1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሊቢያ ከቃዛፊ መገደል በኋላ

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ጥቅምት 14 2009

አካባቢዉን የወረሩት ሚሊሺያዎች ቃዛፊን ከጉድባ ዉስጥ አወጧቸዉ።ቆስለዋል።ያዩ እንደሚሉት ማራኪዎቹ ሰዉዬዉን መኪና ላይ ሲያወጧቸዉ ሌሎች ሚሊሺዎች ደረሱ።ማራኪዎቹ «አትግደሉት እንፈልገዋለን» ይላሉ።

https://p.dw.com/p/2ReUH
Libyen David Cameron zu Besuch in Tripolis
ምስል Getty Images/AFP/S. Rousseau

ሊቢያ ከቃዛፊ መገደል በኋላ

 

የቀድሞዉ የግብፅ ፕሬዝደንት ገማል አብድናስር የአዲሱ እንግዳቸዉን ፍላጎት ስብዕናቸዉንም ለማወቅ ሳይሞክሩ አልቀረም።ሰዉዬዉ ፕሬዝደንት የሚለዉን ማዕረግ አይወዱትም።መሪ መባሉን ይመርጣሉ።ናስር በ1969 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) እንግዳቸዉን ሲቀበሉ ባዲስ ማዕረግ አሞካሹቸዉ።«የአረብ ብሔረተኞች ጠባቂ» ብለዉ።ሻለቃ ሙዓመር አል-ቃዛፊ ባዲሱ እንፈነደቁ ትሪፖሊ ገቡ።ኮሎኔል የሚለዉን ማዕረጋቸዉን ያፈቅሩታል።አብዮታዊ መሪ የሚል አከሉበት።ንጉስ ይጠላሉ።በ2007 የአፍሪቃ የባሕል መሪዎች ንጉሰ-ነገስት ሲሏቸዉ ግን በደስታ ተቀበሉት።ጥቅምት 20 2011።ሲርት።ሁሉም አበቃ።«መዓሰላማ» እንዲል አረብ።የሊቢያ የልቂት-እቶንም ተበረገደ።ባለፈዉ ሐሙስ አምስተኛ ዓመቱ። አምስተኛ ዓመቱ መነሻ፤ጥፋቱ ማጣቃሻ ፤ምክንያቱ መድረሻችን ነዉ።

                          
በሊቢያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ጀርመናዊዉ ዲፕሎማት ማርቲን ኮብለር በቀደም እንዳሉት የሊቢያን ቀዉስ የሚያስወገዱት ሊቢያዉን ብቻ ናቸዉ።ብሒል-ምግባር፤ ቃል ድርጊት ቢሆኑ ኖሮ ለሊቢያ ሆነ-ለሶሪያ፤ ለደቡብ ሱዳን ሆነ-ለኢትዮጵያ ወይም ለሌላ ሐገር  ፖለቲካዊ ምሥቅልቅል ከየሐገሩ ሕዝብ ሌላ-ትክክለኛ መፍትሔ ሰጪ ባልተገኘ ነበር።ድርጊት-ከብሒል መራራቅ አንዳዴም መቃረኑ እንጂ ድቀቱ።መጋቢት 2011።ዋሽግተን።የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት የሊቢያዉን መሪ አስጠነቀቁ።
                                
«ሙዓመር ቃዛፊ የሕዝባቸዉን እምነትና የመምራት ሕጋዊነትን በግልፅ አጥተዋል።ቃዛፊ የገዛ ሕዝባቸዉን መብቶች ከማክበር ይልቅ፤ የጭካኔ ጭቆናን ነዉ የመረጡት።ጭቆናቸዉን ካለቆሙ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች ተሰጥተዋቸዉ ነበር።የሐይል እርምጃዉ እንዲቆም የአረብ ሊግ እና የአዉሮጳ ሕብረት ከኛ ጋር ሆነዉ አስጠንቅቀዉ ነበር።ዝም ከተባሉ ቃዛፊ በሕዝባቸዉ ላይ የከፋ ግፍ እንደሚፈፅሙ የምናምንበት በርካታ ምክንያቶች አሉን።

