1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለኤቦላ መከላከያዉ ለምን ዘገየ?

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 28 2007

ከአንድ ዓመት ተመንፈቅ በፊት በምዕራብ አፍሪቃ ሰወስት ሃገራትን ቀስ በቀስ ሲያዳርስ በቀላሉ የሚገታና በአጭሩ የሚቀጭ ተደርጎ ነበር የታሰበዉ።

https://p.dw.com/p/1G9xF
Sierra Leone Ebola
ምስል DWD. Pelz

ለኤቦላ መከላከያዉ ለምን ዘገየ?

የኤቦላ ተሐዋሲ ወረርሽኝ ግን ጊኒን መግቢያዉ ያድርግ እንጂ ሴራሊዮን ላይቤራን አዳርሶ ወደናይጀሪያ እና ሴኔጋል ለአጭር ጊዜም ቢሆን ጎራ አለ። በዚያም አልተገታም ስፔን፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ማሊ ከዚያም ታላቋ ብሪታንያንያና ጣልያንንም ጎበኘ። ሊጠፋ ነዉ እየተባለ ሲጠበቅ መጀመሪያ በተከሰተባቸዉ ሃገራት አሁን ዳግም ብቅ ብቅ ማለት ጀምሯል።

የህክምና ተመራማሪዎች ጊዜ ወስደዉ የሚያጠኗቸዉ የተለያዩ የህክምና ስልቶች መኖራቸዉ የነበረና ያለ ነዉ። ጥናቱ ግን በገዳይነታቸዉ ስማቸዉ ሲነሳ ለሚያርደዉ የበሽታ ዓይነቶች በቶሎ መፍትሔ መፈለጉ ላይ ጊዜ ይወስዳል፤ ሲወስድም እየታየ ነዉ። የኤች አይቪ ተሐዋሲ ቀስ በቀስ የያዘዉን ግለሰብ አካል እያዳከመና እያዳቀቀ ለሌላ በሽታ አሳልፎ እየሰጠም በሺ ብቻ ሳይገታ የሚሊዮኖችን ሕይወት ያለ ገላጋይ ነጥቋል። ሕዝብ የበዛባት የምትመስለዉ ዓለም ሰዎች በሰበብ አስባቡ እንዲያልፉላት ትሻ ይመስል ለገዳዩ በሽታ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ስታዘግም ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። ካንሰር ዛሬም እንቆቅልሽ ሆኖ ግን ደግሞ ለህክምናዉ የሚረዳ መፍትሄ ፍለጋዉ ሳያባራ ቀጥሏል።

Karte Ebola Neue Fälle 1. Juli 2015
ኤቦላ ያዳረሳቸዉ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት

ከአንድ ዓመት ተመንፈቅ በፊት መጀመሪያ ወደጊኒ የገጠር መንደር ጎራ ማለቱ የተነገረለት የኤቦላ ተሐዋሲ ሰዎቹ ባላቸዉ የአኗኗር ይትበሃል ማለትም በእጅ ላይ መሸፈኛ ፕላስቲክ ወይም ጓንት ሳያደርጉ አስከሬን አጥቦ የመገነዝና የታመመን እየነካኩ የማስታመም ባህል ምክንያት እንደዋዛ መዛመቱ ነዉ የሚነገረዉ። እናም አንድ ሁለት ሳይሆን ሃምሳ መቶዉን በየቀየዉ ገደለ። ከመንደር ወደሀገር ብሎም ወደጎረቤት ሃገራትም ዘለቀና ዘረ አዳምን ይፈጀዉ ገባ። አንድ ወር ሁለት ወር ሶስት እያለ ከራረመ እና የዓለም የጤና ድርጅት አሳሳቢ የጤና እክል መከሰቱን ለዓለም አሳወቀ። በሽታዉ የተደራጀ የጤና መሠረተ ልማት የሌለባቸዉን የሴራሊዮን፣ ጊኒ እና ላይቤሪያ ዜጎችን ብቻ ሳይሆን በኤቦላ ተሐዋሲ የተጎዱትን ወገኖች በህክምና ሙያቸዉ ለመርዳት እዚያ የተገኙትን በጎ ፈቃደኞችም ደፈረ። ከታማሚዎቹ መጤዎች ከጥቂት እድለ ቢሶች በቀር ሁሉም ድነዉ ተነሱ። የምዕራብ አፍሪቃ የኤቦላ ተጠቂ ሃገራት ዜጎችና ሃኪሞቻቸዉ ግን ካልተለመደዉ ምህረት አልባ ወረርሽኝ ጋ የሞት ሽረት ፍልሚያዉን በነሲብ ቀጠሉ።

