1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለጡት ካንሰር ግንዛቤ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 15 2009

በጎርጎሪዮሳዊዉ 2012 ዓ,ም የዓለም የጤና ድርጅት ባካሄደዉ ቅኝት 14 ሚሊየን አዲስ ሰዎች በካንሰር መያዛቸዉን ይፋ አድጓል።

https://p.dw.com/p/2RgvR
DW Shift BreastIT

የጡት ካንሰር

በተጠቀሰዉ ዓመት ብቻም በካንሰር ሕይወታቸዉን ያጡት ሰዎች ቁጥር 8,2 ሚሊየን ነዉ። የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለዉ በቀጣይ ዓመታትም በካንሰር የሚያዙ ሰዎች ቁጥራቸዉ እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችል የሚያመላክቱ አዝማሚያዎች እየታዩ ነዉ።

ወንዶች በብዛት በሳንባ፣ በዘር ፍሬ፣ ትልቁ አንጀት፣ በሆድ እና በጉብት ካንሰር እንደሚጠቁ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃዎች ያመለክታሉ። በተመሳሳይ ሴቶችን የሚያጠቁት ደግሞ የጡት፤ የትልቁ አንጀት፤ የሳንባ፣ የማሕፀን በር እና የሆድ ካንሰር ናቸዉ በቅደም ተከተል። ሰዎችን ለካንሰር ከሚያጋላጡ መሠረታዊ ምክንያቶች፤ መጠን ያለፈ ዉፍረት፤ ፍራፍሬ እና አትክልቶችን በበቂ መጠን አለመመገብ፤ በቂ የሰዉነት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ትንባሆ ማጨስ እና አልክሆን መጠጥን ማዘዉተር በግንባር ቀምትነት ይጠቀሳሉ። 

የጡት ካንሰር በበለፀገዉም ሆነ በማደግ ላይ በሚገኘዉ ዓለም ሴቶችን ከሚያጠቁ የካንሰር ዓይነቶች ግንባር ቀደሙ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅትም ሆነ የዓለም የካንሰር ምርምር ተቋም መረጃዎች በግልፅ ያመለክታሉ። ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸዉ ሃገራት ዉስጥ የጡት ካንሰር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተስፋፋ የመጣ መሆኑን በመጠቆምም፤ የዓለም የጤና ድርጅት ለዚህም ዋነኛዉ ምክንያት የከተሞች መስፋፋት፤ የሰዎች የአኗኗር ዘይቤ መለወጥ፤ እንዲሁም የምዕራባዉያንን የአኗኗር ስልት መከተል እንደሆነም ይተነትናል። ይህን ዘርዘር አድርገን ስንመለከት፤ የኑሮ ሁኔታ መለወጥ አመጋገብ እና እንቅስቃሴን በስፋት ይመለከታል። የታሸጉ ምግቦችን ማዘዉተሩ፣ ፋስት ፉድ ወይም ሰዎች ቤታቸዉ አብስለዉ ከሚመገቡት ይልቅ በየቦታዉ ገዝተዉ የሚመገቧቸዉ ጊዜ አመጣሽ ምግቦች፣ የመጓጓዣዉን ስልት ሁሉ መመልከት ያሻል።

በበለፀገዉ ዓለም የጡት ካንሰር በሕይወት ላይ ሊያስከትል የሚችለዉ አደጋ እንዲቀንስ የረዳዉ ከመታመም በፊት የሚደረጉ ምርመራዎች ናቸዉ። እንዲህ ያለዉን ቅድመ ካንሰር ምርመራ ዉሱን አቅም ባላቸዉ በማደግ ላይ ባሉት ወይም ደሀ በሚባሉት ሃገራት ስለማይደረግም ሰዎች ወደ ህክምና የሚሄዱት በሽታዉ ስር ከሰደደ በኋላ ይሆንና ሕይወት የማትረፍ ዕድሉን ያመነምነዋል። ለዚህም ነዉ አስቀድሞ ምርመራ ማድረጉ በሽታዉ ሳይባባስ እንዲደረስበት ስለሚረዳ፤ አማራጭ የሌለዉ የመከላከያ ርምጃ መሆኑ በአጽንኦት የሚገለፀዉ። የጡት ካንሰር ምርመራ ለማድረግ ጥቅም ላይ ከዋሉ መሣሪያዎች እስካሁን ትልቅ ዉጤት በማስመስገብ የሚደነቀዉና የሚመከረዉ ማሞግራፊ በተሰኘዉ መሣሪያ የሚደረገዉ ምርመራ ነዉ። በዚህ መሣሪያ አማካኝነት በብዙ መቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሴቶች በተደረገ ቅድመ ካንሰር ምርመራና ክትትል 20 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች በጡት ካንሰር ሰበብ ሕይወታቸዉን ከማጣት እንደዳኑ በርሊን የሚገኘዉ ስጋቶችን የሚከታተለዉ የሃርዲንግ ተቋም ጥናት አመልክቷል። ፕሮፌሰር ጌርድ ጊገርንሰር የተቋሙ ባልደረባ ናቸዉ።

