1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መፍትሔ አልባው የኢትዮጵያውያን ፍልሰት

ዓርብ፣ ሚያዝያ 20 2009

ሳዑዲ አረቢያ ቀን እየቆጠረች ነው። አገሪቱ የሰጠችው የሶስት ወራት ምሕረት ሲጠናቀቅ የመኖሪያና የስራ ፈቃድ የሌላቸውን መጠረዝ ትጀምራለች። ሕጋዊ የመኖሪያም ይሁን የሥራ ፈቃድ የሌላቸው ብዙ ኢትዮጵያውያን ግን በመጪው ሰኔ 20 የሚጠናቀቀውን የምህረት አዋጅ ተጠቅመው ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ፈቃደኛ አይደሉም።

https://p.dw.com/p/2c6Qx
Symbolbild Flüchtlingskatastrophe Mittelmeer
ምስል imago/Anan Sesa

ስደት እና የኢትዮጵያ ወጣቶች

ከኢትዮጵያ ተነስቶ የሰሐራ በርሐን በማቋረጥ ግብፅ የገባው ኢትዮጵያዊ ደግሞ የኋላ የቀሩት ጓደኞቹ ሁኔታ አሳስቦታል። ወጣቱ ሰሐራ በርሐን በማቋረጥ ላይ የነበሩ ጓደኞቹ በሕይወት ይኑሩ፤ ይሙቱ አያውቅም። የመጤ-ጠል (ጥቃት) ጊዜ እየቆጠረ በሚያምሳት ደቡብ አፍሪቃ የሥራ ፈቃድ ማግኘት ፈታኝ ሆኗል። በሳዑዲ-አረቢያ፤የሰሐራ በርሐ አሊያም በደቡብ አፍሪቃ በኢትዮጵያውያኑ ላይ አንዳች በደል ሲፈጸም ኢትዮጵያውያን በደቦ ይቆጣሉ። ያወግዛሉ፤የስደት አስከፊነትም ይደሰኮራል። ቁጣው እና ውግዘቱ ግን በተለይ ባለፉት አስር አመታት የበረታውን የኢትዮጵያውያንን ስደት  የሚገታ አይመስልም።

መቀመጫውን ለንደን ያደረገው ዓለም አቀፉ የእድገት ጥናት ተቋም በጎርጎሮሳዊው 2012 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ጥናት ሥራ አጥነት በከተማ፤ የእርሻ መሬት እጦት ደግሞ በገጠር ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን ወደ ስደት የሚያንደረድሯቸው ምክንያቶች ናቸው ሲል አትቶ ነበር። ጥናቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች ቁጥር ከፍተኛ እድገት ቢያሳይም የሥራ እድል ፈጠራው ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ሲልም ተችቷል።

ወጣቱ ተመራማሪ ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ ፍልሰትን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  አስከ አውሮጳ ድረስ ተምሯል። በጀርመኗ የኦልደንበርክ ከተማ የሚገኘው የካርል ፎን ኦስዬትስኪ ዩኒቨሲቲ የሚያስተባብረውን በፍልሰት እና በባህሎች ግንኙነት ላይ የሚያተኩር ትምህርት ካጠናቀቀ በኋላ የመመረቂያ ሥራውን በደቡብ አፍሪቃ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን አድርጓል። ዮርዳኖስ ጥናቱን ለመስራት ኢትዮጵያውያኑ የሚሰሩትን እየሰራ ለወራት ቆይቷል። በጥናቱ ግኝት መሰረት ከደቡብ ኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፍሪቃ የተሰደዱት ዜጎች ምክንያት አንገብጋቢ የሥራ እና የገቢ እጦት ብቻ አይደለም።

Titel: Yordanos Almaz SeifuAutor/Copyright:Yordanos Almaz Seifu, 2017 via Eshete BekeleYordanos Almaz SeifuYordanos Almaz Seifu
ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉምስል DW/E. Bekele

በደቡብ አፍሪቃ ብቻ ሳይሆን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እና የአውሮጳ አገራት በአደገኛ መንገድ የሚሰደዱ ወጣቶች ከሥራ እጦት በተጨማሪ በአገራችን እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተቆጠርን ሲሉ ያማርራሉ። በተሰማሩባቸው የሥራ ዘርፎች ፍትሐዊ ውድድር አለመኖር የሚያማርራቸው ስደተኞች የሚመርጡት የጉዞ መንገድ ግን ሁልጊዜም ሕጋዊ እና ከአደጋ የጸዳ አይደለም።

የፍልሰት ጉዳይ ሲነሳ በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት እንደተስተዋለው አሊያም በሰሐራ በርሐ እንደተፈጠረው አይነት አንዳች ችግር ሲፈጠር መንግሥት ይወቀሳል። መንግሥትም ትኩሳቱ ሲበረታ «ችግሩን እፈታለሁ፤ጥናት ሰርቻለሁ፤ ሕገ ወጥ ደላሎችን እቀጣለሁ» ሲል ቃል ይገባል። ሥር የሰደደው  ችግር ግን እንዲህ በቀላሉ የሚፈታ አይመስልም። ዮርዳኖስ በጥናቱ ካገኛቸው አስተዛዛቢ ገፊ ምክንያቶች አንዱ ኢትዮጵያውያኑን ወደ ደቡብ አፍሪቃ የሚሸኙት የኃይማኖት መምህራን «ርዕይ» የሚሉት ይገኝበታል።

ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ የመመረቂያ ጥናቱን ከጉዞ ማስታወሻዎቹ ጋር አሰናኝቶ በአዲስ አበባ ለንባብ አብቅቷል። ዮርዳኖስ ጥናቱን ለመስራት ወደ ደቡብ አፍሪቃ ባቀናበት ወቅት ኢትዮጵያውያኑ በውስጣቸው ያመቁትን «ብሶት እና የፍልሰት ውጣ ውረድ» አጋርተውታል። «መንገደኛ» የሚል ርዕስ የተሰጠው እና ባለፈው ሰኞ የተመረቀው መፅሐፍ 336 ገጾች እና አራት ምዕራፎች አሉት። በደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች «አደራ አለብኝ» የሚለው ዮርዳኖስ በመፅሐፉ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የሚደረጉ ውይይቶች ላይ የበኩሉን አስተዋፅዖ ለማድረግ አቅዷል። የፍልሰት ጉዳይ ግን እንዲህ በአንድ ግለሰብ ጥረት ብቻ የሚፈታ እንዳልሆነ ዮርዳኖስ ይወተውታል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