Muammar Al Gaddafi Portrait
ምስል Khaled Desouki/AFP/Getty Images

የሊቢያዉ የአርባ-አንድ ዘመን ገዢ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ከተሰወሩ በኋላ በስልክ ከሚያገኗቸዉ ጥቂት ሰዎች አንዱ ሶሪያ ዉስጥ በስደት የሚኖሩት የቀድሞዉ የኢራቅ ምክር ቤት እንደራሴ ሚሻን ጃቡሪ ነበሩ።ጃቡሪ አል ኦሩባ የተሰኘዉ የግል ቴሌቪዢን ጣቢያ ባለቤትም ናቸዉ።ቃዛፊ ለኦሩባ ጣቢያ ሁለቴ መግለጫ መስጠታቸዉን የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኒካላ ሳርኮዚ ከብዙዎቹ የዓለም መሪዎች በተለየ ሁኔታ ተከታትለዉታል።ብዙ ሺዎች ይሞታሉ።ሰብአዊ ድቀቱ ያሻቅባል።አካባቢዉ በሙሉ ይመሰቃቀላል።በርካታ ተባባሪዎቻችን ለአደጋ ይጋለጣሉ።»
እርግጥ ነዉ ሊቢያዉያን በጋዛፊ የአርባ አንድ ዓመት አገዛዝ ተማረዉ፤ ለዉጥ እንዲመጣ ባደባባይ ሠልፍ ጠይቀዉ ነበር።አስጠንቃቂዉ ግን የሊቢያ ሕዝብ አልነበረም።የፓሪስ፤ ለንደን እና ዋሽግተን ሐያላን እንጂ።አሰጥነቅዉ አልቀሩም።
መጀመሪያ የሰወስቱ መንግስታት አከታትሎ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት የጦር ጄቶች የቃዛፊ መንግስት የጦር አዉሮፕላኖች እንዳይበሩ ለማገድ በሚል ሰበብ ሊቢያን ካየር ከባሕር ያጋይዋት ገቡ።ከጦርነቱ በኋላ መደረግ ሥለነበረበት ያቀደ አይደለም ያሰበና የገመተ መኖሩ ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።ከነበረም በሊቢያ የቀድሞዉ የጀርመን አምባሳደር ክርስቲያን ሙሽ እንደሚሉት ግምቱ የተሳሳተ ነበር።
                          
«እንደሚመስለኝ በ2011 ሥለሊቢያ የወደፊት ሁኔታ ሁሉም ማለት ሊቢያዉያን ራሳቸዉም ሆኑ እዚሕ ያለዉ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብም (ከተጨባጩ እዉነት ሳይሆን) ከራሳቸዉ የመነጨ ተመሳሳይ ግምት ነበራቸዉ።ሊቢያዎች የአረብ ሕዝባዊ አብዮት አካላት እንደሆኑ ማለትም ለግለሰብ ነፃነት፤ለመብት መከበርና ለዓለም ግልፅነት የሚደረግ ትግል አድርገዉ ሳያስቡት አልቀሩም።»
የአየር፤ የባሕር ድብደባዉ፤ሚሊሻዎችን መመልመል፤ ማሰልጠን ማስታጠቁ፤ ዉጪ የሚኖሩ ሊቢያዉያንን ማዝመቱ ቀጠለ።ያለቀዉ እያለቀ፤ የሊቢያ የመሰረተ ልማት አዉታሮች እየወደሙ ጀግናዉ  የሰሜን አትላንቲክ ጦር በድል ማግሥት ድል ያበስር ገባ።መስከረም 15 2011 የድል አድራጊዉ ጦር አዝማች አዛዦች የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኒኮላ ሳርኮዚ እና የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን ትሪፖሊን ጎበኙ።አሉም።
                                
«እዚሕ በመምጣቴ ተደሳቼያለሁ።የመጣነዉ ለሊቢያ የሽግግር መንግስት ዓለም አቀፍ ድጋፍ ለመስጠት ነዉ።ብዙ ሥራ መሠራት አለበት።አሁንም ረጅም ጉዞ ይቀራል።ለሊቀመንበር ጀሊል እና ለጠቅላይ ሚንስትር ጅብሪል ድጋፍ መስጠት አስፈላጊ ነዉ።»ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን።የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኒኮላ ሳርኮዚ ቀጠሉ።በጣም ጥሩ ቀን እያሉ።
                              
