1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቆሻሻን ለአስፋልት ግንባታ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 26 2007

በሚሊየን ዓመታት ሂደት ከቅሪተ አፅም የሚፈጠረዉ ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት የሃይድሮ-ካርቦኖች ድብልቅ ነዉ። ይህ ከከርሰ ምድር የሚወጣ የነዳጅ ዘይት ድፍድፍ ሲጣራ ነዉ በሂደቱ ለመንገድ ግንባታ የሚዉለዉ ሬንጅ የሚገኘዉ።

https://p.dw.com/p/1GPj6
Symbolbild Mafia Süditalien Müll Neapel
ምስል picture-alliance/dpa/C. Abbate

ቆሻሻን ለአስፓልት ሥራ

በማጣራቱ ሂደትም የነዳጅ ዘይቱ ድፍድፍ ከድብልቅ የካርቦን ንጥረነገሮች በመገኘቱ ከፍተኛ መጠን ያለዉ ካርቦን ወደከባቢ አየር ይገባል። በከባቢ አየር የሚከማቸዉ ካርቦንና ሌሎች ሙቀትን አምቀዉ የሚይዙ አደገኛ ጋዞች ተባብረዉ የአየር ሙቀት መጨመር ለዓለማችን ዋና ስጋት እንዲሆን ማብቃታቸዉን የዘርፉ ተመራማሪዎች በየጊዜ ይገልፃሉ።

ይህና ሌሎች ምክንያቶች ተባብረዉም የምድርን የሙቀት መጠን በማባባስ ለአየር ንብረት መለዋወጥ ዋነኛዉን ሚና ይጫወታሉ። እንዲህ ያለዉን ችግር ማስቀረት ባይቻል እንኳ ወደከባቢ አየር የሚገባዉን የበካይ ጋዝ ልቀት ለመቀነስ እንዲረዳ በማሰብ ነዉ ከየጓዳዉ የሚጣሉ ተረፈ ምግቦችን አስፓልት ለመሥራት የሚዉለዉን ሬንጅ ቦታ እንዲወስዱ የተሞከረዉ። በሙከራ ብቻም አልቆመም ጣልያን ዉስጥ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል።

ከቆሻሻ መንገድ መገንባት ይቻላል ሲባል መጀመሪያ ግር ይል ይሆናል። በጣሊያንዋ ዋና ከተማ ሮም ግን ይህ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል። እንዲህ ነዉ ነገሩ፤ የየቤትና ጎዳናዉን ቆሻሻ የሚያነሳዉ ኩባንያ ዉዳቂዉን ምን ማድረግ እንዳለበት አያዉቅም ነበር። ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ግን የየቤቱ የጓዳ ቆሻሻ ሁሉ በስርዓት ወደሌላ ጥቅም እንዲዉል በሚያስችለዉ ስልት ይስተካከል ጀምሯል። በዚህም አስፓልት መንገዶችን ጠብቀዉ እንዲቆዩ የሚያደርጋቸዉ ሬንጅን የሚተካ ምርት እየተገኘ ነዉ። ቆሻሻ የጣሊያን ብቻ ሳይሆን የብዙ ሃገራት ችግር ነዉ። ሮም ከተማ ብቻ በየዓመቱ ሁለት ሚሊየን ቶን ገደማ ቆሻሻ ይከማችባታል። ይህ ነዉ ከተፈጥሮ የተገኘ ሬንጅ እንዲመረት ምክንያት ሆኖ የባለቤትነት መብትና ፈቃድ የተሰጠዉ።

«በተፈጥሮ ምርቶችን ወደአስፓልት መገንቢያ ሬንጅ የመቀየሩ ሃሳብ ቆሻሻን ወደጠቃሚ ምርት የመለወጥ ሂደት ነዉ።»

