1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስደተኞች እና ዘረኛ ጥቃቶች በጀርመን

ማክሰኞ፣ ሰኔ 7 2008

ጀርመን ስደተኞችን ከዘረኛ ጥቃቶች ባለመከላከል ተወቅሳለች ። ዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው ሐሙስ ባወጣው ዓመታዊ የሰብዓዊ መብት ዘገባ ጀርመን ውስጥ በስደተኞች መጠለያዎች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች እየተባባሱ መሄዳቸውን አስታውቋል ።

https://p.dw.com/p/1J6Wt
Deutschland Düsseldorf Feuerwehr Brand Flüchtlingsunterkunft
ምስል picture-alliance/dpa/R. Vennenbernd

ስደተኞች እና ዘረኛ ጥቃቶች በጀርመን

ከእነዚህ ወንጀሎችም አብዛኛዎቹ ተገቢው ምርመራ እንዳልተካሄደባቸው እና ተገቢ ብይንም እንዳልተሰጠባቸው አምነስቲ በዘገባው ጠቁሟል ።እንደ ዘገባው ይህ የሆነው ቁጥራቸው ከ1.1 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ስደተኞች ጀርመን በገቡበት በጎርጎሮሳዊው 2015 ብቻ ሳይሆን ከዚያም በፊት ጭምር ነው ።ባለፈው መጋቢት ወር ውስጥ ዴር ሽፒግል የተባለው የጀርመን ታዋቂ መፅሄት እንደዘገበው በጎርጎሮሳዊው 2014 በስደተኞች መጠለያዎች ላይ ከተፈጸሙ ጥቃቶች አብዛኛዎቹ መፍትሄ አላገኙም ። እንደዘገባው በዓመቱ በደረሱት 157 ጥቃቶች ላይ ከተካሄዱት ምርመራዎች በ15 ቱ ላይ ብቻ ነው ውሳኔ የተሰጠው ።በዚሁ አመት ከተፈፀሙት ጥቃቶች 107 ቱ አንድም ተጠርጣሪ አልተያዘባቸውም ። 50 ዎቹ ደግሞ ተጠርጣሪዎች ቢኖሩም የ28 ቱ ፋይል ተዘግቷል ። 5 ቱ አሁንም ፋይላቸው ያልተዘጋ ሲሆን ሁለት ደግሞ ፍርድ ቤት አልቀረቡም ።አምነስቲ ከዚህ ቀደም ዘረኝነትን መሠረት አድርገው ከተፈፀሙ ወንጀሎች መካከል በህግ አስፈጻሚዎች ችላ ተብለዋል ካላቸው አንዱን በአሁኑ ዘገባው አስታውሷል ። በኅቡዕ ይንቀሳቀስ የነበረው በምህፃሩ NSU የተባለው አፍቃሪ ናዚ ቡድን እጎአ ከ2000 እስከ 2007 ዓም ድረስ 9 የውጭ ዜጎችን እና አንድ ፖሊስ መግደሉ የተደረሰበት በጎርጎሮሳዊው 2011 ዓም መሆኑን ሕግ አስፈፃሚዎች ስራቸውን በሚገባ አለማከናወናቸው የሚያሳይ ነው ብሏል አምነስቲ ። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የጀርመን ቅርንጫፍ ተጠሪ ሴልሚን ካሊስካን ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ከዘረኝነት ጋር የተያያዙ ወንጀሎች ተዳፍነው የሚቀሩበት ምክንያት በጀርመን ተቋማዊ ዘረኝነት የሚጫወተው ሚና በግልፅ እንዲታወቅ ባለመደረጉ ለዚህም መፍትሄ ባለመፈለጉ ነው ።
« በጀርመን ህግ አስፈፃሚዎች ዘንድ ተቋማዊ ዘረኝነት እንዳለ በግልፅ የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ ። አምነስቲ ኢንተርናሽናል የጀርመን ምክር ቤት በህዳር 2015 በኤን ኤስ ኡ ላይ ተጨማሪ ምርመራ የሚያካሂድ ኮሚቴ እንዲቋቋም ማድረጉን በደስታ ተቀብለናል ። ይሁንና እንዳለመታደል ሆኖ በእኛ አመለካከት ኮሚቴው ተቋማዊ ዘረኝነት ስህተት እንዲፈጠር በማድረግ ረገድ የሚጫወተውን ሚና ግን ደብቆታል ። »
ሴልሚን ካሊስካን ተቋማዊ ዘረኝነትን ምን ማለት እንደሆነ ሲያብራሩም
«ተቋማዊ ዘረኝነት በዋነኛነት የሚታየው በጭፍን ያለምንም ምክንያት አስቀድሞ ውሳኔ ላይ በመድረስ ፣ በድንቁርናና ፈጽሞ ባለማሰብ ነው።ይህም ዘራቸውን ቀለማቸውንና በማህበረሰቡ ውስጥ ስፍራ ያላገኙትን ወገኖች እንዲገለሉ እና በዘረኞች እንዲበደሉ ምክንያት ይሆናል ።»