Sierra Leone Ebola Hilfe
ምስል L'Appell Deutschland

በሽታዉ ትኩረት ማግኘቱ አንድ ነገር ሆኖ በየመገናኛ ብዙሃኑ ብዙ ተባለለት። የተለያዩ የመድኃኒት ኩባንያዎችም መፍትሄ እንዲያመጡ ተወተወቱ። ጊዜ ወሰደ፤ ይህም ትችትን አስከተለ። ጉዳዩን ከሚከታተሉት መካከል ብሪታንያ ዉስጥ የኤቦላ ወረርሽኝ ምላሽ ሰጪ ተቋምን የሚመሩት ሳይንቲስት ፕሮፌሰር አድሪያን ሂል አራቱ ታላላቅ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ለኤቦላ መከላከያ ክትባት ማዘጋጀት ያቃታቸዉ የማይቻል ሆኖ ሳይሆን መድኃኒቱ ቢዘጋጅ ገበያ የለዉም በሚል ስጋት ነዉ በማለት ክፉኛ ተችተዋቸዋል። ምዕራብ አፍሪቃ ዉስጥ ኤቦላ ገና 2000 ሰዎችን እንደገለደለ ግላስኮ ስሚዝ ክላይን፣ ሳኖፊ ሜርክ እና ፊዘር የተባሉት አራት ታዋቂ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች መከላከያ ክትባቱን አምርተዉ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ተስፋፍቶ የበርካቶችን ሕይወት ባላጠፋ፤ ብዙዎችንም ባልያዘ ነበር ሲሉም ፕሮፌሰሩ የወቀሱት ከዓመት በፊት ነበር።

የኤቦላ ተሀዋሲ ክፉኛ ከጎዳቸዉ ሶስት የአፍሪቃ ሃገራት ሊጠፋ የመቃረቡ ዜና ተነግሮ ሳይበርድም ዳግም ከኤቦላ ተሀዋሲ ነጻ በተባሉት ሃገራት መከሰቱ ስጋቱን ከፍ አድርጎታል። ከዚህ ቀደም ኤቦላ ይከሰትባቸዉ ከነበሩት ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ፤ ሱዳንና ዩጋንዳ ቶሎ መጥፋቱ የተለመደ ነበር አሁን ግን ከዓመት ከስምንት ወር በላይ ሴራሊዮን ላይቤሪያና ጊኒን ፋታ አልሰጥ ማለቱ እንቆቅልሽነቱን ከፍ አድርጎታል።

Ebola Impfung
ምስል picture-alliance/dpa/A. Jallanzo

ሰሞኑን ሴራሊዮን ዉስጥ አንድ ኗሪ ከዋና ከተማ ፍሪታዉን የሙስሊሞችን የፆም ወቅት ፍፃሜ በዓል ለማክበር ዘመዶቹ ወደሚገኙበት የገጠር መንደር ይገባል። ትኩሳት ስለጠናበት ሃኪም ቤት ቢገባም የኤቦላ ጥርጣሬ ሲኖር የህክምና ባለሙያዎቹ የሚያደርጉት የስልክ ጥሪ አልተሰማም ነበር። እናም ሳይገመት ሰዉየዉ በበሽታዉ ሕይወቱ አለፈ። በቀጣይም ሁለት ቤተዘመዶቹ ታመሙ ያኔ በአካባቢዉ ጥርጣሬዉ ከፍ አለ። እንደተገመተዉም ኤቦላ መሆኑ ተረጋገጠ። ቀደም ሲልም 500 ሰዎች ተሐዋሲዉ ሳይነካቸዉ አይቀርም በሚል ጥርጣሬ ክትትል እየተደረገላቸዉ እንደሆነ ተሰምቷል። አንድ ሰዉ በኤቦላ ተሐዋሲ ከተያዘ ከሁለት እስከ 21 ቀናት ድረስ የህመም ምልክቱ ይታይበታል። ክትትሉም ይህን ለማጣራት ነዉ። የኤቦላ ተሐዋሲ እንደአዲስ በማስጋቱም የአሜሪካን የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ቶም ፍሪደን በሴራሊዮን የጤና ስርዓት ላይ ለመመካከር እዚያዉ ይገኛሉ። የተሀዋሲዉ ተዳፍኖ ማገርሸት በጤና አገልግሎቱ ላይ መሠራት የሚገባቸዉ መሻሻሎች መኖራቸዉን ያመለክታል ነዉ የተባለዉ።

ምንም እንኳን የኤቦላ ተሐዋሲ ስጋትነት በምዕራብ አፍሪቃ ገና ባያከትምም ጊኒ ዉስጥ ለሙከራ የቀረበ የመከላከያ ክትባት ሙሉ በሙሉ ስኬታማ ነዉ እየተባለለት ነዉ። በአንድ ሳምንት ጊዜ ዉስጥም ከ7,600 በላይ ሰዉ መከላከያ ክትባቱን ተከትቦ ፍንጭ መታየቱን ላንሰት የተሰኘዉ የህክምና መረጃ መጽሔት ይፋ አድርጎታል። የዓለም የጤና ድርጅትም ባለፈዉ ሳምንት ዓርብ ክትባቱን በጣም ተስፋ ሰጪ ነዉ ሲል አድንቆታል። የዓለም የጤና ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ማሪ ፖል ኪኒ ስለክትባቱና ሙከራዉ እንዲህ ነዉ ያሉት፤

