1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ለሙሉ ቆጣቢዎች ያደላው የ40/60 ቤቶች ግንባታ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 5 2009

የኢትዮጵያ መንግሥት በ40/60 እቅዱ የገነባቸውን የመኖሪያ ቤቶች በመጀመሪያው የዋጋ ተመን ሙሉ ክፍያ ለቆጠቡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በዕጣ አከፋፍሏል። የቤት ግንባታ መርሐ-ግብሩ ሙሉ ክፍያ ለፈጸሙ ተመዝጋቢዎች ብቻ የመኖሪያ ቤቶች ሲያከፋፍል የተቀመጠለትን መርኅ ጥሶ ይሆን?ለባለ አንድ መኝታ ቤት ተመዝግበው የቆጠቡስ ስለምን ችላ ተባሉ?

https://p.dw.com/p/2gQBK
Addis Ababa (Äthiopien)
ምስል picture alliance/landov


ከአራት አመታት ገደማ በፊት 166,006 የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የኢትዮጵያ መንግሥት ይፋ ባደረገው የ40/60 የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ መርኃ-ግብር ሲመዘገቡ ቆጥቤ ጎጆ እቀልሳለሁ ብለው ነበር። የግንባታ ሂደቱ አዝጋሚነት ተስፋ ያስቆረጣቸው ቁጠባውም የፈተናቸው የመኖሪያ ቤት የማግኘት ዕድላቸውን "የሕልም እንጀራ"ያሉት አልጠፉም።
የመኖሪያ ቤቶቹ ተገንብተው ከተመረቁ ወራት ቢቆጠሩም ቁልፎቻቸው ከባለቤቶቻቸው እጅ ለመግባት እስከ ቅዳሜ ጠብቀዋል። የመኖሪያ ቤቶቹን የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ይገንባቸው እንጂ ለባለቤቶቻቸው የማስረከብ ኃላፊነቱን የወሰደው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነበር። ሐምሌ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. የዕጣ አወጣጥ ሥርዓት ከመካሔዱ በፊት ግን የባለ ሁለት እና ሦስት መኝታ ቤቶች የዋጋ ተመን ጭማሪ ማድረጉ ተሰማ። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ እንደሚሉት የባለ ሁለት መኝታ ቤት ዋጋ ከ150 በመቶ በላይ ሲንር የባለ ሦስት መኝታ ቤቶች ቀድሞ ከተተመነላቸው በእጥፍ ጨምረዋል።
በዕለተ-ቅዳሜው የዕጣ አወጣጥ ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞች የብድር አስተዳደር ኃላፊ አቶ ኪዳኔ መንገሻ 17,644 ነዋሪዎች የቤቶቹን ሙሉ ክፍያ ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል። እንደ ኃላፊው ከሆነ በዕጣ አወጣጥ ሥርዓቱ የተካተቱ ተመዝጋቢዎች የቤቶቹን ዋጋ በ18 ወራት ውስጥ በባንክ የሒሳብ ደብተራቸው የቆጠቡ ናቸው። በዚህ መሠረት ለባለ ሁለት መኝታ ቤት የተመዘገቡ ነዋሪዎች ሙሉ ክፍያውን ለማጠናቀቅ በወር 13,800 ብር ገደማ ቆጥበዋል። ለባለ ሦስት መኝታ ቤቶች የተመዘገቡት በአንፃሩ ወደ 24,000 ብር ገደማ መቆጠብ ነበረባቸው። ቅዳሜ ዕለት የመኖሪያ ቤቶች በዕጣ የወጣላቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በአዲሱ የዋጋ ተመን መሠረት ተጨማሪ ክፍያ ይጠበቅባቸዋል። የባለ ሁለት መኝታ ቤት ባለቤቶች 364,000 ብር ገደማ እንዲሁም ባለ ሦስት መኝታ ቤት የደረሳቸው ከ349,000 ብር በላይ ተጨማሪ ክፍያ አለባቸው። 
