1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

SKA ለአፍሪቃ ሳይንስ ያሳደረው ተስፋ፣

ረቡዕ፣ ግንቦት 22 2004

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ፣ የሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን፤ ለአፍሪቃ ሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ዕድገት ፣ እጅግ ከፍ ያለ አስተዋጽዖ ያደርጋል ተብሎ በጉጉት ይጠበቅ ስለነበረው፣ ደቡብ አፍሪቃ፣ ከተፎካካሪዋ አውስትሬሊያ ጋር በእጩነት

https://p.dw.com/p/154wv
ምስል picture-alliance/dpa

ስለቀረበችበት ፣ የ SKA ፕሮጀክት የይሁንታ ውሳኔ መዘግየት ማውሳታችን አይዘነጋም። ይሁንና ፣ በ ሁለት ቀናት ልዩነት አምስተርዳም ፤ ኔደርላንድ ውስጥ በተካሄደ ስብሰባ፤ የፕሮጀክቱ ተመልካች አካል፣ ጥያቄው፣ የመጨረሻውን ውሳኔ እንዲያገኝ አብቅቷል። ባለፈው ዓርብ ፤ የተላለፈው ሰሎሞናዊ መሰል ብይንም ሆነ ውሳኔ ፣ ሰናይ ዜና እንደነበረ አልታበለም።

የቀረበው የ SKA ፕሮጀክት፤ ማለትም በዓለም ውስጥ እስካሁን ወደር ያልተገኘለት ኅዋን የሚያስስ የሩቅ ማሳያና ማዳመጫ ረቂቅ ቴሌስኮፖች የሚተከሉበትን ጣቢያ በተመለከተ ፣ የጉባዔው ተሳታፊዎች፤ በአመዛኙ ፣ ለደቡብ አፍሪቃ ላቂያ ሰጥተው መምረጣቸው፣

Protea Südafrikas Wappenblume
ምስል picture-alliance/dpa

«የ SKA አስተናጋጅ ከሆንን ለአፍሪቃ የሳይንስና ፈጠራ ችሎታ ዐቢይ ዕድል ይሆናል» ያሉትን ፕሬዚዳንት ጄኮብ ዙማን ጨምሮ የዚያችን አፍሪቃዊት ሀገር፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኀላፊዎችንና አፍሪቃውያን ተመራማሪዎችን ሁሉ እጅግ ማርካቱ አልቀረም። ባለፈው ረቡዕ ዝግጅታችንም፤ ውሳኔው ፣ የደቡብ አፍሪቃን ጥያቄ በአወንታዊ መልኩ ከመለሰ ፣ ለአፍሪቃው ክፍለ ዓለም ምን ዓይነት ትርጓሜ ሊኖረው እንደሚችል፤ ከፕሪቶሪያው የእስዋኔ ዩኒቨርስቲ፣ ሁለት ምሁራንን ማነጋገራችን ይታወስ ይሆናል። ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ባንኮች በተገኘ ድጋፍ እውን ከሚሆነው የ SKA ፕሮጀክት ኀላፊዎች መካከል፤ John Womersley----

«ባለፈው ዐሠርተ-ዓመት፤ ከተከሠቱት እጅግ አስገራሚ ግኝቶች አንዱ፣ 95 ከመቶው ፍጥረተ ዓለም፣ ከአቶም የተፈጠረ አለመሆኑ ነው። የሚታወቀው የ 19 ወይም 20 ከመቶው ክፍል ብቻ ነው። እንደ እኔና እንደ እናንተ፣በጊዜያት እርከን ፣ ከተለያዩ ንጥረ ነገሮች የተገኘ አይደለም ። በኅዋ ፣ «ጥቁር ነገር» እና «ጽልመታዊ ኃይል ምንጭ » የምንለው ያልታወቀው ነገር የተፈጠረው፣ ከየት እንደመጣ አንዳች የምናውቀው ጉዳይ የለም። ይህን ለመግለጽ የሚያስችል ነባቤ ቃልም የለንም። ለዘመናዊው ፊዚክስ፤ አሳሳቢ ፈተና ሲሆን፤ ይኸው SKA ደግሞ፤ ለተነሱት ጥያቄዎች መልሱንም ሆነ ግንዛቤውን እንድናገኝ፣ አብነቱ ያለው በዚህ መሣሪያ ነው።»

ኅዋን ይበልጥ ጠለቅ አድርጎ ለማሰስና በአጠቃላይ ለሥነ ፈለክ ምርምር ሰፊ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው የታመነበት፣

