1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሃያኛዉ ዓመት የጀርመን ዉሕደት-የዉሕደቱ በዓል ታላቅ ፌስታ

ረቡዕ፣ መስከረም 19 2003

በኤንባሲ ዉስጥ ጥገኝነት ስለጠየቁት ወገኖች፣ ወደ ምዕራብ ጀርመን መጓዝ እንዲችሉ ስላደረኩት ድርድር፣ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃንስ ዲትሪሽ ጌንሸር፣ በፕራግ የጀርመን ኤንባሲ በረንዳ ላይ ስላደረጉት ንግግር፣ የጀርመን ግንብ እንደፈረሰ በጀርመን ምክር ቤት ዉስጥ ስላደረኩት ንግግር---

https://p.dw.com/p/PPtK
ለጥቅምት 3 አጥቢያ ራይሽታግ ሕንፃ ላይ ርችት-ሲተኮስምስል picture-alliance/dpa


እ.ጎ.አ በ 1990ዉ ጥቅምት 2 ማታ በሺ የሚቆጠር ህዝብ በርሊን ዉስጥ የጀርመንን ዉህደት አክብርዋል። ፖለቲከኞችም ዉጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል የማይታወቅ ድርድር ለወራቶች ሲያካሄዱ ቆይቶአል።

ሌሊቱን በቀድሞዉ የጀርመን ምክር ቤት ህንጻ (Reichstag) አናት ላይ የደስታዉ መግለጫ ርችት ሲፈነጥቅ በርካታ ህዝብ በደስታ አልቅሶአል። ሕዝቡ ጀርመናዊዉም ሆነ ሌላዉ የአዉሮጻ ነዋሪ ይሆናል ብሎ ያልገመተዉ የአንድ ትልቅ ታሪካዊ ክስተት መስካሪ ነዉ። የምስራቅ ጀርመን ህዝብ ሰላማዊ በሆነ አብዮት በሶሻሊስት ርዕዮተ አለም የሚመራዉን መንግስት አስወገደዉ። በዚህ ሰላማዊ ንቅናቂ አንድም ጥይት አልጮኸም። ምንም አይነት ብጥብጥ እና ግጭት አልተከሰተም። አንድም ሰዉ አልተጎዳም።በማግሥቱ ጥቅምት 3 ቀን የጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ከጀርመን ፊደራላዊ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ጋር ተዋሃደች።የጀርመን ህዝብም በአንድ አገር መኖር ጀመረ።

Flash-Galerie Richard von Weizsäcker wird 90 Wiedervereinigung 1990
የዉሕደቱ ዕለት፦- ሪሻርድ ፎን ቫይትሴከር፤ ሄልሙት ኩል፦ ደ ሚዜርና ሌሎችምስል picture alliance/dpa

በዚህ ምሽት የፊደራላዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጀርመን ፕሪዝዳንት የነበሩት ሪሻርድ ፎን ቫይትሴከር የጀርመን እና የአዉሮጳ ክፍለ አሐጉር ዳግም አንድነትን ተመለክተዉ እንዲህ ሲሉ ገልጸዉ ነበር «እኛ ጀርመናዉያን ሃላፊነታችንን በጥንቃቄ ለመቀበል ዝግጁ ነን፣ በተባበረዉ አዉሮጻ ዉስጥ እና በአጠቃላይ በአለም ላይ ሰላምን ለማስፈን የሚጠበቅብንን አስተዋጽኦ ሁሉ እናደርጋለን»

አንቅልፍ አልባዉ ሌሊት

የምዕራብ ጀርመን መራሔ-መንግሥት የፅሕፈት ቤት ሐላፊ ሚኒስትር የነበሩት ሩዶልፍ ዛይተርስ በጣም ስራ የበዛበት ግን አስደሳች ሳምንት አሳልፈዋል። ለመራሔ-መንግስት ሄልሙት ኮል ታማኝ ሰራተኛ በመሆን ባለፉት አስራ ሁለት ወራቶች የተከሰተዉን ሁሉ አይተዋል። ከዉህደቱ ድግስ አንድ ቀን ቀደም ብለዉ ያደሩት በርሊን ዉስጥ ባለዉ በዚያን ጊዜዉ፣ የመንግስት ስራ አስፈጻሚ ቢሮ ዉስጥ ነበር። እንቅልፍ በአይናቸዉ አልዞረም ነበር።«በኤንባሲ ዉስጥ ጥገኝነት ስለጠየቁት ወገኖች፣ ወደ ምዕራብ ጀርመን መጓዝ እንዲችሉ ስላደረኩት ድርድር፣ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃንስ ዲትሪሽ ጌንሸር፣ በፕራግ የጀርመን ኤንባሲ በረንዳ ላይ ስላደረጉት ንግግር፣ የጀርመን ግንብ እንደፈረሰ በጀርመን ምክር ቤት ዉስጥ ስላደረኩት ንግግር፣ ሄልሙት ኮል በዋርሶ እንደነበሩ፣ ከዝያም በድሪስደን ፍራዉን ኬርሸ በሚባለዉ ጥንታዊ ቤተክርስታያን አካባቢ፣ ታላቅ ታሪካዊ ንግግር ስለማድረጋቸዉ ሳሰላስል ነዉ ያነጋሁት» ይላሉ-እሳቸዉ።

