1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ሚያዝያ 17 ቀን፤ 2008 ዓ.ም.

ሰኞ፣ ሚያዝያ 17 2008

እንግሊዛዊው ጠፈርተኛ ከምድር ውጪ ከኅዋ ዓለም አቀፍ የጠፈር ማዕከል ሆኖ የለንደኑ ማራቶንን ተሳትፏል፤ በጊነስ ቡክ ላይም ተመዝግቧል። በዚሁ በወንድም በሴትም ኬንያውያን አሸናፊ በሆኑበት የለንደን ማራቶን የሩጫ ፉክክር ትዕግስት ቱፋ እና ቀነኒሳ በቀለ ውጤት አስመዝግበዋል። የአንደኛነቱ ድል ግን ለምን አልተሳካም? የስፖርት ተንታኝ መልስ አለው።

https://p.dw.com/p/1IcNn
London Marathon 2016 Virgin Money London Marathon
ምስል Reuters/P.Childs

ስፖርት፤ ሚያዝያ 17 ቀን፤ 2008 ዓ.ም.

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሌስተር ሲቲ የዋንጫ ባለቤት የመሆን ዕድሉ እጅግ ሰፍቷል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ባየር ሙይንሽን ዋንጫውን ለመውሰድ ቀጣዩን ጨዋታ ብቻ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ጆዜ ሞሪኒሆ በበጋው ወራት ተጨዋቾችን ገዝተው እንዲያስመጡ 300 ሚሊዮን ፓውንድ ተመድቦላቸዋል።

አትሌቲክስ

እሁድ ሚያዝያ 16 ቀን፤ 2008 ዓ.ም.በለንደን ከተማ በተከናወነው የማራቶን ሩጫ ውድድር በወንድም በሴትም ኬንያውያን አትሌቶች አሸናፊዎች ሆነዋል። ኢትዮጵያ በሴቶች ፉክክር በትዕግሥት ቱፋ በኩል የሁለተኛ ደረጃ ስታገኝ፤ በወንዶች ውድድር በአትሌት ቀነኒሳ በቀለ የሦስተኛነት ደረጃን ይዛለች። ባለፈው ሣምንት በቦስተን እና በሐምቡርግ የማራቶን ውድድሮች በወንድም በሴትም ድል የቀናቸው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በለንደኑ ውድድር ለምን በኬንያውያን ተበለጡ? የሀትሪክ ጋዜጣ ም/ዋና አዘጋጅ እንዲሁም በሬዲዮ እና በጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ምስጋናው ታደሠ የቡድን ሥራ ያለመኖሩ ዋነኛ ሰበብ መኾኑን ገልጧል።

በለንደኑ የማራቶን ሩጫ በሁለተኛነት ያጠናቀቀችው አትሌት ትዕግሥት ቱፋ የገባችበት ሰአት 02:23:03 ነው። ቀነኒሳ በቀለ 02:06:36 በመሮጥ ሦስተኛ ወጥቷል። ኬንያዊው ኤሊዩድ ኪፕቾጌ በ02:03:05 አንደኛ ወጥቷል። ኬንያዊቷ ጀሚማ ሱምጎንግ በአንደኛነት ያጠናቀቀችበት ጊዜ 02:22:58 ነው።

የለንደኑ ማራቶን ትናንት በለንደን ጎዳና ሲከናወን እንግሊዛዊው ስነ-ፈለክ ተመራማሪም ምድርን በእየ 90 ደቂቃው በሚዞረው ዓለም አቀፉ የኅዋ ምርምር ጣቢያ ውስጥ ሆኖ ውድድሩን ተሳትፏል። የስበት ኃይል እጅግ አነስተኛ በሆነበት እና ማናቸውም ቁሶች በሚንሳፈፉበት ኅዋ ውስጥ በስፖርት መሥሪያ የመሮጫ ንጣፍ ላይ ሆኖ ግራና ቀኝ በሸራ በተወጠረ ሰንሰለት ታስሮ የ2 ሰአቱን ሩጫ ተካፍሏል። የለንደን ጎዳናዎች የሩጫ ድባብን ለማምጣትም ከመሮጫ ንጣፉ አጠገብ አይፓድ አስቀምጦ ጎዳናዎቹን እና የሯጮቹን እግሮችም ሲመለከት ነበር።

እንግዲህ በዚህ መልኩ ባደረገው የኅዋ የማራቶን ሩጫ እንግሊዛዊው ጠፈርተኛ ቲም ፒክ የመጀመሪያው የማራቶን ወንድ ሯጭ ተብሎ ስሙ በታሪክ መዝገብ ሠፍሮለታል። የ42 ኪሎ ሜትሩን ሩጫ ኅዋ ላይ ያጠናቀቀበት የ3 ሰአት፤ ከ35 ደቂቃ ጊዜ አስደናቂ ተግባራትን የፈጸሙ ሰዎች በሚካተቱበት ጊነስ ቡክ የተሰኘው መዝገብ ላይ እንዲገባ አስችሎታል። በሴቶች ዘርፍ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2007 ዓመት ኅዋ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሮጥ ስሟ በታሪክ የተመዘገበው አሜሪካዊት ጠፈርተኛ ሱኒታ ዊሊያምስ ናት። የቦስተኑ ማራቶንን ከዘጠኝ ዓመት በፊት ከኅዋ የምርምር ጣቢያ ላይ ሆና በመካፈል ያጠናቀቀችበት የ4 ሰአት ከ24 ደቂቃ ጊዜ በኅዋ ማራቶን በመሮጥ የመጀመሪያዋ ሰው አሰኝቷታል።