«ለኛ በጣም ጥሩ ቀን ነዉ።በመምጣታችን እንኮራለን፤ በጣም ጠቃሚ ነዉ።» በኔቶ ጦር የሚደገፉት የሊቢያ አማፂያን ትሪፖሊን ሲቆጣጠሩ ከቤተ መንግስታቸዉ የሸሹት ኮሎኔል ሙዓመር ጋዛፊ በስልክ ከሚያገኟቸዉ ጥቂት ወዳጆቻቸዉ አንዱ ደማስቆ በስደት የሚኖሩት የቀድሞዉ የኢራቅ የምክር ቤት እንደራሴ ሚሻን ጀቦሪ ነበሩ።ጀቦሪ አል-ኦሩባ የተሰኘዉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ባለቤትም ናቸዉ።ቃዛፊ በቴሌቪዥን ጣቢያዉ ሁለቴ የሰጡትን መግለጫ የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኒካላ ሳርኮዚ እንደ አብዛኛዉ የዓለም መሪዎች ሁሉ ተከታትለዉታል። ሳርኮዚ፤ የቃዛፊና  የልጃቸዉ የሰይፍ አል ኢስላም አፍ እንዲዘጋ ከሌሎቹ የዓለም መሪዎች ይበልጥ የሚጨነቁበት ልዩ ምክንያት ግን ነበራቸዉ።የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ለምርጫ ዘመቻ ማስፈፀሚያ ከሊቢያ ገዢዎች ገንዘብ ተቀብለዋል መባሉን የትሪፖሊ ገዢዎች እንዳያጋልጡ አጥብቀዉ ይፈልጋሉ።

Kanada Luftwaffe Symbolbild
ምስል picture alliance/dpa/P. Reed/ Department of National Defence

ዳይሊ ቴልግራፍ የተሰኘዉ ጋዜጣ የቀድሞዉን የሊቢያ የሽግግር መንግስት የዉጪ ስላላ ጉዳይ ሐላፊ ራሚ ኤል ኦቤይዲን ጠቅሶ እንደዘገበዉ የቃዛፊ ሁለተኛ መግለጫ እንደተሰማ፤ የሶሪያዉ ፕሬዝደንት  በሽር አል-አሰድ የቃዛፊን የሳተላይት ስልክ ቁጥር ከቴሌቪዥን ጣቢያዉ ባለቤት ተቀብለዉ እንዲሰጧቸዉ የፈረንሳዩ አቻቸዉ ይጠይቃሉ።
አል-አሰድ ቁጥሩን ከሰጧቸዉ ፈረንሳይ በአል-አሰድ ላይ የተነሳዉን ሕዝባዊ ተቃዉሞ ደግፋ በሶሪያ መንግስት ላይ ግፊት ማድረጓን እንደምትቀንስ ሳርኮዞ ቃል ይገባሉ።የሚፈልጉትን አገኙ።ቃዛፊ ያሉበትን አካባቢ አወቁ።ጥቅምት ሃያ 2011። በርካታ አጀብ ያለዉ ቅፍለት ከሲርት ወደ ሚስራታ መንቀሳቀሱን ሲርት የሸመቁት የፈረንሳይ ሰላዮች ለሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የጦር አዛዦች ጠቆሙ።የኔቶ ጄቶች ያን ቅፍለት ዶጋ አመድ ሲያደርጉት።ሰዉዬዉ አንድ ጉድባ ዉስጥ ተሸሸጉ።

Libyen Nato Luftangriff 2011
ምስል AFP/Getty Images

የኔቶ ጄቶች ቦምብ-ሚሳዬል ጋብ ሲል አካባቢዉን የወረሩት ሚሊሺያዎች ቃዛፊን ከጉድባ ዉስጥ መዝቀዉ አወጧቸዉ።ቆስለዋል።ያዩ እንደሚሉት ማራኪዎቹ ሰዉዬዉን መኪና ላይ ሲያወጧቸዉ ሌሎች ሚሊሺዎች ደረሱ።ማራኪዎቹ «አትግደሉት እንፈልገዋለን» ይላሉ።የሰማቸዉ የለም።የአረብ ብሔረተኞች ጠባቂ፤ ኮሎኔል፤አብዮታዊዉ መሪ፤የአፍሪቃ ንጉሰ-ነገስት፤የሊቢያ የአርባ ዘመን ገዢ ተፈፀመ።የሊቢያ አበሳ አለማብቃቱ እንጂ ሰቀቀኑ።እርግጥ ነዉ-የፓሪስ፤ ዋሽግተን፤እና ለንደን መሪዎች የሌለ-ተስፋ ሰጥተዉ፤ ቃል ገብተዉም ነበር።ሳርኮዚ ቀደሙ።
                                        
