1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥር 1 2009

የኢትዮጵያ ቡና ከወልድያ ከነማ ጋር ባደረገው ጨዋታ የስፖርት ታዳሚያንን ያስደነገጠ ክስተት ተፈጥሮ ነበር። በጨዋታው ወቅት አንገቱ ላይ ተመትቶ ራሱን የሳተው የቡናው የተከላካይ የመስመር ተጨዋች አህመድ ረሸድ ዛሬ ከሐኪም ቤት ወደ ቤቱ ገብቷል። በስልክ ስናናግረው ደከም ባለ ድምጹ «በጨዋታ ወቅት የሚከሰትን ነገር አታውቀውም» ብሏል።

https://p.dw.com/p/2VXFe
Spanien Cristiano Ronaldo und Lionel Messi
ምስል picture alliance /empics/PA Wire

ስፖርት፤ ጥር 1 ቀን፣ 2009 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ ጨዋታ 10ኛ ሳምንቱን ነገ ይጀምራል።  የባለፈው ሳምንት ዘጠነኛ ዙር ግጥሚያ የኢትዮጵያ ቡና ከወልድያ ከነማ ጋር ባደረገው ጨዋታ የስፖርት ታዳሚያንን ያስደነገጠ ክስተት ተፈጥሮ ነበር። በጨዋታው ወቅት አንገቱ ላይ ተመትቶ ራሱን የሳተው የቡናው የተከላካይ የመስመር ተጨዋች አህመድ ረሸድ ዛሬ ከሐኪም ቤት ወደ ቤቱ ገብቷል። በስልክ ስናናግረው ደከም ባለ ድምጹ «በጨዋታ ወቅት የሚከሰትን ነገር አታውቀውም» ብሏል።

Brasilien Olympische Spiele Rio 2016 21 08 - Marathon Feyisa Lilesa
ምስል Getty Images/AFP/O. Morin

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጨዋታው ዝርዝር መረጃ እንደደረሰው አስፈላጊውን ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ ለዶይቸ ቬለ ገልጧል። የለንደን ማራቶን ውድድር ላይ ከፍተኛ ግምት የተሰጠው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ ባስገኘበት የሪዮ ኦሎምፒክ እጆቹን ከፍ አድርጎ በማነባበር መንግስት ላይ ተቃውሞ ያሰማው አትሌት ፈይሳ ሊሌሳ እንደሚወዳደሩ ይፋ ኾኗል። በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ነጥብ ጥሏል።  

የኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ ዐሥረኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ ይከናወናሉ። ደደቢት እና አዳማ ከነማ በእኩል 18 ነጥብ ሆኖም በግብ ልዩነት አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንድ ነጥብ በአዳማ ከነማ ተበልጦ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል። ኢትዮጵያ ቡና በ10 ነጥብ ደረጃው ዐሥረኛ ነው። የሶከር ኢትዮጵያ የስፖርት ድረ-ገጽ ዋና ኤዲተር ኦምና ታደለ ጨዋታዎቹን ተከታትሏል።

ከባድ ጉዳት የደረሰበት የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋች

ሐሙስ ዕለት ድሬዳዋ ከነማን 3 ለ0 የረታው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከነገ በስትያ ከወልድያ ጋር ይጫወታል። ወልድያ ባለፈው ዐርብ የኢትዮጵያ ቡናን  1 ለ0 መርታቱ ይታወሳል። የኢትዮጵያ ቡና ዐሥረኛ ሳምንት ግጥሚያውን ነገ የሚያከናውነው  ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነው። የኢትዮጵያ ቡና ከወልድያ ጋር ባደረገው ጨዋታ የመስመር ተከላካይ ተጨዋቹ  አህመድ ረሸድ በቅጽል ስሙ ሽሪላው  አንገቱ ላይ ተረግጦ ከባድ አደጋ ደርሶበት ነበር።

ጨዋታው ለ10 ደቂቃ ያህል ተቋርጦ ጉዳት የደረሰበት ተጨዋች ወደ ሐኪም ቤት እንደተወሰደም ተገልጧል። ለመሆኑ አህመድ ረሸድ አሁን ጤንነቱ ምን ይመስላል? ከሀኪም ቤት ወጥቶ እቤቱ እንደገባ በስልክ አግኝተነዋል። ስናነጋግረው አንገቱ ላይ የደረሰበት ጉዳት ኅመም እየተሰማው ነበር። «በመስመር በኩል የተመታውን ኳስ [አየር ላይ ተንሳፍፌ] ስመለስ ነው ልጁ የነካኝ  ከዛ በኋላ ራሴን አላውቅም፤ የተፈጠረውን ነገር አላስታውስም» ብሏል። ሕይወቱን ለማዳን ረዥም ጊዜ ርብርብ እንደተደረገ፤ ምላሱን ወደ ቦታው ለመመለስም ብዙ እንደፈጀ ገልጧል። «አንገቴ ላይ ነው ትንሽ የረገጠኝ፤ አውቆ ነው ብዬ አልገምትም» ሲልም የደረሰበት ጉዳት ሆነ ተብሎ ይሁን አይሁን እንደማያውቅ ተናግሯል። 