እግር ኳስ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ 76 ነጥብ የሰበሰበው መሪው ሌስተር ሲቲ ከቀሪ ሦስት ጨዋታዎቹ ሁለቱን ካሸነፈ መቶ በመቶ ዋንጫውን መውሰዱን ያረጋግጣል። ትናንት ስዋንሲ ሲቲን 4 ለ0 አንገት አስደፍቶ የላከው ስዋንሲ ሲቲ ዘንድሮ የዋንጫው ባለቤት ለመሆን ከእንግዲህ የሚጠበቅበት 5 ነጥብ ብቻ ነው። ቀሪ ጨዋታዎቹ ከማንቸስተር ዩናይትድ፣ ከኤቨርተን እና ከቸልሲ ጋር ይሆናል።

የሌስተር ሲቲ ግብ አዳኙ ጂሚ ቫርዲ ባለፈው ሣምንት በፈጸመው ጥፋት በቀይ ካርድ በመሰናበቱ በትናንቱ ጨዋታ አልተሰለፈም ነበር። ላይስተር ሲቲ በሰፋ ግብ ልዩነት ከማሸነፍ ግን ያገደው ነገር አልነበረም። በ10ኛው ደቂቃ ላይ ተከላካይ በፈጸመው ስህተት ሪያድ ማኅሬዝ ለላይስተር ሲቲ ቀዳሚዋን ግብ አስቆጥሯል። ጂሚ ቫርዲ በሌለበት ጨዋታ የሌስተር ሲቲው ሌዎናርዶ ኢሾዋ ለቀበሮዎቹ ሁለት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ገኖ ወጥቷል። የማርክ አልብሪቶን ግብ ተደምራ ሌስተር ሲቲ በአራት ግብ ተንበሽብሾ ደጋፊዎቹን አስፈንጥዟል።

በፕሬሚየር ሊጉ በሁለተኛ ደረጃ የሚከተለው ቶትንሀም ሆትስፐር ዛሬ ማታ ከከዌስት ብሮሚች አልቢኖ ጋር 35ኛ ጨዋታውን ያከናውናል። እስካሁን 68 ነጥብ አለው። እሱም ቢሆን ዋንጫ የማግኘት እድሉ ቢጠብም ሙሉ ለሙሉ ያከተመለት ግን አይደለም። ዋንጫ ለመውሰድ ከቀሪ 4 ጨዋታዎቹ ሦስቱን አሸንፎ የሌስተር ሲቲን በሦስቱም ጨዋታዎች መሸነፍ መጠበቅ አለበት። ያኔ ላይስተር ሲቲን በአንድ ነጥብ በልጦ ዋንጫውን በእጁ ማስገባት ይችላል ማለት ነው። አለበለዚያ ደግሞ አራቱንም ጨዋታዎች አሸንፎ ሌስተር ሲቲ በሁለት ጨዋታዎች እንዲሸነፍ አጥብቆ መመኘት አለበት።

የኳስ ነገር የሚሆነው አይታወቅም። ኾኖም የሌስተር ሲቲ የዘንድሮ ጥንካሬ እና የተጋጣሚዎቹ ደከም ብሎ መታየት ቶትንሀም ሆትስፐርን ከምኞት እንዳይዘል ሊያደርገው ይችል ይሆናል። ቶትንሀም ሆትስፐር ቀሪ ጨዋታዎቹ ከዌስት ብሮሚች፣ ከቸልሲ፣ ከሳውዝ ሐምፕተን እና ከኒውካስል ጋር ነው።

ከትናንት በስትያ ስቶክ ሲቲን 4 ለ0 ያንኮታኮተው ማንቸስተር ሲቲ ነገ ከስፔኑ ኃያል ሪያል ማድሪድ ጋር ለሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ ይፋለማል። ከነገ በስትያ ደግሞ የጀርመኑ ኃያል ባየር ሙይንሽን የስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድን ይገጥማል።

የባየር ሙይንሽኑ አሠልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ የደርሶ መልስ ግማሽ ፍጻሜውን አሸንፈው ለፍፃሜ በመድረስ ዋንጫውን ለማሸነፍ የቻሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ቀደም ሲል በባርሴሎና ቆይታቸው ለሁለት ጊዜያት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ባለቤት መሆኑን የቻሉት እኚህ ዝነኛ አሠልጣኝ በሁለተኛነት ማጠናቀቅ የሰለቻቸው መሆኑንም ጠቆም አድርገዋል። «ክብር እና ዝናው ለአሸናፊዎች ነው። ለቁጥር አንዶች። ለሁለተኛዎች አይደለም። ለዚያ መፋለም አለብን፤ አንደኛ ለመሆን» ብለዋል።