ይላሉ ሮም የሚገኘዉ የቆሻሻ አስወጋጅ ኩባንያ ኃላፊ አሌሳንድሮ ፊሊፕ። ኩባንያዉ ቆሻሻን ወደአስፓልት መገንቢያ ሬንጅ የመቀየር ሃሳብ የባለቤትነት ፈቃድ አለዉ። ፊሊፕ እንደሚሉት አገልግሎቱና ተግባሩ በአዉሮጳ የታሪክ ማህደር ከሚባሉት ዉብ ከተሞች አንዷ ከሆነችዉ ሮም በሚሊየን ቶን የሚገመተዉን ቆሻሻ ያፀዳል። ይህ ባይሆን ኖሮ ዳግም ለሌላ ጥቅም የማይዉለዉ ዉዳቂ ሁሉ ዉሎ አድሮ ከተማዋን የሚበክል ሊሆን እንደሚችልም ያስረዳሉ።

«እንዳሁኑ ቆሻሻዉ ሁሉ ዳግም ለሌላ ጥቅም እንዲዉል ባይሠራ ኖሮ የሚጣለዉ ዉዳቂ አካባቢዉን ይበክለዉ ነበር። አሁን ከዚህ ሙሉ በሙሉ ድኗል። ይህም ለአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃዉ ትልቅ ድል ነዉ።»

Tunnel Blanka in Prag
ምስል picture-alliance/dpa/M. Dolezal

እርግጥም ቆሻሻን ከየጎዳናዉ ከየደጁ በማንሳት ተግባር የተሠማራዉ ኩባንያ ከየጓዳዉ የምግብ ትርፍራፊዎች እና ዉዳቂዎች መሥራት ስለሚቻለዉ የመንገድ መገንቢያ ሬንጅ ብዙ ማብራራትና ማስታወቂያ ብጤም መሥራት ነበረበት። የገቢ ምንጭነቱ አንድ ነገር ቢሆንም አካባቢን ከብክለት ለማፅዳት የተነሣለት ዋናዉ ዓላማ ግን በዋጋ የሚተመን አይሆንም። በየቤቱ ደጅና በየጎዳናዉ የሚገኙት የቆሻሻ ማከማቻዎች ተንፈስ ብለዋል። እንደበፊቱ ወደሌላ ጥቅም የማይለወጥ ዉዳቂ ማሰባሰቢያ ሳይሆኑ የጥሬ እቃ መሰብሰቢያዎች ናቸዉ ዛሬ።

ሮም ከቆሻሻ ተጣርቶ በሚመጣ አካባቢን በማይበክል የመንገድ መገንቢያ ሬንጅ የመጠቀም ተስፋዋ ከፍ ማለቱ ቢነገርላትም የሚጣሉት ቆሻሻዎች ሁሉ ዳግም ሌላ ጥቅም ላይ የሚዉሉ ናቸዉ ማለት ግን አይደለም። የግድ ለሚፈለገዉን የአስፓልት መንገድ መሥሪያ የሚሆነዉን ምርት ማስገኘት የሚችሉት መመረጥ ይኖርናቸዋል። የከተማዋ ምክትል ከንቲባ እስቴላ ማሪኖ ይህ ተግባር እየተስፋፋ ሲሄድ ወደፊት ሮም ዉስጥ የቆሻሻዉን ክምችት ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ መገመት አይከብድም ነዉ የሚሉት።

«ከቆሻሻዉ ቀደም ተብሎ እንደተገለፀዉ ሬንጅ ማዘጋጀት ይቻላል፤ ለዚህ የማይሆነዉን ደግሞ ለሚገነባዉ መንገድ መደላድል ማድረግ፤ አልፎ ተርፎም የብስኪሌት መሄጃ መንገድ ሁሉ መሥራት ይቻላል። ይህን በማድረጋችንም ከተማችን ዉስጥ በየመንገዱ የሚከመረዉ ቆሻሻ ጥቅም ላይ እናዉላለን።»

