1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢራኑ የፖለቲካ ተንታኝ ሳዴግህ ዚባካላም የዶይቼ ቬለ የመናገር ነፃነት ሽልማትን አሸነፈ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 25 2010

ዶይቼ ቬለ የ2018ቱን  የመናገር ነፃነት ሽልማት ለኢራኑ የፖለቲካ ሳይንቲስት ሳዴግህ ዚባካላም ሰጥቷል ። በመጪው ሰኔ 5 ቀን 2010 ዓ.ም. በቦን ከተማ በሚካሔደው ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን የውይይት መድረክ (Global Media Forum) አሸናፊው ሳዴግህ ዚባካላም ሽልማቱን ከዶይቼ ቬለ ዋና ዳይሬክተር ፒተር ሊምቡርግ እጅ ይቀበላል። 

https://p.dw.com/p/2x5Qz
Iran Sadeq Zibakalam, Politikwissenschafter
ምስል Imago/Xinhua

በቴህራን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ሳዴግህ ዚባካላም በኢራን አንቱታን ካተረፉ የፖለቲካ ተንታኞች አንዱ ነው። ተንታኙ በቅርቡ በአገሪቱ ተቀስቅሶ በነበረው አለመረጋጋት ዙሪያ ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረገው ቃለ-መጠይቅ የኢራንን መንግሥት በመተቸቱ ባለፈው ሚያዝያ ወር የ18 ወራት እስራት ተፈርዶበት ነበር። እስካሁን ያልታሰረው ሳዴግህ ዚባካላም በጉዳዩ ላይ ይግባኝ ጠይቋል። 

ሳዴግህ ዚባካላም ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው የሲቪክ ማኅበራት ተወካይ መሆን ችሏል።  በተደጋጋሚ ወግ አጥባቂ ከሆኑ የመንግሥቱ ተወካዮች እና ደጋፊዎች ጋር ሙግት በመግጠም የሚታወቅ ሲሆን የኢራን የኑክሌር መርኃ-ግብርን ጨምሮ ስሱ በሆኑ የአገር ውስጥ እና የውጭ ፖሊሲዎች ላይ በአደባባይ አስተያየት ሰጥቷል። 
ዚባካላም ከጎርጎሮሳዊው 1970ዎቹ ጀምሮ በለውጥ አራማጅነቱ የሚታወቅ ነው። በ1974 ዓ.ም. ትምህርቱን በዩንይትድ ኪንግደም ሊያጠናቅቅ ገደማ ለጉብኝት ወደ ትውልድ አገሩ ኢራን ብቅ ባለበት በቀድሞው የአገሪቱ ንጉስ ሻሕ የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውሎ ነበር። በወቅቱ "መንግሥቱን በሕቡዕ ለመጣል አሲሯል" እንዲሁም "ፕሮፖጋንዳ" አሰራጭቷል የሚል ክስ ቀርቦበት ነበር። 

የዶይቼ ቬለ ዋና ዳይሬክተር ፒተር ሊምቡርግ "የተገደበ ሐሳብን የመግለፅ ነፃነት እና ፕሬስ ባለባቸው አገራት የሚኖሩ ዜጎችን መድረስ እና ተዓማኒ መረጃ ማቅረብ የዶይቼ ቬለ ዋንኛ ዓላማ ነው። ከእነዚህ አገሮች አንዷ ሰዎች መረጃ ከማግኘት ሥልታዊ በሆነ መንገድ የታገዱባት ኢራን ነች። የ2018 የመናገር ነፃነት ሽልማት በኢራን የሲቪል ማኅበረሰብን ለማበረታታት እና ዚባካላም ሐሳቡን በመግለፁ ምክንያት የከሰሰውን የኢራን መንግሥት ለመተቸት የታቀደ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። ዋና ዳይሬክተሩ የዶይቼ ቬለ መረጃዎች ገደብ ቢጣልባቸውም እንኳ ተቋሙ ለኢራናውያን ዜና እና መረጃ ለማቅረብ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። 
"መንግሥታችን እንደ ኢራን ከመሰሉ አገራት ጋር በሚያደገው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መረጃን ለመገደብ የሚያደርጉትን ያላቋረጠ ጥረት ሊገመግም ይገባል የሚል ሐሳብ አለኝ" ሲሉ በአፅንዖት ተናግረዋል። 

dw freedom Prof Sadegh Zibakalam

ሳዴግህ ዚባካላም በበኩሉ "የዶይቼ ቬለ የመናገር ነፃነት ሽልማትን ማሸነፍ ታላቅ ክብር እና ደስታ ነው። በኢራን ከመንግሥቱ የተለየ አስተያየት ማንጸባረቅ ወንጀል ነው። ይኸ የመናገር ነፃነትን ለአመታት የመታገል ልምድ ያላት አገሬ መራር እውነት ነው። ይኸ ሽልማት የሚገባቸው ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እንዲከበር የሚሟገቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢራናውያን አሉ" ሲል ተናግሯል። 

የዶይቼ ቬለ የመናገር ነፃነት ሽልማት ሰብዓዊ መብት እና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እንዲከበር የተለዩ ሥራዎች የሰሩ ግለሰቦች እና ተቋማትን እውቅና ይሰጣል። በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም. በእስር ላይ የሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ጦማሪ ራይፍ ባዳዊ የመጀመሪያው የሽልማቱ አሸናፊ ነበር። በ2016 ዓ.ም ይኸው ሽልማት ለቱርካዊው ጋዜጠኛ ሴዳት ኢርጊን ተበርክቶለታል። ባለፈው አመት የዋይት ሐውስ ዘጋቢዎች ማኅበር የሽልማቱ አሸናፊ ሆኗል።

ዘንድሮ ሽልማቱ ይፋ የተደረገበት ወቅት ከዶይቼ ቬለ 65ኛ አመት ጋር ተገጣጥሟል። ዶይቼ ቬለ የመጀመሪያውን ሥርጭት ያከናወነው በጎርጎሮሳዊው ግንቦት 3 ቀን 1953 ዓ.ም. ነበር። 
ግንቦት  3, 2017

www.dw.com/freedom