በሁለት ዓመት ቆይታቸው ቡድናቸው ባየር ሙይንሽንን ለሁለት ጊዜያት ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ቢያደርሱም የድል ምኞታቸውን ግን ቀደም ሲል ገናና ባደረጉት ቡድን በባርሴሎና እና በሪያል ማድሪድ ከእጃቸው ተነጥቀዋል። በቡንደስ ሊጋው ግን በሦስተኛ ዓመታቸው ሦስተኛ ዋንጫቸውን ሊጨብጡ የሚጠብቁት የፊታችን ቅዳሜን ብቻ ነው።

አሠልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ በቡንደስ ሊጋ ቆይታቸው 100ኛው የሚሆነው የቅዳሜ ጨዋታን ካሸነፉ ለሳቸው ሦስተኛ፤ ለሚያሠለጥኑት የባየር ሙይንሽን ቡድን ደግሞ በአራት ተከታታይ የጨዋታ ዘመን አራተኛ ዋንጫ ይኾናል ማለት ነው። እዚያ ስኬት ጫፍ ላይ ለመድረስ ቅዳሜ በሜዳቸው ቦሩስያ ሞይንሽን ግላድባኅን ይገጥማሉ።

ተጋጣሚያቸው ግን በቡንደስ ሊጋው አምስተኛ ደረጃ ይዞ በመጨረስ የሚቀጥለው የውድድር ዘመን የአውሮፓ ሊግ ተሳታፊ ለመሆን ከማለሙ አንፃር በቀላሉ የሚታይ ተፎካካሪ አይሆንም። በዚህም አለ በዚያ ሰውዬው ዓለማችን ውስጥ ከሚገኙ ጥቂት ምርጥ አሠልጣኞች አንዱ በመሆናቸው የቅዳሜው 32ኛ ጨዋታ ባይሳካላቸው እንኳን እስከ ፍፃሜው 34ኛ ግጥሚያ ድረስ አንዱን ማሸነፋቸው የማያጠራጥር ነው።

በስፔን ላሊጋ ስፖርቲንግ ጂዮንን 6 ለ0 ያደባየው ባርሴሎና ደረጃውን በ82 ነጥብ ይመራል። የሻምፒዮንስ ሊግ ተፋላሚው አትሌቲኮ ማድሪድ ተመሳሳይ ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ ልዩነት ብቻ ሁለተኛ ነው። ራዮ ቫሌካኖን 3 ለ0 አሸንፎ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሪያል ማድሪድ ከመሪዎቹ የሚለየው በአንድ ነጥብ ብቻ ነው።

በቀጣዩ የጨዋታ ዘመን በበጋው ወራት ማንቸስተር ዩናይትድን ከሉዊ ቫን ጋል የሚረከቡት አሠልጣኝ ጆዜ ሞሪኒሆ ተጨዋቾችን ገዝተው እንዲያስመጡ 300 ሚሊዮን ፓውንድ ተመድቦላቸዋል ሲል ዴይሊ ስታር የተሰኘው እለታዊ ጋዜጣ ዘግቧል።

የሌስተር ሲቲው የክንፍ ተጨዋች አልጄሪያዊው ሪያድ ማኅሬዝ ለቡድኑ 17 ግቦችን በማስቆጠር እና 11 ግቦችን በማመቻቸት በፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋቾች ማኅበር የዓመቱ ምርጥ ተጨዋች ተብሎ ሽልማቱን ትናንት ለንደን ከተማ ግሮስቬነር ሆቴል ውስጥተቀብሏል። ለሽልማት የታጩት የዌስትሐሙ ዲሚትሪ ፓዬት፣ የቶትንሐሙ አጥቂ ሐሪ ኬን፣ የአርሰናሉ ወሳኝ ሰው ሜሱት ኦትሲል እና አብረውት የሚጫወቱት የቀበሮዎቹ ጂሚ ቫርዲ እና ንጎሎ ካንቴ ነበሩ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

የሌስተር ሲቲው የክንፍ ተጨዋች አልጄሪያዊው ሪያድ ማኅሬዝ
የሌስተር ሲቲው የክንፍ ተጨዋች አልጄሪያዊው ሪያድ ማኅሬዝምስል Reuters/J. Cairnduff
የባየር ሙይንሽን አሠልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ
የባየር ሙይንሽን አሠልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላምስል picture-alliance/dpa/M. Cruz
እንግሊዛዊው ስነ-ፈለክ ተመራማሪ ቲም ፒክ በኅዋ ሲሮጥ
እንግሊዛዊው ስነ-ፈለክ ተመራማሪ ቲም ፒክ በኅዋ ሲሮጥምስል picture alliance/dpa/H. Kaiser
የለንደን ማራቶን አሸናፊዎች፤ ከግራ በኩል ትዕግሥት ቱፋ
የለንደን ማራቶን አሸናፊዎች፤ ከግራ በኩል ትዕግሥት ቱፋምስል Reuters/P.Childs

ኂሩት መለሰ