Berlin-Marathon Sieger Kenenisa Bekele aus Äthiopien
ምስል Reuters/F. Bensch

በአህመድ ረሸድ ላይ የደረሰው ጉዳት ጥፋት ይሁን አጋጣሚ የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን በማጣራት አስፈላጊውን ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ ለዶይቸ ቬለ  ገልጧል። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውድድር ክፍል ባለሙያው አቶ  ዳንኤል ዘለቀ ተጨዋጡ ላይ ስለደረሰው ጉዳት ጠይቀናቸው፦ «በመጀመሪያ ደረጃ በእግር ኳስ ሕግ ውስጥ» ዳኛው በተሰጠው ሥልጣን መሰረት ይወስናል ብለዋል። የዕለቱ ዳኛ ጉዳት ደርሷል ብሎ ካሰበ ዳኛው የራሱን ውሳኔ ያስተላልፋል «ያን ውሳኔም በጽሑፍ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን» እንደሚቀርብም ገልጠዋል። የዕለቱ ዳኛ እና የጨዋታው ተቆጣጣሪ የሰበሰቡት መረጃ በስልክ እስካነጋገርንባቸው ሰአት ድረስ እንዳልደረሳቸው አስታውቀዋል። መረጃው እንደደረሳቸውም ፌዴሬሽኑ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ ተናግረዋል።  

የኢትዮጵያ ቡና እና ወልዲያ ጨዋታዎችን የመሩት ዳኛ የጨዋታ ዝርዝር ማብራሪያ እንደደረሰው ፌዴሬሽኑ በተቀመጠለት የዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት የሕግ ክፍሉ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍም ተናግረዋል።

አትሌቲክስ

ከሁለት ሳምንት በኋላ በሚከናወነው የለንደን ማራቶን የሩጫ ፉክክር ላይ አትሌት ቀነኒሳ እና አትሌት ፈይሳ ሊሌሳ እንደሚገኙ የለንደን ማራቶን አዘጋጆች በድረገጽ ጽሑፋቸው አስታውቀዋል። ተስፋዬ አበራ፣ ጥላሁን ረጋሳ እና አሰፋ መንግሥቱም በውድድሩ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መሆናቸው ታውቋል። ግርማይ ገብረሥላሴ፣አማኑኤል መሰለ እና ገብሬ ክብሮም ኤርትራን ወክለው ይሳተፋሉ። የኬንያዎቹ አቤል ኪሩይ፣ ዳንኤል ዋንጂሩ እና ቤዳን ካሮኪ ሙቺሪም ተሳታፊዎች ናቸው።

ኤፍ ኤካፕ

በእንግሊዝ ኤፍ ኤካፕ የእግር ኳስ ፍልሚያ በፕሬሚየ ርሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል ሁለተኛ ዲቪዚዮን ከሚገኘው ፕሌይማውዝ አርጊል ጋር በሜዳው አንፊልድ ገጥሞ ነጥብ ጥሏል። ሁለቱ ቡድኖች ትናንት ባደረጉት ጨዋታ የሊቨርፑሉ አማካይ ኤምሬ ካን የመሀል ሜዳውን በሚገባ ተቆጣጥሮ ቆይቷል። በእርግጥ ጀርመናዊው አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ እስከ ጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ ድረስ ያሰለፏቸው ወጣት ተጨዋቾቻቸውን ነበር። በኋላ ላይ የገቡት ዳንኤል ስቱሪጅ እና አዳም ላላና ሊቨርፑልን ከዜሮ ከመውጣት አላዳኑትም። ዳንኤል ስቱሪጅ በግቡ ቋሚ ጥግ ደጋግሞ የመታቸው ኳሶች መክነዋል።

ትናንት ቶትንሀም ከአስቶን ቪላ ጋር ተገናኝቶ በዳቪስ እና ሶን ግቦች 2 ለ0 ማሸነፍ ችሏል።  አንደኛ ዲቪዚዮን ውስጥ የሚጫወተው ሚልዋል የፕሬሚየር ሊጉ በርመስን 3 ለ0 ኩም አድርጓል። ቅዳሜ ዕለት ማንቸስተር ዩናይትድ በሜዳው ኦልትራፎርድ ሪዲንግን 4 ለ0 ሸኝቷል። አንድ ቀን ቀደም ብሎ ደግሞ ማንቸስተር ሲቲ ዌስትሀምን 5 ለ0 የግብ ጎተራ አድርጎ ሸኝቶታል። አርሰናል በእንግሊዝ እግር ኳስ ሊግ ሻምፒዮንሺፕ ተሳታፊው ፕሬስተንን 2 ለ1 ቅዳሜ ዕለት አሸንፏል። የፕሬሚየር ሊግ መሪው ቸልሲ አንደኛ ዲቪዚዮን የሚገኘው ፔተርቦሮውን 4 ለ0 ድል አድርጓል።

Schweiz | FIFA-Präsident Gianni Infantino und Diego Maradona
ምስል picture-alliance/AP Photo/W. Bieri

ፊፋ

የዓለም አግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ፊፋ ዛሬ ማምሻውን በስዊትዘርላንድ መቀመጫው በዙሪክ በሚካሄድ ታላቅ ፌስታ  የ2016 ምርጥ ተጨዋቾች አሸናፊዎችን ይፋ ያደርጋል። ከዘጠኝ ቀናት በፊት የተገባደደውን የ2016 ዓ.ም.ን ኮከብ ተጫዋቾችና አሠልጣኝ መርጦም ይሸልማል። በዘንድሮው ውድድር የፖርቹጋሉ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ፣ የፈረንሳዩ አንቶኒዮ ግሪዝማን እንዲሁም የአርጀንቲናው ሊዮኔል ሜሲ ለፍጻሜ ቀርበዋል። የአርጀንቲናው የዓለም እግር ኳስ የምንጊዜም ምርጥ ዲያጎ ማራዶና ፊፋ ለዓለም ዋንጫ የተሳታፊ ሃገራት ቁጥር ከ32 ወደ 48 ከፍ እንዲል የቀረበውን ማሻሻያ እንደሚደግፍ ገለጠ። ፊፋ የተሳታፊ ሃገራትን ቁጥር ዛሬ በሚያደርገው ስብሰባ ወደ 48 ከፍ እንደሚያደርገው ይጠበቃል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም  ተክሌ