1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“ለኤርዶኻን ለመንበርከክ ዝግጁ አይደለሁም” ማርቲን ሹልዝ

ቅዳሜ፣ መስከረም 6 2010

የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ዕጩ መራሔ-መንግስት ማርቲን ሹልዝ “ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ለማስቆም እንደ ኒጀር ከመሳሰሉ ሀገራት ጋር መስራት ይገባናል” አሉ፡፡ ሹልዝ ይህን የተናገሩት ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ልዩ ቃለ ምልልስ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/2k6n0
Deutschland wählt DW Interview mit Martin Schulz
ምስል DW/R. Oberhammer

መስከረም 14 አጠቃላይ ምርጫ በምታካሄደው ጀርመን የስደተኞች ጉዳይ አንገብጋቢ አጀንዳ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ሹልዝ በስደተኞች ጉዳይ ላይ እንደ ኒጀር ከመሳሰሉ ሀገራት ጋር መተባበር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው “ይህ የሚሆነው ግን በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተቆጣጣሪነት ይሆናል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡  ምክንያታቸውን ሲጠቅሱም “ህገ መንግስታዊ ልማዶች ሊጠበቁ ስለሚገባ እና የተወሰኑ ሀገራት ዓለም አቀፍ ህጋዊ አካሄዶችን ያለመከተል አደጋም ስላለ ነው” ብለዋል፡፡    

ሹልዝ ጀርመን ከሌሎች ሀገራት ጋር ስላላት ግንኙነትም ተጠይቀው ነበር፡፡ ሀገሪቱ ከቱርክ ጋር የገባችው እስጥ አገባ እስካሁን አልበረደም፡፡ የቱርክ ፕሬዝዳንት ራቺብ ጣይብ ኤርዶኻን ጀርመንን በተደጋጋሚ ሲወቅሱ ተደምጠዋል፡፡ ሹልዝ “ከኤርዶኻን ጋር ያለው ችግር ስደተኞችን በጥሩ ሁኔታ አልያዘም በሚል አይደለም፡፡ ይልቁንስ ለቱርክ ህዝብ ባለው መጥፎ አያያዝ ነው” ሲሉ የችግሩን መንስኤ አስረድተዋል፡፡ “ለኤርዶኻን ለመንበርከክ ዝግጁ አይደለሁም፡፡ እንዲያስፈራሩን መፍቀድ የለብንም” ሲሉም ጠንከር ባሉ ቃላት አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል፡፡ 

የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገር ለመሆን በድርድር ላይ የምትገኘው ቱርክ በህብረቱ ከፍተኛ ተደማጭነት ካላት ጀርመን ጋር ያላት ግንኙነት መሻከር የአባልነት ጥያቄዋ ላይ ጥላ ማጥላቱን ታዛቢዎች ያስረዳሉ፡፡ ሹልዝ ቃለ-ምልልስ የሚያደርግላቸውን ጋዜጠኛ  “ወደ ቱርክ ለዘገባ ብትሄድ በቀጣዩ ቀን እስር ቤት ትገባ ወይ አትገባ እንደሁ አላውቅም፡፡ ይህ በእርግጠኝነት ከአውሮፓ ህብረት መርሆዎች ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም” ሲሉ ቱርክ በንግግር ነጻነት ላይ የምታራምደውን አቋም በምሳሌ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡

Deutschland wählt DW Interview mit Martin Schulz
ምስል DW/R. Oberhammer

የመራሔተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል ዋነኛ ተፎካካሪ የሆኑት ሹልዝ ስለ መሪዋ ተጠይቀው ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ “አንጌላ ሜርክል ጀርመንን ‘በደህና ሁኔታ የሚኖርበት እና በኑሯችን የምንደስትበት ሀገር’ በሚለው መፈክር ስር እንዲቀጥል ማድረግ ችለዋል፡፡ ትክክል ናቸው፡፡ በደህና ሁኔታ እየኖርን ነው ያለነው፡፡ በዚህ ሀገር በመኖራችን ደስተኞች ነን፡፡ ነገር ግን ነገም ህይወት ጥሩ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ለዚህም ነው ለህዝቡ የትኛውን መንገድ እንደምንከተል መንገር የሚገባን” ብለዋል፡፡   

በሕዝብ አስተያየት መለኪያዎች በየጊዜው ዝቅተኛ ውጤት ማግኘታቸውን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ እምብዛም ቦታ እንደማይሰጡት በምላሻቸው አመልክተዋል፡፡ “የጠዋት ጋዜጣ ስከፍት የድምጽ መለኪያዎች ወደ እኔ አጋድለው ካየሁ ደስተኛ ነኝ፡፡ የድምጽ መለኪያዎቹ መጥፎ ከሆነ ደስተኛ አልሆንም፡፡ ነገር ግን በህይወቴ ሙሉ የራሴን ከፍ እና ዝቅ ድርሻ አግኝቻለሁ፡፡ የውስጥ ስሜቴ የሚነግረኝ የድምጽ መለኪያዎቹ በቃ የድምጽ መለኪያዎች መሆናቸውን ነው፡፡ ህዝቡ በመስከረም 14 ይናገራል፡፡ ከዚያ የምናየው ነው የሚሆነው፡፡ በድምፅ አስተያየት መለኪያዎች የምትምራ ከሆነ ምን እንደሚገጥምህ ታውቃለህ? የራስህን መርሆዎች ትተህ የጊዜውን ተወዳጅ አስተያየት ትከተላለህ፡፡ እኔ ይህን አላደርግም” ሲሉ ፍርጥም ብለው መልሰዋል፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

እሸቴ በቀለ