በጎርጎሮሳዊው 2015 ጀርመን ውስጥ በተገን ጠያቂዎች መጠለያዎች ላይ 1,031 ጥቃቶች መድረሳቸው ተመዝግቧል ። እነዚህ ጥቃቶችም የዛሬ 3 ዓመት ከተፈፀሙት 63 ጥቃቶች ጋር ሲነፃፀሩ በ16 በመቶ አድጓል። አምነስቲ እንዳለው በሃገሪቱ ታሪክ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በዘረኝነት መንስኤ ይህን ያህል ጥቃቶች ደርሰው አያውቁም ።።በዘገባው እንደተመለከተው በሃገሪቱ በተለይ ዘርንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችም በ87 በመቶ ጨምረዋል ። ያም ማለት በ2013 693 የነበረው ይህን መሰሉ ጥቃት በ2015 ወደ 1,295 ከፍ ብሏል።ካትያ አንድሩሽ የአውሮጳ ህብረት የመሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅት የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ ናቸው ። አንድሩሽ ችግሩ በጀርመን ብቻ ሳይሆን በመላው የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት ውስጥ ያለ ነው ይላሉ ። በርሳቸው አስተያየት በጀርመን የሚደርሰው ጥቃት በተገቢው ሁኔታ በመመዝገቡ በሃገሪቱ በስደተኞች ላይ የሚደርስው ጥቃት በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ይረዳል ። ሆኖም በርሳቸው አስተያየት በጀርመን ከፍተኛ ጥቃቶች መመዝገባቸው በሌሎቹ የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት ሁኔታው የተሻለ ነው ማለት አይደለም ።ጀርመንን በመሳሰሉ ሃገራት ችግሩ መኖሩ ይበልጥ ጎልቶ ለመውጣት የቻለው የተሻለ የመረጃ አሰባሰብ ስርዓት ስላለ ነው ሲሉም ይከራከራሉ ።
«ጀርመንን ነጥዬ ለማውጣት አልፈልግም ። ጀርመንን በሚመለከት በወረቀት ላይ የሰፈሩት አሃዞች በርግጥ ከፍተኛ ይመስላሉ ።በቅርብ ጊዜው የአውሮፓ ህብረት የመሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ዘገባ ላይም እነዚሁ አሃዞች አሉ። ሆኖም መጥቀስ የምፈልገው ጀርመንን ጨምሮ ከፍተኛ የሚመስሉ የጥላቻ ወንጀሎች የተመዘገቡባቸው የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት የጥላቻ ወንጀልን በመከላከል እና ስለዚሁም መረጃዎችንም በመሰብሰብ የተሻሉ ሃገራት ናቸው ። ይህ ደግሞ በመሠረቱ ችግሩን እንደችግር ለማየትና መፍትሄ ፍለጋውንም ለመጀመር እኛ ፣ፖሊሲ አውጭዎች ፖለቲከኞች እና ህዝቡም ማወቅ የሚፈልገው ነው ።ስለዚህ በአንድ ሃገር የተፈፀመው ወንጀሉ ቁጥር ከፍተኛ ነው በሌላው ደግሞ ዝቅተኛ ነው ብሎ ዝቅተኛ ቁጥር ከተሰጠባቸው ሃገራት ይልቅ ችግሩ ይበልጥ የሚታየው ከፍተኛ አሃዝ በተመዘገበባቸው ሃገራት ነው መባሉን እቃወማለሁ ። ምክንያቱም እውነታው በተቃራኒው ሊሆን ይችላል ።»
ለመሆኑ በአውሮጳ እየተባባሰ የሄደውን ጥላቻ ያስከተለው ወንጀልን ለመከላከል በአውሮጳ ህብረት የመሠረታዊ ሠብዓዊ መብቶች ድርጅት በኩል ምን ተደርጓል? ድርጅቱ በመፍትሄነት የሚያቀርበው ሃሳብስ ምን ይሆን ? ለዚህ ጥያቄ አንድሩሽ የሰጡትን መልስ ወደ ኋላ ላይ እንሰማለን ለአሁኑ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የጀርመን ቅርንጫፍ ሃላፊ በተለይ በጀርመን የተባባሰውን ጥላቻ እና ዘረኝነት ያስከተለውን ወንጀል ለመከላከል ቢወሰዱ ያላቸውን እርምጃዎች እናስቀድም ።በባለፈው ሳምንቱ ዘገባው በጀርመን ፀረ የውጭ ዜጎች ወንጀል በቅርብ ዓመታት መባባሱን የገለፀው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው ዓመት እንደታየው የጀርመን ህዝብ ስደተኞች በራቸውን ከፍተው ከተቀበሉት አውሮጳውያን አንዱ መሆኑን ሳያነሳ አላለፈም ። አምነስቲ በስደተኞችና በውጭ ዜጎች ላይ ጥቃት እንዳይደርስ አስቀድሞ አለመከላከልና ከደረሰም በኋላ አብዛኛዎቹን ተከታትሎ አጥፊዎችን ያለ መቅጣት መንስኤ ነው በሚለው ተቋማዊ ዘረኝነት ላይ ልዩ ትኩረት እንዲደረግ አሳስቧል ።
