1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ታኅሣሥ 03 ቀን፣ 2009 ዓ.ም.

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 3 2009

እንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ  የደረጃ ሠንጠረዥ መሪው ቸልሲ እና ተከታዩ አርሰናል በሳምንቱ ማሳረጊያ ላይ ባደረጉት ጨዋታ አሸንፈው ተጨማሪ ነጥብ ሰብስበዋል። ሊቨርፑል ነጥብ መጣሉን ቀጥሏል።  በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ላይፕትሲሽ ማሸነፍ ቢችልም በደረጃ ሰንጠረዡ መሪነቱን ለባየር ሙሽይንሽን አስረክቧል።

https://p.dw.com/p/2UAL9
Deutschland FC Schalke 04 v Bayer 04 Leverkusen
ምስል Getty Images/Bongarts/S. Franklin

ስፖርት፣ ታህሳስ ሶስት፣ 2009

በኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ አምስተኛ ዙር የእግር ኳስ ጨዋታ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ አቻ ሲወጣ፤ ኢትዮጵያ ቡና አሸንፏል።  በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ  የደረጃ ሠንጠረዥ መሪው ቸልሲ እና ተከታዩ አርሰናል በሳምንቱ ማሳረጊያ ላይ ባደረጉት ጨዋታ አሸንፈው ተጨማሪ ነጥብ ሰብስበዋል። ሊቨርፑል ነጥብ መጣሉን ቀጥሏል።  በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ላይፕትሲሽ ማሸነፍ ቢችልም በደረጃ ሰንጠረዡ መሪነቱን ለባየር ሙሽይንሽን አስረክቧል። የአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ለመምራት ከተመረጡ 17 አፍሪቃዊ ዋና ዳኞች መካከል ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ዳኛ ይገኙበታል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቸልሲ ግስጋሴውን ቀጥሏል። አርሰናል እግር በእግር እየተከተለ ነው። ወደ ዝርዝር ከማለፋችን በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለተከናወኑ የፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎች አጠር ያለ ቅኝት ይኖረናል። በሶከር ኢትዮጵያ ዶት ኔት ድረ ገጽ የስፖርት ጋዜጣ ላይ መጋቤ አርታኢ ሆኖ የሚያገለግለው ሣሙኤል የሺዋስ ጨዋታዎቹን በስታዲየም ተገኝቶ ተከታትሏል። በሳምንቱ መጨረሻ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች አምስተኛ ሣምንት ስምንት ጨዋታዎች ተደርገዋ።  «ከእነዚህ ስምንት ጨዋታዎች ውስጥ ስድስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቋል» ሲል ሣሙኤል አክሏል።

Großbritannien Manchester - Fussball Premier League - Manchester City vs Manchester United
ምስል Getty Images/A. Livesey

የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የአዳማ ከተማ ጨዋታ በደጋፊዎች እና በተመልካቾች ዘንድ እንደተጠበቀው ሆኖ አለመጠናቀቁን ጋዜጠኛ ሣሙኤል የሺዋስ አክሎ ጠቅሷል። ሁለቱ ቡድኖች ባለፈው ዓመት የጨዋታ ዘመን ላይ እንደታየው ሁሉ ከማጥቃት ይልቅ መከላከል ላይ በማተኮር ነጥብ ይዘው ለመውጣት ሲሞክሩም ታይተዋል።

የኢትዮጵያ ቡና ከሲዳማ ጋር ያደረገውን ጨዋታ በማሸነፉ ቡድኑ በአራት ጨዋታ 2 ነጥብ ብቻ በመያዝ ከነበረበት የነጥብ ቀውስ የተገላገለበት መሆኑን ሣሙኤል ጠቅሷል።  የኢትዮጵያ ቡና 2 ለ1 ቢያሸንፍም ሲዳማ ቡና በደረጃ ሠንጠረዡ ቅዱስ ጊዮርጊስን ተከትሎ አሁንም ሁለተኛነቱን አስጠብቋል። በሜዳው የነበሩት የቡና ደጋፊዎች ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበረም ተገልጧል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 10 ነጥብ አለው። ሲዳማ ቡና በ9 ይከተላል። 

ጋቦን በምታዘጋጀው 31ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ ውድድሮችን የሚያጫውቱ 17 ዋና ዳኞች እና 24 ረዳት ዳኞች ማንነት ይፋ ተደርጓል። በዋና ዳኞች ስም ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያዊው የእግር ኳስ ዳኛ በአምላክ ተሰማ ይገኙበታል።

ዌስት ብሮሚችን ትናንት 1 ለምንም የረታው ቸልሲ የደረጃ ሰንዘረዡን በ37 ነጥብ እየመራ ነው። አርሰናል ከትናንት በስትያ ስቶክ ሲቲን 3 ለ1 በማሸነፍ ነጥቡን 34 አድርሷል። የሁለተኛነት ደረጃውንም እንዳስጠበቀ ነው። የደረጃ ሠንጠረዡን ሲመራ ቆይቶ ቀስ እያለ ያስረከበው ሊቨርፑል በተደጋጋሚ ነጥብ ጥሏል።  ሊቨርፑል ትናንት ዌስትሐምን ገጥሞ ሁለት እኩል በመለያየቱ ከ15ኛ ጨዋታው በኋላ በ31 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቅዳሜ ዕለት በላይስተር ሲቲ 4 ለ2 ጉድ የሆነው ማንቸስተር ሲቲ ሊቨርፑልን በአንድ ነጥብ ርቀት ይከተለዋል። ማንቸስተር ዩናይትድ በሚኪታሪያን ብቸኛ ግብ ትናንት ቶትንሐምን 1 ለምንም ማሸነፍ ቢችልም፤  በደረጃ ሠንጠረዡ አምስተኛነቱን ግን ሊነጥቀው አልቻለም። 27 ነጥብ ይዞ 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቶትንሀም ማንቸስተር ዩናይትድን በ3 ነጥብ ይመራል።  

Henrikh Mkhitaryan
ምስል picture alliance/Zumapress

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ዘንድሮ ከታችኛው ዲቪዚዮን ያደገው ላይፕትሲሽ ቡድን በ14ኛ መደበኛ ጨዋታው መሪነቱን ለባየር ሙይንሽን አስረክቧል። ቅዳሜ ዕለት ቮልፍስቡርግን በሰፋ የግብ ልዩነት 5 ለ0 ያንኮታኮተው ኃያሉ ባየር ሙይንሽን ከላይፕትሲሽ ጋር በነጥብ እኩል ቢሆንም በግብ ክፍያ ልዩነት ግን አንደኛ መሆን ችሏል። ላይፕትሲሽን ቅዳሜ ዕለት ጉድ የሠራው ዘንድሮ ወደ ቡንደስሊጋው አብሮት ያደገው ኢንግሎሽታድት ቡድን ነው። ሆኖም ኢንግሎሽታድት በ9 ነጥብ የደረጃ ሠጠረዡ ጠርዝ ላይ በ17ኛ ደረጃ ይገኛል። በወራጅ ቃጣናው በአንድ ነጥብ የሚበልጠው ዳርምሽታድትን ብቻ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