Nelson Mandela
ምስል DW/AP

«እስኩየር ኪሎሜትር አሬይ» በሚገባ ሲደራጅ ፣ ወይም ፕሮጀክቱ በተሟላ ሁኔታ ሥራውን ሲጀምር ፤ አውስትሬሊያ ውስጥ ፣ በይበልጥ ደግሞ በደቡብ አፍሪቃ፣ ፤ ከሩቅ ድምጽ የሚቀበሉ ፣ እያንዳንዳቸው 15 ሜትር ስፋት ያላቸው ፣ በጠቅላላ 3000 «የኤሌክትሮኒክስ ጆሮዎች» ሊባሉ የሚችሉ ትላላቅ እንቅብ መሰል ሳህኖች(DISHES) ወይም (አንቴናዎች)ይተከላሉ። ኅዋን ለማሰስ፣ በደቡብ አፍሪቃና በአውስትሬሊያ እንዲሁም ኒው ዚላንድ የሚተከሉት አዲሶቹ ቴሌስኮፖቹ ፣ ከዚህ ቀደም ከተሠሩት ተመሳሳይ ዘመናዊ መሣሪያዎች፤ 50 እጥፍ ጥንካሬና 10,000 እጥፍ ፍጥነት ይኖራቸዋል። ፕሮጀክቱ ፤ በአጠቃላይ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚያስወጣ ነው። ያም ሆኖ ደቡብ አፍሪቃ ራሷ ለፕሮጀክቱ 2,5 ቢሊዮን ዩውሮ የመደበች ስትሆን፤ የፕሮጀክቱን አውታሮች ለመንከባከብም በያመቱ 100 ሚሊዮን ዩውሮ ለማውጣት ዝግጁ መሆኗ ታውቋል።

ሁለቱም አገሮች፣ ፕሮጀክቱን ብቻ ለብቻ ለማካሄድ እስከመወዳደር ደርሰው እንደነበረ ቢታወቅም ፤ ከሞላ ጎደል፣ «ሰሎሞናዊ» በመሰለው ውሳኔ ሳይረኩ እንዳልቀሩ ነው የተነገረው። የደቡብ አፍሪቃ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስትር ፤ ወ/ሮ ናሌዲ ፓንዶር፤--

ውሳኔው ፣ለደቡብ አፍሪቃ የሳይንስ ጠበብት፤ ለራሷ ለደቡብ አፍሪቃና ለመላው አፍሪቃ አስደሳች መሆኑን፣ ሙሉ በሙሉ ለደቡብ አፍሪቃ እንዲወሰን ይሹ እንደነበረ ፤ ሆኖም፤ ¾ኛውን ድጋፍ ማግኘቱም ጥሩ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ከምሁራኑም ፣ የእስዋኔ ዩኒቨርስቲ ባልደረባና የደቡብ አፍሪቃ የሳይንስ አካደሚ አባል ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ እንዲህ አክለውበታል----።

Naledi Pandor und Peter Frankenberg
ምስል Wolfram Scheible / SAP AG

ኢጣልያን የተጠናወተው የምድር ነውጥ፣

በሰሜን ኢጣልያ ኤሚሊያ የተባለውን ክፍለ-ሀገር፣ በአንድ ወር ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ትናንት ያርገፈገፈው የምድር ነውጥ ፤ እስካሁን የ 16 ሰዎችን ህይወት መቅጠፉ ታወቀ። ደብዛው የጠፋ አንድ ሰው እየተፈለገ ነው። በግምት 350 ሰዎች የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን፤ 10,000 የሚሆኑ መጠጊያ አልባ ቀርተዋል። በ RICHTER መለኪያ 5,8 ኃይል የነበረው ነውጥ ጉዳት ያደረሰባቸውን ሰዎች ለመርዳት ጠ/ሚንስትር ማሪዮ ሞንቲ ከሚንስትሮች ም/ቤት ጋር መክረዋል።

ግንቦት 12 ቀን 2004 ሰሜን ኢጣልያን ያናወጠው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ ከ 1300 ዓ ም ወዲህ በኀያልነቱ የመጀመሪያው ነው ተብሏል በሪተር መለኪያ 6 ነበረና!

