1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርት

ጉዞ ከኬፕታውን እስከ ካይሮ 

ዓርብ፣ ሰኔ 30 2009

«አንድ ጊዜ አፍሪቃን ከጫፍ እስከ ጫፍ ተጉዛ ማየት ትልቁ ምኞቴ ነበር» ትላለች የዛሬው የወጣቶች ዓለም እንግዳችን መስከረም ኃይሌ። ከደቡብ አፍሪቃ -ኬፕ ታውን ተነስታ ግብፅ- ካይሮ ድረስ ተጉዛለች። 

https://p.dw.com/p/2gA2r

Vom Kapstadt nach Kairo
ምስል M. Haile

ጉዞ ከኬፕታውን እስከ ካይሮ 

አላማቸው በትንሽ ገንዘብ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እየተጓዙ አዲስ ነገር ማየት ወይም አገር መጎብኘት ነው። በእንግሊዘኛ „backpackers“ ተብለው ይጠራሉ። ለጉዞ የሚያስፈልጋቸውን ነገር አንድ ሻንጣ ውስጥ ከተው እና ጀርባቸው ላይ አዝለው ስለሚጓዙ ነው።  ዛሬ በካናዳ ሞንትሪያል የምትኖረው መስከረም ኃይሌ ከእነዚህ አይነት ተጓዞች አንዷ ናት። አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችው መስከረም ትምህርቷን የተከታተለችው ሁለተኛ ሀገሬ በምትላት ህንድ ሀገር ነው።  ከዛም  እየተዘዋወረች ብዙ ሀገሮችን ያየች ቢሆንም ትልቅ ህልሟ ግን አፍሪቃን ከጫፍ እስከ ጫፍ መጓዝ ነበር። መስከረምም ይህንን ህልሟን እውን ለማድረግ የወሰነችው በጎርጎሪዮሳዊው 2008 ዓም ነው። ግን ይህን ውሳኔዋን ተግባራዊ የማድረጉ ጉዳይ በዚያን ጊዜ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ለጡት ካንሰር ህክምና ላይ ይገኙ በነበሩት እናቷ የጤና ሁኔታ ላይ ጥገኛ ነበር። ህይወት አጭር ነው ብላ የምታምነው መስከረም ከእናቷ ጋር የተወሰነ ጊዜ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ካሳለፈች እና እናቷም ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ እሷም ከነበረችበት ከኬፕ ታውን ረዥሙን ጉዞዋን ጀምራለች። 16 ድንበሮችን አቋርጣ ካይሮ ለመድረስ የፈጀባት ጊዜ ዘጠኝ ወር ሲሆን፤ ይህም በመሀል እናቷን ለማስታመም ወደ ኢትዮጵያ መሄድ እና መቆየት ስለነበረባት ነው። መስከረም እናቷ ከአረፉ በኋላ የጀመረችውን ጉዞ የመቀጠሉ ውሳኔ ቀሪዎቹን ቤተሰቦቿን ይበልጥ አስጨንቋቸው ነበር። እሷ ግን በውሳኔዋ ፀንታ ቀጥላለች። ጉዞው አደገኛ ሆኖ ባታገኘውም ፈታኝ ግን ነበር ትላለች። መስከረም ኃይሌ በወጣትነቷ ከኬፕ ታውን  ተነስታ  ካይሮ  ድረስ ስላደረገችው የጀብድ ጉዞ ማዳመጫውን ተጭነው መስማት ይችላሉ።
ልደት አበበ
አርያም ተክሌ

Vom Kapstadt nach Kairo
መስከረም የጀብድ ጉዞ ያስደስታታልምስል M. Haile