«ዴሞክራሲ፤ ሠላም እና እርቅ።»ፕሬዝደት ኦባማ ቃል-ተስፋዉን አጠናክረዉ፤ አሳምረዉ፤ አጉልተዉ አከሉበት።
                              
«ዛሬ የቀዳፊ ሥርዓት በርገጥኝነት ተወገደ ማለት እንችላለን።የመጨረሻዎቹ ጠንካራ ይዞታዎቹ ተማርከዋል።የሽግግር መንግሥቱ ሐይሉን እያጠናከረ ነዉ።ለረጅም ጊዜ ሥልጣን ላይ የቆየዉ አምባገነን ከእንግዲሕ የለም።በሊቢያ ታሪክ ይሕ ልዩ ቀን ነዉ።የአምባገነኑ ጥቁር ጥላ ገፏል።በዚሕም ምክንያት አዳዲስ ተስፋዎች ፈንጥቀዋል።የሊቢያ ሕዝብ አሁን ሁሉን አቀፍ፤ ታጋሽ እና ከቃዛፊ ሥርዓት ጋር ፍፁም የሚቃረን ሊቢያን የመገንባት ታላቅ ሐላፊነት አለበት።»
የሊቢያ ሕዝባዊ ዓመፅ ከተቀሰቀሰበት ከየካቲት አጋማሽ፤ የምዕራባዉያን የጦር ጄቶች ሊቢያን መደብደብ እስከጀመሩበት እስከ መጋቢት ማብቂያ ድረስ የቃዛፊ መንግሥት ጦር ገደለ የተባለዉ ሰዉ ቁጥር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ ድርጅቶች እንዳስታወቁት ከአምስት መቶ እስከ 1000 ቢደርስ ነበር።
የኔቶ ጦር ሊቢያን መደብደብ ከጀመረበት ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ እስከተገደሉበት ድረስ፤ የተገደለዉ ሕዝብ ቁጥር፤ የሊቢያ የሽግግር መንግሥት ያኔ እንዳስታወቀዉ ከ25 ሺሕ እስከ 30 ሺሕ ይደርሳል።ቃዛፊ ከተገደሉ በኋላስ? ሊቢያ እንደ ሐገር የታለችና-እንበል ይሆን?።በአዉሮጳ ሕብረት ምክር ቤት የዉጪ ግንኙነት ባልደረባ ማቲያ ቶልዶ እንደሚሉት ሊቢያ ዜጎችዋ መከራ እያጨዱባት ነዉ። 

                        
«ለአብዛኛዉ ሊቢያዊ የዕለት ከዕለት ኑሮ በጣም ከባድ ነዉ።መብራት ይቋረጣል።ትሪፖሊ ዉስጥ ባለፈዉ ወር ብቻ አንድ መቶ ዘጠኝ ጊዜ እገታዎች ደርሰዋል።ገንዘብ በጣም ትንሽ ነዉ።ማግኘት ከባድ ነዉ።ስለዚሕ ኑሮ በጣም ከባድ ነዉ።ፀጥታዉ ደፍርሷል።ኤኮኖሚዉ ወድቋል።»
ሰዉም በየዕለቱ ይወድቃል።ይገደላል።ይደፈራል።ይታሰራል።ለወትሮዉ የአፍሪቃ ሐብታሚቱ ሐገር ዛሬ የአሸባሪዎች መራቢያ፤ የአጋቾች፤ የስደተኛ አሸጋጋሪዎች መናኸሪያ ሆናለች።
                                 
«በሐገሪቱ በመቶ የሚቆጠሩ የተለያዩ ታጣቂ ቡድናት አሉ።ቢያንስ አምስቱ የተለያየ ሥልጣን ማዕከላት አላቸዉ።ዋንኞቹ ምሥራቅ ሊቢያ ዉስጥ ጄኔራል ኸሊፋ ሒፍጣር የሚመሩት መንግሥት፤ ትሪፖሊ ዉስጥ ደግሞ ሁለት መንግስታት አሉ።አንዱ እዉቅና የሌለዉ መንግስት ነዉ።ሁለተኛዉ ዓለም አቀፉ ዕዉቅና ያለዉ የአል ሲራጅ መንግስት ነዉ።ሌሎች እራሳቸዉን የሊቢያ መንግስት የሚሉ ብዙ ተዋኞች አሉ።የመንግሥት አይነት አቅም ያላቸዉ ማለት በጀት የሚቆጣጠሩ፤ ጦር ያላቸዉ፤ ፓስፖርት መስጠት የሚችሉ ግን የሉም።»  
የዩናይትድ ስቴትስ የጦር አዉሮፕላኖች ዛሬም ሊቢያን በተለይ ሲርት እና አካባቢዋን ይደበድባሉ።ዒላማቸዉ የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግስት (ISIS) የተሰኘዉ ቡድን ነዉ አሉ።የሳርኮዚ፤ የካሜሩን፤የኦባማ ሰላም፤ ዴሞክራሲ፤ ሰብአዊ መብት የትደረሰ ይሆን።ግን ኦባማ እንደለደን እና ፓሪስ ብጤዎቻቸዉ ሥልጣን ከማስረከባቸዉ በፊት አንድ ነገር ብለዋል።«ተሳስቻለሁ።» 

Nato Bombenangriff in Libyen
ምስል DW

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