ባለፈው ሳምንት በደረሰው ነውጥ 7 ሰዎች መሞታቸውና 50 ያህል መቁሰላቸው የሚታወስ ነው። የአያሌ ምዕተ-ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠሩ ታሪካዊ ህንጻዎች ፈርሰዋል። ትናንት ከላካሰምበርግ ጋር የወዳጅነት ግጥሚያ ሊያደርግ የነበረው የኢጣልያ ብሔራዊ የአግር ኳስ ቡድን መሠረዝ ግድ ሆኖበታል። ኢጣልያ ፣ ያለማቋረጥ እሳት የሚተፋው ደብረ ኤትና የሚገኝባት ሀገር ስትሆን፤ ፣ በተለያዩ ዘመናትም ከምድር ነውጥና እሳተ ገሞራ ጋር የተያያዙ ፣ አደጋዎች ያጋጠሟት መሆኑን ከታሪክ መረዳት ይቻላል።

Israel Totes Meer
ምስል AP

ስለምድር ነውጥ ከተነሣ ፣ በ 26 እና 36 ዓ ም መካከል እሥራኤል ውስጥ፤ ከኢየሩሳሌም ፣ 20,8 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በሙት ባህር አካባቢ አጋጥሞ የነበረው የምድር ነውጥ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን ትክክለኛ ዕለት ለማወቅ አስተዋጽዖ አድርጓል ሲሉ የአሜሪካ የሥነ ምድር ተመራማሪ Jefferson Williams እና የጀርመን የሥነ ምድር ባለሙያዎች Markus Schwab እና Achim Bauer አስታወቁ። ጠበብቱ ይህን ያሉት ሙት ባህር ጠረፍ ዐይን ገዲ በተባለው ለመዝናኛ በተመደበ ቦታ ፤ በእርከን የአፈርና ቋጥኝ ምርምር ካደረጉ በኋላ ነው። ተመራማሪዎቹ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ 31 ዓመተ-ዓለም ከዚያም በ 26እና 36 ዓ ም መካከል፣ የመጀመሪያው የዚያ ምዕተ-ዓመት ነውጥ ማጋጠሙን ገልጸዋል። ጀፈርሰን ዊልያምስ ፣ ክርስቶስ ፤ በዕለተ ዓርብ ተሰቅሎ የሞተው፣ 4ቱም ወንጌላውያን ፤ ሜቴዎስ፤ ማርቆስና ሉቃስ በአይሁድ ቀን መቁጠሪያ፣ «ኒሳን» በ14ኛው ቀን የፋሲካ ቂጣ ከመባላቱ በፊት ማታውኑ መሆኑን ያረጋግጣሉ ፤ ይህ ደግሞ ከሞላ ጎደል ፍጹም ትክክለኛ መሆኑ ተደርሶበታል ያላሉ። ዮሐንስ ብቻ ቀኑን 15 አድርጎታል። ይሁንና ፤ የአይሁድን ቀን መቁጠሪያ ከሥነ ፈለክ ስሌት ጋር በማዛመድ ጥቂት አማራጭ ቀናት ቢወሱም፤ በትክክል የሚገጣጠመው ከ ሚያዝያ 3 ቀን 33 ዓመተ ምኅረት ጋር ነው ሲሉ ተመራማሪዎቹ አስረድተዋል።

Ausstellung Die Neuen Hebräer in Berlin
ምስል AP

ጀፈርሰን ዊልያምስና ቡድናቸው፤ ከስቅለት በፊት ወይም በኋላ የተከናወኑ የተከሠቱ የምድር ነውጦች እንደነበሩ ይታወቃል ብለዋል። ማቴዎስ በወንጌሉ የሚለው ፤ እንዲሁም፤ በ 26 እና በ36 ዓ ም በአካባቢው ያጋጠመው ነውጥ፣ በዐይን ገዲ ጠረፍ የአፈርና ቋጥኝ እርከንን እጅግ ያዛባ ነበረ ወይስ የማቴዎስ የአገላለጽ ዘይቤ ነው? ምርመራው መቀጠል ያለበት ነው ባይ ናቸው። በዕለተ ስቀለት ፤በተፈጥሮ ስለመከሠቱ የተገለጠው የቀን ጨለማም በመመራመር ላይ መሆናቸውን ዊልያምስ ተናግረዋል። ከእኩለ ቀን እስከ 9 ሰዓት ለ 3 ሰዓት ሰማዩ ጨልሞ እንደነበረ 3ቱ ወንጌላውያን የጻፉት፣ ዊልያምስ እንደሚያምኑት፣ መንስዔው የአቧራ ማዕበል ነው። በመጀመሪያው ምዕተ-ዓመት ፣ በኢየሩሳሌምና አካባቢዋ በደረሰ የምድር ነውጥ ፤ በማዕበል ሳቢያ የተጠራቀመ የአቧራ ክምችት አለ የለም? ጀፈርሰን ዊልያምስ ፣ እንዳስታወቁት ምርምራቸውን ይገፉበታል።

ተክሌ የኋላ፣

ሒሩት መለሰ