አዲሱ የዋጋ ተመን ለቤት ፈላጊዎች እንግዳ መሆኑ አልቀረም። የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ አባይነህ ግን በሰንጋ ተራ እና ክራውን የተገነቡት የመኖሪያ ቤቶች የዋጋ ተመን በጥናት ተወስኗል ባይ ናቸው። የቤት ግንባታ መርኃ-ግብሩ ይፋ ተደርጎ ምዝገባ ሲጀመር በመኖሪያ ቤቶቹ ዋጋ ላይ "መጠነኛ ማስተካከያ" ይደረጋል መባሉን የሚያስታውሱት አቶ አብዱልመናን ጭማሪው ቀድሞ እንደተባለው "መጠነኛ" ለመሆኑ ጥያቄ አላቸው። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው በግንባታ ግብዓቶች ጭማሪ እና በቤቶች ስፋት ለውጥ ምክንያት የተደረገው ጭማሪ የማይቀር ቢሆንም "አስደንጋጭ" እንደሆነም ይናገራሉ።
ሙሉ ክፍያውን በባንክ የቆጠቡ 16,672 ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤቶቻቸውን አላገኙም። ከእነዚህ መካከል ከ10,000 በላይ የሚሆኑት በቅዳሜው የዕጣ አወጣጥ ሥርዓት እድል ያልቀናቸው ናቸው። ሌሎች 41,348 ነዋሪዎች 40 በመቶ እና ከዚያ በላይ መቆጠባቸው ተሰምቷል። ቁጠባውን ጀምረው መቀጠል የተሳናቸው አሊያም መጠበቁ ያሰለቻቸውም አልጠፉም። 
መካከለኛ ገቢ ያላቸው የቤት ፈላጊዎችን ጥያቄ ለመመለስ የተጀመረው መርኃ-ግብር በስም 40/60 ይባል እንጂ በዕለተ-ቅዳሜው የዕጣ አወጣጥ ሥርዓት የተካተቱት ተመዝጋቢዎች መቶ በመቶ የቆጠቡ ብቻ ናቸው። ከ40 በመቶ በላይ የቆጠቡ ከ41,000 በላይ ነዋሪዎች በዕጣ አወጣጥ ሥርዓቱ የመካተት ዕድል አላገኙም። መርኃ-ግብሩ የታቀደለትን አላማ ስቶ ይሆን? አቶ ዮሐንስ አባይነህ የቤት ግንባታ መርኃ-ግብሩ ፈጽሞ መርሁን አልጣሰም ሲሉ ይሞግታሉ። በ40/60 የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ መርኃ-ግብር ለባለ አንድ መኝታ የተመዘገቡ ነዋሪዎች በባለ 12 እና በባለ ዘጠኝ ፎቆቹ ሰንጋ ተራ እና ክራውን ቦታ አላገኙም።  ተመዝግበው ሲቆጥቡ የከረሙ አዲስ አበቤዎች ባለ አንድ መኝታ ቤቶች አለመኖራቸውን የተረዱትም ዘግይተው ነበር። አቶ ዮሐንስ በሂደት በተደረገው የንድፍ ለውጥ ምክንያት ባለ አንድ መኝታ ቤቶች መቅረታቸውን ይናገራሉ። 
አቶ ዮሐንስ የቤቶች ግንባታ መርሐ-ግብሩ በአቅም እጦት እና በእቅድ አስተዳደድ ልምድ ማነስ መዘግየቱን ይስማማሉ። የግንባታ ግብዓቶች እጥረት ለመዘግየቱ ሌላው ገፊ ምክንያት መሆኑንም ገልጠዋል። አቶ ዮሐንስ 20,932 የመኖሪያ ቤቶችን ግንባታ በሚቀጥለው ዓመት ለማጠናቀቅ ማቀዳቸውንም ተናግረዋል። አቶ አብዱልመናን መሐመድ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እቅዶች ከአቅሙ በላይ የተለጠጡ መሆናቸውን ይተቻሉ። ባለሙያው ከአራት ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ላሏት አዲስ አበባ የመኖሪያ ቤቶች ችግርን ለመፍታት ሌሎች አማራጮችንም መመልከት ያሻል ባይ ናቸው። 

እሸቴ ቀበለ
ሸዋዬ ለገሠ

Äthiopien Hausbau
ምስል DW/E. Bekele
Äthiopien Hausbau
ምስል DW/E. Bekele