« እኛ እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል መንግስት በፀጥታ ባለሥልጣናትን ሥራ ውስጥ ተቋማዊ ዘረኝነት የሚጫወተውን ሚና ያለማቋረጥ ማጣራት እንዳለበት በጥብቅ እናሳስባለን ።በኛ አመለካከት ጉዳዩ በሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ላይ በሙሉ ገለልተኛ ምርመራ ማካሄድ የመጀመሪያው አስፈላጊ እርምጃ ነው ።»
የጀርመን የፍትሕ ሚንስትር ሀይኮ ማስ መስሪያ ቤታቸው የአምነስቲን ዘገባ መርምሮ አስፈላጊውን ርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል። በውጭ ዜጎች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ችላ በማለት እና በጉዳዩ ላይ ዓይኑን በመጨፈን የተወቀሰው የጀርመን ፖሊስ ግን ወቀሳውን ሃሰት ሲል አስተባብሏል ። ። መሥሪያ ቤታቸው በርግጥ በሰው ኃይልም ሆነ በአንዳንድ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ችግር ቢኖርበትም የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን ግን ችላ እንደማይል የጀርመን ፖሊስ ህብረት ሊቀ መንበር ራይነር ቬንድት ተናግረዋል ።ሊቀመንበሩ በጀርመን ትልቁ የሰብዓዊ መብት ድርጅት አምነስቲ ሳይሆን ፖሊስ ነው ሲሉም ተከራክረዋል ። የአውሮጳ ህብረት የመሠረታዊ ሠብዓዊ መብቶች ድርጅት የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ አንድሩሽ በበኩላቸው ችግሩ አዲስ እንዳይደለ አስታውሰው ችግሩን ለመከላከል በአውሮጳ ህብረት ደረጃ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል ።
«ችግሩን መከላከል የማንችል አንዳልሆንን መጥቀስ እፈልጋለሁ ። ይህ የአውሮጳ ህብረት ለዓመታት ሲከላከለው የቆየ ጉዳይ ነው ። በአውሮፓ ህብረት ደረጃ ጥላቻ ያስከተላቸውን ወንጀሎች መከላከል የሚያስችሉ ጠንካራ ህጎች አሉ ። እነዚህም ዘረኝነትን የውጭ ዜጎች ጥላቻን በሥራ ቅጥር እና በሥራ ቦታ የሚደርስ አድልዎን መከላከል የሚያስችሉ ናቸው ። እናም ይህ ጉዳይ ችላ የተባለ አይደለም ።»
በአንድሩሽ አስተያየት ወንጀሉን ለመከላከል የተሻለ መረጃ ያስፈልጋል ። በአውሮጳ ህብረት የሚፈፀሙ ጥላቻ ያስከተላቸው ወንጀሎች በርሳቸው አባባል መመዝገብ አለባቸው ። ምን ያህል ጥላቻ ያስከተላቸው ወንጀሎች እንደተፈፀሙ ካልታወቀ ችግሩን መከላከል አዳጋች ነው ይላሉ።እርሳቸው እንደሚሉት በውሮጳ በርካታ መሰል ወንጀሎች ተፈጽመዋል የሚል ስሜት አለ ይሁንና ይህን የሚያረጋግጡ አሃዛዊ መረጃዎች ግን የሉንም ።የአሃዛዊ መረጃዎቹ መሰብሰብ ደግሞ ፖሊሲ ለማውጣት ፖሊሲ አውጭዎችንም ሥራቸውን በአግባቡ ላከናወናችሁም ብሎ ለመውቀስ አስፈላጊ ነው ባይ ናቸው ከዚህ ሌላ አንድሩሽ ፖሊሶችን ማሰልጠን ፣ ከተበዳዮቹ ጋር እለት በዕለት የሚገናኙ አካላት ተበዳዩን በተገቢው መንገድ እንዲያስተናግዱ እና የጥላቻ ወንጀልን ለይተው እንዲያውቁ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል ።

Deutschland Brand in künftiger Flüchtlingsunterkunft Ebeleben
ምስል picture-alliance/dpa/S. Kahnert
Deutschland Brand Flüchtlingsunterkunft Hafenstraße in Lübeck
ምስል picture alliance/dpa/R. Rick
Deutschland Berlin PK Amnesty zu zu rassistischer Gewalt
ምስል picture-alliance/dpa/K. Nietfeld
Brand in Asylbewerberunterkunft in Herxheim
ሴልሚን ካልስኪንምስል picture-alliance/dpa

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