Mammographie
የማሞግራፊ ምርመራምስል Colourbox

«እንደማሞግራፊ ምርመራ ይህን ሊመረምር የሚችል ጥሩ የመመርመሪያ ስልት የለም። ወደ600 ሺ የሚሆኑ ሴቶች ናቸዉ በዚህ በነሲብ በተመረጠዉ የምርመራ ሙከራ እንዲሳተፉ የተደረገዉ። ዉጤቱ ደግሞ በሌላ በየትም ቦታ ቢደረግ ሊገኝ የማይችል ነዉ የሆነዉ።»

 በእርግጥ ይህ ብዙ ገንዘብ የሚጠይቅ ምርመራ መሆኑ ይታወቃል። በተለይ እንደኢትዮጵያ ባሉ ሃገራት እንዲህ ያለዉን መመርመሪያ መሣሪያ በየሃኪም ቤቱ ማግኘት የሚቻል አይሆንም። ግን ደግሞ ቅድመ ምርመራዉን ማድረጉ ዛሬ በየጊዜዉ የሰዎችን ሕይወት እንደ ዋዛ ከሚቀጥፈዉ የጡር ካንሰር ከሚያስከትለዉ ጉዳት ራስን የመከላከያዉ ዋነኛ መንገድ መሆኑ አያጠያይቅም። ከዚህ ቀደም በዚሁ ዝግጅታችን ያነጋገርናቸዉ በአዲስ አበባ የጥቁር አንበሳ ሃኪም ቤት የጨረር ሕክምና ኃላፊ ዶክተር ወንድማገኝ ጥግነህ፤ የማሞግፊ ምርመራ የማግኘት ዕድሉ ባይኖርም እያንዳንዷ ሴት በየቤቱ በግሏ ልታደርገዉ የምትችለዉ እንዳላት ነግረዉናል።

የጡት ካንሰር የሴቶች ችግር ብቻ ነዉ ብለዉ ያስቡ ከሆነ ተሳስተዋል። እንደሴቶቹ አይሁን እንጂ ወንዶችም ለዚህ ሊጋለጡ እንደሚችሉ በተለያዩ ጊዜያት የወጡ መረጃዎች እና የህክማናዉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ስላለዉ ዶክተር ወንድማገኝ እንዲህ ብለዉን ነበር፤

የአንድ ሴት ለጡት ካንሰር የመጋለጥ ዕድል ከፍ የሚያደርገዉ ምን ይሆን? ዶክተር ወንድማገኝ ጥግነህ ሰዎች ሊያስተዉሉት የሚገባ ያሉት የመጋለጥ ዕድል ዘርዝረዋል።

Symbolbild - Brustkrebs
ምስል Getty Images/J. Sullivan

በየዓለመቱ ጥቅምት ወር ላይ ሰዎች የጡት ካንሰርን ለመከላከል ሊያደርጉ የሚገባቸዉን ቅድመ ጥንቃቄ አስመልክቶ በተለያዩ ሃገራት የማስተማሪያ እና ማስገንዘቢያ መድረኮችን ማዘጋጀት የተለመደ ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥም ላለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት ይህ እንቅስቃሴ በየዓመቱ ሲደረግ ታይቷል። እኛም በዚሁ ዝግጅት መዘገባችን ይታወስ ይሆናል። ዘንድሮዉ ግን ከዚህ ቀደም በአደባባይ ይደረጉ የነበሩት ስለጡት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴዎች በወቅቱ የሀገሪቱ ሁኔታ ተገትተዉ፤ በመገናኛ ብዙሃን ዝግጅቶች ብቻ እንደሚሸፈን መወሰኑን ለመረዳት ችለናል። የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ማኅበረሰብ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር የትናየት አበበ ስለዘንድሮዉ ዝግጅት አብራርተዋል።

የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት ለጡት ካንሰርም ሆነ ለሌሎች የካንሰር የጤና እክሎች ከመታመም አስቀድሞ የካንሰር ቅድመ ምርመራ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነዉ። እነሱ እንደሚሉትም ማንኛዉም ዓይነት እብጠት ወይም ቲዩመር በትንሽነቱ እና በተወሰነ አካባቢ ብቻ ባለበት ወቅት ማከሙ ይቀላል፤ የመዳን ዕድሉም ከፍተኛ ይሆናል። አመጋገብ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ፤ ክብደትን መቆጣጠር፣ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ፣ በተቻለ መጠን ካሰቡበት ብዙዎች ሊያደርጉት የሚችሉት ቀላሉ ካንሰርን መከላከያ እና ጤንነት የመጠበቂያዉ መንገድ ነዉ።

 ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