ከቆሻሻዉ ሬንጅን የማምረቱ ተግባር ያን ያህል ዉስብስብ ሂደት እንዳልሆነ ነዉ የሮም ከተማን ቆሻሻ የሚያስወግደዉ ኩባንያ ኃላፊ ፊሊፕ የሚያስረዱት። ቆሻሻዉ ከመጀመሪያዉ በሁለት ወገን ይከፈላል። የምግብ ትርፍራፊና ለምግብ ዝግጅቱ የዋሉ አትክልቶች ዉዳቂ በአንድ ወገን ተለይቶ ይከማቻል። ከዚህ ዉስጥ የየግቢዉ አትክልት ቁርጥራጭ እና ሌላ ሌላዉም ይካተታል። ይህ ከሌላ ነገር ጋር ይደባለቃል ለምሳሌ ከአመድ ጋር። ፊሊፕ ያስረዳሉ፤

«የዚህ ዉጤት ክትትልና ቁጥጥር ይደግበታል፤ ይህም በዉስጡ ተፈጥሮ ላይ ምን ዓይነት ጉዳትና አደጋ ሊያስከትል የሚችል ነገር እንዳይገባ ለመጠንቀቅ ይረዳል።»

ሮም በአሁኑ ጊዜ በአጠቃላይ ከከተማዋ ከሚሰበሰበዉ ቆሻሻ አንድ ስድስተኛ የሚሆነዉን ለመንገድ ግንባታ አስፈላጊ የሆነዉን ሬንጅ እያመረተችበት ነዉ። ያ ማለት ደግሞ 300 ቶን ገደማ ይሆናል በአንድ ዓመት። ቆሻሻን ወደጠቃሚ ምርት በመለወጥ በተለይም ለመንገድ ግንባታ ያዋለችና በዚህም ላይ ሙከራ እያካሄደች የምትገኘዉ ሀገር ጣሊያን ብቸኛዋ አይደለችም። የሮም ምክትል ከንቲባ እስቴላ ማሪኖ እንደሚሉት የባለቤትነቱ ጥያቄ የማያነጋግር ቢሆንም ሀገራቸዉ ሀሳቡንና ስልቱን ከሌሎች ጋር ለመጋራት አይከብዳትም።

Italien Müll in den Straßen von Neapel Protest
ምስል Anna Monaco/AFP/Getty Images

«ይህ የፈጠራ ጥንካሬያችንን የሚያረጋግጥ እንደሚሆን ተስፋ አድርጋለሁ፤ በተለይም በአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃዉ ቴክኒዎሎጂ በየጊዜዉ ለየት ያሉ ነገሮችን ይዘን መቅረባችን የተለመደ ነዉ። ያም ሆኖ ግን ይህን በሚመለከት ከሌሎች ሃገራትና ከተሞች ጋር ስንወዳደር የእኛ የላቀ ነዉ ማለት እችላለሁ።»

አሁን ሮም የራሷን ከተማ ከቆሻሻ ክምችት በስልት አላቅቃ ሙያዋን ይዛ ከተረፈ ምግብ አትክልቶች የተዘጋጀ ሬንጇን ለዓለም ገበያ የማቅረብ ተስፋ ሰንቃለች። ይህን ለማዘጋጀት ደግሞ አስፈላጊዉ ጥሬ እቃ ያልቃል በማይባል መጠን እንደልብ ታገኘዋለች።

እንደጣሊያን ሁሉ ይህን ምርምር የገፋችበት ዩናይትድ ስቴትስ ናት። እዚያ ደግሞ በተለይ ድንች የተጠበሰበት ዘይት እና የአትክልቶች ዉዳቂ ለሬንጅ መሥሪያዉ ዓይነተኛ ጥሬ እቃዎች ናቸዉ። በየቤቱም ሆነ ምግብ ቤቶች ለተለያዩ ምግቦች መጠባበሻ የሚዉለዉ ዘይት እየተደፋ የዉኃም ሆነ የአፈር ብክለቱን ከሚያባብስ ይህ ስልት ጠቃሚ የአካባቢ ተፈጥሮ መጠበቂያ ሊሆን እንደሚችል ነዉ ምርምሩን የጀመረዉ የዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የገለፀዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