽኬ /አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