1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ተወቀሱ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 2 2009

በአሁኑ ጊዜ የኢጣልያ እና የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች የባህር ስደተኞችን ወደ ሚነሱበት ወደ ሊቢያ እየመለሱ ነው። በሜዴትራንያን ባህር ላይ ስደተኞችን ከአደጋ የሚታደጉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም የባህር ስደትን ያበረታታሉ እየተባሉ መወቀሳቸው ቀጥሏል።

https://p.dw.com/p/2hts3
Mittelmeer Küste Libyen Rettungsaktion Flüchtlinge
ምስል Reuters/D. Zammit Lupi

ስደተኞችን የመታደጉ ጥረት እና ወቀሳው

በሜዴትራኒያን ባህር በኩል ወደ አውሮጳ ለመሻገር የሚሞክሩ ስደተኞችን ለመግታት የሚደረገው ጥረት ከቀድሞ ይበልጥ አሁን ተጠናክሯል። የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ስደተኞችን እንዲከፋፈሉ ለቀረበላቸው ጥያቄ ያሳዩት ቸልተኝነት ያስመረራት ኢጣልያ ችግሩን ለመቋቋም የበኩሏን እርምጃ እየወሰደች ነው። ኢጣልያ አሁንም ሊገታ ያልቻለውን የባህር ስደት ለማስቆም በቅርቡ ከሊቢያ ባህር ኃይል ጋር ይበልጥ ተቀራርባ ለመሥራት ወስናለች። በዚሁ መሠረት የኢጣልያ ባህር ኃይል ከሊቢያ መርከቦች ጋር በሊቢያ የባህር ጠረፍ ላይ ቁጥጥር ለማካሄድ እና ለሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎችም የቴክኒክ እና የሎጂስቲክ ድጋፍ ለመስጠት አቅዷል። የጋራው ቁጥጥር እና የእገዛው ዓላማም ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ማስቆም እና ስደተኞችን ጭነው ከሊቢያ የሚነሱ ጀልባዎችን ወደ መጡበት መመለስ መሆኑን ሮም አስታውቃለች። ሮም ኢጣልያ ውስጥ ስደተኞችን ለመርዳት የተቋቋመው ኤጀንስያ አበሻ  የተባለው ድርጅት መሥራች እና ሃላፊ አባ ሙሴ ዘርአይ የአሁኑ እርምጃ  የአውሮጳ መንግሥታት ህገ ወጥ የሚሉትን ስደት ለመግታት ከዚህ ቀደም ያሳለፏቸው ውሳኔዎች ውጤት መሆኑን ለዶቼቬለ ተናግረዋል። 
በአሁኑ ጊዜ የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች በርካታ ስደተኞችን ወደ ተነሱበት አካባቢ በመመለስ ላይ ናቸው። ባለፉት ጥቂት ቀናት የባህር ጠባቂዎች ከ1 ሺህ በላይ ስደተኞችን ወደ ሊቢያ መልሰው ልከዋል። ካለፈው ጥር አንስቶ የሜዴትራንያንን ባህር በጀልባ አቋርጠው ደቡብ አውሮጳ የደረሱ ስደተኞች ቁጥር ወደ 114 ሺህ ይጠጋል። ዓለም አቀፉ የፍልሰት ጉዳዮች ድርጅት እንዳስታወቀው ከመካከላቸው 82 በመቶው ኢጣልያ ነው የገቡት። ድርጅቱ እንደሚለው ሁሉም ለማለት ይቻላል የተነሱት ከሊቢያ ነው። ባለፉት ሰባት ወራት በጉዞ ላይ ሰጥመው ህይወታቸው ያለፈው የጀልባ ስደተኞች ትክክለኛ ቁጥር በውል ባይታወቅም ወደ 2 ሺህ እንደሚደርስ ይገመታል። የባህር ስደቱ ለመቀጠሉ የኢጣልያ መንግሥት እና የአውሮጳ ህብረት በሜዴትራንያን ባህር ላይ ስደተኞችን ከሞት የሚታደጉ የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ይወቅሳሉ። የአውሮጳ ህብረት ድንበር ጠባቂ ድርጅት በምህፃሩ ፍሮንቴክስ እና ኢጣልያ እነዚህን የተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን የህገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎችን ሥራ ያመቻቻሉ፣ ስደተኞች በአደገኛ የባህር ጉዞ ወደ አውሮጳ ለመሰደድ እንዲሞክሩ ያደፋፍራሉ የሚል ክስ አቅርበውባቸዋል። ባለፈው ሳምንት በዚሁ ተግባር ተጠረጥሮ ክስ ስለቀረበበት ሉቬንታ ስለተባለው አንድ የጀርመናውያን የነፍስ አድን መርከብ የሲሲሊዋ የትራፓኒ ከተማ አቃቤ ህግ አምቦርግዮ ካርቶስዮ በሰጡት አስተያየት መርከቧ ሁል ጊዜ ስደተኞችን የመታደግ ሥራ ብቻ አይደለም የምታከናውነው ብለዋል።
«በአንዳንድ ሁኔታዎች በባህር ላይ ሉቬንታ የሚያከናውነው ሥራ አደገኛ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ሰዎችን መታደግ ሳይሆን በሊቢያ ህገ የሰዎች አሻጋሪዎች የሚመጡ ሰዎችን መቀበል ነው።» 
ይህን መሰሉን ወቀሳ በ2016 በርካታ የባህር ስደተኞችን ያስገባችው ጀርመን እና የስደተኞች መተላለፊያ የነበረችው ኦስትሪያም ሰንዝረዋል። ስደተኞችን የምንረዳው በዓለም ዓቀፍ ህግ መሠረት ነው የሚሉት መንግሥታዊ ያልሆኑት ድርጅቶች ክሱን ይቃወማሉ። ኢጣልያ በሜዴትራንያን ባህር ላይ ስደተኞችን የሚታደጉ መርከቦችን ያሰማሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ላወጣችው የስነ ምግባር ደንብ ተገዥ እንዲሆኑ አሳስባለች። በድርጅቶቹ ሥራ ተማርሬያለሁ የምትለው ኢጣልያ መርከቦቻቸው ወደቦቿ እንዳያርፉ እንደምትከለክልም እያስጠነቀቀች ነው። በአሁኑ ጊዜ ከባህር ላይ ስደተኞችን የሚታደጉት ድርጅቶች እና ስደተኞች ለአደጋ የመጋለጣቸው መረጃ ሲደርሳቸው ለኢጣልያ ባህር ኃይል የሚያሳውቁ አበሻ ኤጀንስያን የመሳሰሉ ድርጅቶችም በጅምላ የባህር ስደትን በማበረታታት ጠንካራ ወቀሳ እየቀረበባቸው ነው። አባ ሙሴ ወቀሳውን መሠረት የሌለው የስም ማጥፋት ዘመቻ ይሉታል። 
ፈረንሳይም እንዲሁ ስደተኞች በሜዴትራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮጳ እንዳይመጡ ለመከላከል ሊቢያ ውስጥ ስደተኞች የሚከማቹበት  ማዕከላትን እንደምታቋቋም አስታውቃለች። ማዕከላቱ የሚቋቋሙት ስደተኞች አውሮጳ ለመድረስ እጅግ አደገኛ አማራጮችን ከመውሰድ እንዲቆጠቡ መሆኑን የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮ ባለፈው ሰሞን ተናግረዋል። ወደ አውሮጳ የሚሰደዱት በሙሉ ተገን ለማግኘት አሳማኝ ምክንያት እንደሌላቸው የተናገሩት ማክሮ እነርሱ ወዳሉበት እንሄዳለን ብለዋል። ማክሮ እንዳሉት ማዕከሉን በቅርቡ ለመክፈት ነው ያሰቡት። ይሁን እና ማክሮ የተረጋጋ መንግሥት በሌለባት በሊቢያ የስደተኞች ማከማቻ ማዕከላት ለመስራት ማቀዳቸው ክፉኛ ተተችቷል። አባ ሙሴም እቅዱን ከሚተቹት እና ከሚቃወሙት አንዱ ናቸው።የአውሮጳ መንግሥታት ስደተኞች እንዳይመጡባቸው የሚወስዷቸው የተለያዩ እርምጃዎች ችግሩን በዘላቂነት የሚፈቱ መፍትሄዎች እይደሉም የሚሉ ትችቶች ይሰነዘሩባቸዋል።  አባ ሙሴም ተመሳሳይ አስተያየት ነው ያላቸው።

Mittelmeer Flüchtlinge Rettungsaktion
ምስል Reuters/Marina Militare
Mittelmeer Flüchtlinge Rettungsaktion
ምስል Reuters/Marina Militare
Mittelmeer Küste Libyen Rettungsaktion Flüchtlinge
ምስል Reuters/D. Zammit Lupi

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