Helmut Kohl Rudolf Seiters
ኮልና የፅሕፈት ቤታቸዉ ሐላፊ ሩዶልፍ ዛይተርስምስል AP

323 የዉጥረትና አጓጊዎቹ ዕለታት

የበርሊኑ ግንብ ከተደረመሰ-ጀርመን በይፋ ዳግም እስከ ተዋሐደችበት እስከ ጥቅምት 3: 1990 ((እ.ጎ.አ.) ድረስ 323 ቀናት አለፉ። ለሁለቱ የጀርመኖች ፖለቲከኞች፣ ቀናቱ፣ ዉስብስብ ድርድር የተደረጉባቸዉ እና ከባድ ዉሳኔዎች ያሳለፉባቸዉ ነበሩ። ከሁሉም በላይ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጀርመን ብዙ ለዉጦች ተደርገዉ በአዲስ መንገድ ጉዞ ጀምራለች። ድሮ ከምትመራበት ከሶሻሊስቱ ርዕዮተ-ዓለም በመዉጣት ከፊደራል ጀርመን ጋር ለመዋኸድ እንዲያስችላት ፊደራላዊ የሆነ መንግስት እ.ጎ.አ በ 1990 በመቋቋም አዲስ የፌደራል ክፍለ-ግዛቶችንም መስርታለች። በዚሕ ሒደት የምስራቅ ጀርመን የስለላ ድርጅት ፈርሶአል። የፊደራል ጀርመን የመገበያያ ገንዘብ ዲ-ማርክ፣ የምስራቅ ጀርመን የመገበያያ ገንዘብ ሆነ። የጀርመን መንግስት ይህን ሁሉ በጥድፍያ ለመስራቱ ምክንያት ነበረዉ። በምስራቅ አዉሮጳ ዉስጥ የለዉጥ እንቅስቃሴ ከጀመረ ጀምሮ፣ አዉሮጳ እረፍት አጥታ ከርማለች። በተለያዩ ቦታዎች፣ ህዝብ ከቦታ ቦታ በነፃ መንቀሳቀስ እንዲችል እንዲሁም የአመራር እና የፖለቲካ ለዉጥ እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረቡን ቀጥሏል።

Gorbatschow und Weizsäcker
ጎርቫቾቭና ቫይትሴከርምስል REGIERUNGonline/Reineke

በሶቭየት ህብረት «ግላስኖስት እና ፔሪስትሮይካ» የተሰኘዉ መርሕን ተከትሎ በከፍተኛ ፍጥነት በመዘመት ላይ የነበረዉ እንቅስቃሴ፣ ብዙዎቹን የምሥራቅ አዉሮጳ ሐገራት እያዳረሰ ነበር።የቀድሞ የምዕራብ ጀርመን መራሔ-መንግሥት የፅሕፈት ቤት ጉዳይ ሐላፊ ሩዶልፍ ዛይተርስ «በዝያን ወቅት ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንቅስቃሴ ነበር፣ ይህ የለዉጥ እንቅስቃሴ ሞስኮ ብቻ ሳይሆን በብዙ ምዕራብ አዉሮጳ አገራትም ከፍተኛ ፍርሃትን አስከትሎ ነበር» በማለት ያስታዉሱታል።