«እስካሁን ያሉት መረጃዎች ክትባቱን ከወሰዱት 2,014 ሰዎች መካከል አንዳቸዉም የኤቦላ ተሐዋሲ የሚያስከትለዉ ህመም አልታየባቸዉም። ስለዚህ ይህን ስልት ተጠቅመን ሙከራዉን በመቀጠል ወጣቶች ሁሉ እንዲከተቡ በማድረግ ኤቦላን ለመግታት የሚታገለዉን ቡድን በመርዳት ጊኒ ዉስጥ የኤቦላ ስርጭትን ወደዜሮ እናወርደዋለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን።»

World Health Organization (WHO) - Marie Paule Kieny
ዶክተር ማሪ ፖል ኪኒምስል Fabrice Coffrini/AFP/Getty Images

በርን ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተመራማሪዎች እንደገለፁት ከሆነ በሙከራ ክትባቱ የታየዉ ዉጤት ተሐዋሲዉ ከአንድ ሰዉ ወደሌላዉ እንዳይዛመት ማድረግ ነዉ። መከላከያ ክትባቱን የወሰዱት ሰዎችም 10 ቀናት ተጠብቀዉ በተደረገዉ ምርመራ ተሐዋሲዉ እንዳልተዛመተ ተረጋግጧል። ክትባቱን ለማምረት ዳተኝነት በመታየቱ ግን የዓለም የጤና ድርጅት ኃላፊነቱን ወስዶ ዶክተሮች፣ ለጋሾችንና ተመራማሪዎችን አስተባብሮ ከዚህ ዉጤት ለመድረስ መቻሉ ነዉ የተነገረዉ። የኖርዌይና የካናዳ መንግሥታትም ለዚህ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጋቸዉ ተመዝግቧል። ሜርክ የተሰኘዉ የመድሃኒት ኩባንያ ያዘጋጀዉ ይኽ የክትባት ሙከራ እዉን እንዲሆንም ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን ትልቅ ሚና ተጫዉቷል። ይህ የሃኪሞች ስብስብ ወረርሽኙ ጊኒ፣ ሴራሊዮንና ላይቤሪያን ባስጨነቀበት ወቅት የበጎ ፈቃድ ባልደረቦችን አሰማርቶ የማይረሳ ሙያዊ ኃላፊነቱን ተወጥቷል።

የጀርመን የህክምና ባለሙያዎች ድርሻም ቀላል አልነበረም። አሁንም ሴራሊዮን ዉስጥ የሚገኘዉ ኒኮላስ አሾፍ ሌአፔል ጀርመን የተሰኘዉ ማኅበር ባልደረባ ነዉ። በቪተን ሔርዴከ ዩኒቨርሲቲየህክምና ትምህርት ተማሪዉ አሾፍ በአንድ ወቅት ስለበሽታዉ ብዙ ሲወራ ቆይቶ አሁን ችላ መባሉ ኤቦላ ፈፅሞ የጠፋ እና የሚጎዳዉ የሌላ አስመስሎታል ይላል።

Impfstoff gegen Ebola
የኤቦላ መከላከያ ክትባትምስል Reuters

«በኢቦላ ተሐዋሲ የተጠቁ ሰዎች እንዳሉ እንሰማለን። የሚያሳዝነው ነገር ግን በጀርመን እና በአውሮጳ የሚገኙ የመገናኛ አውታሮቻችን እንደቀድሞው ትኩረት ሰጥተው ዚዘግቡበት አይታይም። ምናልባትም በኢቦላ የተጠቃ ሰው ከእንግዲህ በጀርመን፣ በዩናይትድ ስቴትስ ወይንም ደግሞ በአጠቃላይ በአውሮጳ ስለሌለ ይኾናል፤ ብቻ ያ መኾኑ ያሳዝናል። »

በእርግጥም ስለኤቦላ በሚያወጧቸዉ ዘገባዎች ገፆቻቸዉን ያጣብቡ የነበሩ ጋዜጦችና መጽሔቶችም ክትባቱ ተገኘ የሚለዉን መረጃ ለማዉጣት ከመፋጠናቸዉ ዉጭ ችላ ብለዉት ሰንብተዋል ማለት ይቻላል። ግን ደግሞ የምዕራብ አፍሪቃዎቹን ደሀ ሃገራት የጤና መሠረተ ልማት ደካማነት በማሳየት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ርዳታ እንዲሰባሰብ ያደረጉት ቅስቀሳ ትልቅ ቦታ የሚሰጠዉ ነዉ። ያም ሆኖ በኤቦላ የተጎዱትን የጊኒ፣ ሴራሊዮንና ላይቤሪያን የጤና መሠረተ ልማት እና አገልግሎት ደረጃዉን ከፍ ለማድረግ እና ኤኮኖሚያቸዉን ለመደገፍ የተጠየቀዉ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ርዳታ ከታሰበዉ ጊዜ ዘግይቷል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