1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በርካታ ቤቶች ፈረሱ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 16 2009

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የምትገኘው የመርሳ ከተማ በርካታ ቤቶችን ህገወጥ ናቸው በሚል አፈረሰ፡፡ ቤታቸው የፈረሰባቸው ያለመጠለያ መቅረታቸውን እና ንብረቶቻቸው ላይ ጉዳት መድረሱን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2RkDo
ከወራት በፊት በአዲስ አበባም ሕገወጥ የተባሉ ቤቶች ፈርሰዋል
ከወራት በፊት በአዲስ አበባም ሕገወጥ የተባሉ ቤቶች ፈርሰዋል ምስል DW/Y. Egziabare

Meresa town administration demolishes Hundreds of Houses - MP3-Stereo

ቤቶቹ የፈረሱት በመርሳ ከተማ ዙሪያ በሚገኙት አቧሬ፣ ወረ ላሎ እና ቀበሮ ሜዳ በተሰኙ አካባቢዎች ነው፡፡ የከተማዋ አስተዳደር ቤቶቹን ማፍረስ የጀመረው ዛሬ ጠዋት እንደነበር እና እርምጃው እስከ እኩለ ቀን መቀጠሉን ነዋሪዎች ለዶይቸ ቨለ ገልጸዋል፡፡ የአካባቢው ፖሊስ፣ ሚሊሽያ እና አፍራሽ ግብረ ኃይል በዶዘር በመታገዝ ቤቶቹን ሲያፈርሱ መመልከታቸውን ያስረዳሉ፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የከተማይቱ ነዋሪ አንዳንዶቹ ቤቶች ንብረታቸው በውስጥ እንዳለ ይፈርሱ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ “በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ዕቃ፣ ንብረት የወጣ ምንም ነገር የለም፡፡ በዶዘር እና በተለያየ ነገር ነው እየፈረሰ ያለው፡፡ ህገ ወጥ ቤት ተብለው ነው የፈረሱት፡፡ አሁን ህዝቡ ሜዳ ላይ ነው ያለው” ሲሉ ዛሬ በመርሳ ስለነበረው ሁኔታ ይገልጻሉ፡፡

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳስተዋሉ እና ከየቤቶቹ የተነቀሉ ጣሪያዎች በመኪና ተጭነው እንደተወሰዱ መስማታቸውን ያስረዳሉ፡፡ “ሰዎቹን ውጭ ላይ አድርገው ጣራውን እና ቆርቆሮውን እየገፈፉ ወዲያው ወሰዱት ነው የሚሉት፡፡ ከሰዓት የለም፡፡ ጠዋት ላይ፣ ማርፈጃቸውን ግን እየጫኑ ወስደዋል፡፡ ቤት ውስጥ እያሉ እሪ እያሉ እያለቀሱ ነው አፍርሰው የሄዱት” ብለዋል፡፡

የሚፈርሱ ቤቶችን በሚመለከት የተቋቋመ ኮሚቴ “ቤት አልባ የሆኑትን ሰዎች ምን እናድርጋቸው?” በሚል ስብሰባ እንደተቀመጠ መስማታቸውን ይናገራሉ፡፡ በአካባቢው ነዋሪ የሆኑ እና ህገወጥ ስለተባሉ ቤቶች መረጃ ለኮሚቴ ሲሰጡ የነበሩ እንኳ “እነዚህ ሰዎች የት ሊያድሩ ነው? ብርድ እየመጣ ነው” ሲሉ መወያየታቸውንም ይጠቁማሉ፡፡      

በከተማዋ በትንሹ ከ300 እስከ 400 ቤቶች እንደፈረሱ እንድ የከተማዋ ነዋሪ የተናገሩ ሲሆን ሌሎች ግን ቁጥሩ ከዚያም በላይ ከፍ ሊል ይችላል ይላሉ፡፡ በቁጥሩ ላይ እንዳለው ልዩነት ሁሉ ቤታቸው ለፈረሰባቸው ነዋሪዎች ቅድመ ማስጠንቀቂያ መሰጠት አለመሰጠቱ ላይም ነዋሪዎች ልዩነት ያሳያሉ፡፡ በአንድ ወገን ያሉት አፍራሽ ግብረ ኃይሎች ድንገት መጥተው ቤቶቹን ማፍረስ እንደጀመሩ ሲናገሩ ሌሎቹ ደግሞ “ከሳምንት በፊት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል” ባይ ናቸው፡፡

Äthiopien - Zerstörte Häuser und deren ehemalige Bewohner in Addis Abeba
ምስል DW/Y. Egziabare

“ምንም የተነገረ ህዝቡ ያወቀው ነገር የለም፡፡ ህገ ወጥ ቤት በሚል ነው እየፈረሱ ያሉት፡፡ ህዝቡ የሰማው ነገር የለም፡፡ ዕቃ ያወጡት ነገር የለም፡፡ እዚያው ላይ እያተረማመሱት ነው ያሉት፡፡ እና በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ህዝቡ አሁን ለቅሶ ላይ ነው” የሚሉት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት የከተማዋ ነዋሪ ናቸው፡፡

ከሳምንት በፊት ማስጠንቀቂያተሰጥቷል የሚሉት የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው “ይፈርሳል ብለው በአብላጫ አሰወስነዋል፡፡ ከሳምንት በፊት ይፈርሳል ብለው ነግረዋቸዋል፡፡”      

ቤቶቹ የፈረሱት በህገወጥ መንገድ ተገንብተዋል ተብለው ነዋሪዎቹ ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም እንዳንዶቹ ካርታ የነበራቸው እንደሆነ እና የቤቶቹ ባለቤቶች ከአካባቢው አርሶ አደ መሬት ገዝተው ግንባታ ሲያከናኑ በአስተዳደሩ በኩል በዝምታ መታለፉን ወደ ኋላ መለስ ብለው ያስታውሳሉ፡፡

“ሰዎች እንኖርበታለን ብለው ከገበሬውም እየገዙ የሰሩ አሉ፡፡ ደብተርም ያላቸው መኖሪያ ብለው እየኖሩ ያሉ፡፡ እየኖሩበት ቢሆንም ህገ ወጥ ነው በማለት ጠቅላላ ዛሬ ከጠዋት ጀምረው ሲያፈርሱ ነው የነበረው” ይላሉ የከተማይቱ ነዋሪ ፡፡          

በከተማ ዳር በተገነቡት ቤቶች ውስጥ ነዋሪ የነበሩት ግለሰቦች በአብዛኛው በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ እንደነበሩ የከተማዋ ነዋሪ ያብራራሉ፡፡ “የገጠር ሰዎች ናቸው፡፡ ከተማ ማን ያስገባቸዋል፡፡ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ከገጠር ወደዚያ ይመጡና እዚያ አካባቢ ይሰፍራሉ፡፡ ወደየት ይጠጋሉ ወደከተማ?”

በጉዳዩ ላይ የከተማውን አስተዳደር አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፡፡ የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ስለጉዳዩ መረጃ የለኝም የሚል ምላሽ ሰጥቷናል፡፡ የመርሳ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ ዘቢባ ደጉ ምላሽ ለመስጠት ተሰማምተው የነበረ ቢሆንም በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ላይ ደጋግመን ብንደውልም ሊያነሱን አልቻሉም፡፡  

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