1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሪክ ማቸር መዲና ጁባ ተመለሱ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 18 2008

የማቸር ጁባ መግባት ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት ለመመሥረት የተደረገዉን ሥምምነት ገቢራዊ ለማድረግ ከሚያስፈልጉ ቅድመ-ጉዳዮች ዋነኛዉ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1IcvC
Südsudan Oppositionsführer Riek Machar
ምስል picture-alliance/dpa/P. Dhil

[No title]

ላለፉት ሁለት ዓመታት የደቡብ ሱዳን አማፂ ቡድንን የመሩት ሪክ ማቸር ዛሬ የሐገሪቱ ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት ምክትል ፕሬዝደንት ሆነዉ ቃለ መሐላ ፈፅሙ።ማቻር የሚመሩት አማፂ ቡድን ከፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር መንግሥት ጋር ባለፈዉ ነሐሴ በተፈራረመዉ ዉል መሠረት ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት መመሥረቱ ሁለት ዓመት ያስቆጠረዉን ጦርነት ለማስቆም እንደ ሁነኛ እርምጃ የሚታይ ነዉ።

እንዲያም ሆኖ ማቻር ዛሬ ጁባ የገቡት የሠላም ስምምነቱ ለተደጋጋሚ ጊዜ ገቢራዊ ሳይሆን ከቀረ በኋላ መሆኑ ይታወቃል። ማቻር ዛሬ ከኢትዮጵያዋ ጋምቤላ ከተማ ወደ ጁባ የተጓዙት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አዉሮፕላን መሆኑ ተዘግቧል። የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይላት የፈረሙትን ስምምነት ካላከበሩና ማቻርም እስካለፈዉ ቅዳሜ ድረስ ጁባ ካልገቡ ለጋሽ መንግሥታት እርምጃ ለመዉስድ አስጠንቅቀዉ ነበር።

Südsudan Oppositionsführer Riek Machar
ምስል Reuters/J. Solomun

ማቸር ከዚሕ ቀደም በተቆረጠዉ ቀን ማለት ባለፈዉ ሳምንት ሰኞ ወደ ጁባ ያልሄዱት አስከትለዉ በሚገቡት ጦር ብዛትና በታጠቀዉ የመሳሪያ ዓይነት ሰበብ ከመንግሥት ጋር ባለመግባባታቸዉ ነበር። ባለፈዉ ነሐሴ በተፈረመዉ ዉል መሠረት የማቻር ዘቦች ከ20 አውቶማቲክ ጠመንጃዎችና በሮኬት ከሚወነጨፍ ፈንጂ ዉጪ ሌላ ጦር መሳሪያ መታጠቅ የለባቸዉም።

መንግሥት በበኩሉ የአዉቶማቲኩ ጠመንጃ ቁጥሩ በ7 መገደብ አለበት ሲል ነበር ። በደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ጦርነት በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች መገደላቸዉና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸዉ መፈናቀላቸዉና ወደ ጎረቤት ሃገር መሰደዳቸዉ ይታወቃል።

ሥለ ደቡብ ሱዳን ሠላም የናይሮቢ ወኪላችንን አነጋግረነዉ ነበር።

ፋሲል ግርማ

ነጋሽ መሐመድ