የዉሕደት መስኮት

የጀርመኖች መዋሐድን መፈለጋቸዉ በአንዳንድ የአዉሮጻ መንግስታት ዘንድ ጥርጣሪን አስከትሎ ነበር። በመሃል አዉሮጳ አንዲት ጠንካራ ጀርመን መመስረቷ ከፍተኛ ስጋትን ቀስቅሶአል።የያኔዋ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርጋሪት ታቸር፣ ጀርመንን ዉሕደት በግልጽ ተቃዉመዋል። የፈረንሳዩም ፕሪዝደንት ፍራንስዋ ሜትሯምም በዉህደቱ ብዙ ደስተኛ አልነበሩም።ሶቭየት ህብረት ዉስጥም በአዉሮጳ ያለዉ ለዉጥ ቅራኔን አምጥቶአል። ምክንያቱም አለምን ሲቆጣጡ የነበሩ በአገሮች ላይ ያላቸዉን ሃያልነት እያጡ መጡ። የካፒታሊስት አገራት የኔቶ አባል እንደሆኑት ሁሉ ያንን በመስተካከል የዋርሶን የጦር ስምምነት ያደረጉት የሶሻሊስት ርእዮተ-አለም የሚከተሉ አገሮች በሶቪየት ህብረት ስር መሆንን ባለመፈለግ እያፈነገጡ መዉጣት ጀመሩ። በዚሕም ምክንያት በፕሬዝዳንት ጎርባቾቭ መንግስት ላይ ግልበጣ ቢደረግ የጀርመን ዉህደት አጠራጣሪ ሊሆን ይችላል በሚል ምዕራባዉያን ስጋት ዉስጥ ወድቀዉ ቆይተዋል።

Bildgalerie Helmut Kohl und Mitterand
ሄልሙት ኩልና ፍራንስዋ ሚትራምስል AP


የጀርመን ዉህደት በአለም የፖለቲካ መድረክ

ጀርመናዉያን እደለኞች ናቸዉ። ምክንያቱም በይፋ በተዋሐዱበት እ.ጎ.አ በ1990 በአለም ዉስጥ የተፈፀመ ታላቅ ፖለቲካዊ ታሪክ የነሱ ብቻ ነበርና። በዚህም በዚያን ጊዜ ከጀርመን ዉሕደት በስተቀር አለምን የሳበ ምንም አይነት የፖለቲካ ትኩረት አልነበረም። ከዚያን ጊዜዉ ትንሽ ዘግየት ብሎ ቢሆን ኖሮ፣ የአለምን ፖለቲካዊ ትኩረት በኢራቅ ላይ ያነጣጥር ነበር።ይኸዉም እ.ጎ.አ 1990 ኢራቅ ኩየትን ወርራ የራሴ ግዛት-አካል ነች በማለት በሐይል መቆጣጠሯ አለም ወደ ኢራቅ ፊቱን እንዲመልስ አድርጎታል። ሌላዉ እ.ጎ.አ 1991 አጋማሽ ላይ የሶቭየት ሕብረቱ ቀዩ ጦር አንዳንድ ጀነራሎች ሚኻኤል ጎርባቾቭን ከስልጣን ለማስወገድ ያደረጉት ሙከራ አለም ዳግም እስትንፋሱን ለጥቂት ጊዜ እንዲያቋርጥ አድርገዉት ነበር። ይህ ክስተት ጀርመን ከመዋሃድዋ አንድ አመት በፊት ቢፈጸም ኖሮ፣ ዳግም ዉህደቱ ዉስብስብ እና ረጅም ጊዜ የሚፈጅ፥ አሰልቺም ይሆን ነበር።በዚህም ጀርመን በተዋሃደችበት ወቅት የአለምን የፖለቲካ መድረክና ትኩረት ብቻዋን መቆጣጠር ችላለች።

Dresden Deutsche Einheit
ጥቅምት 2፦1990 ማታ-የዉሕደቱ ፌስታ በድሬዜደን ከተማምስል picture-alliance/ZB


የጀርመን ምክር ቤት

ማታ የተተኮሰዉ የርችት ፍንጥቅጣቂ በየመንገዱ ትቶ ያለፈዉ ቆሻሻ ገና ተጠርጎ አልተነሳም። በጥዋት የምዕራብ ጀርመን የፓርላማ አባላት እና የሶሻሊስት ጀርመን ፖለቲከኞች በጋራ ተሰባስበዉ ዉይይታቸዉን አካሂደዋል።ከዚሕም ከሁለት ወራት እንዳለፈ ሁለቱ ጀርመኖች እ.ጎ.አ ከ1932 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በጋራ የምክር ቤት አባላት ምርጫ አደረጉ። በምርጫዉም የክርስትያን ዲሞክራቲክ እና የነጻ ዲሞክራቲክ ፓርቲዎች ጥምር መንግስት ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት አሸነፈ።፣ሄልሙት ኮልም በመሪነታቸዉ ቀጠሉ።

ማቲያስ ፎን ሔልፌልደ
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