MNLA ዘመቻው አበቃ አለ
ሐሙስ፣ መጋቢት 27 2004ሰሜን ማሊን ከተቀረው ማሊ ለመገነጠል የሚታገለው የማሊ ብሔራዊ ነፃ አውጭ ጦር በእንግሊዘኛው ምህፃር MNLA አማፅያን በሰሜን ማሊ የተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ማብቃቱን አስታወቁ ። እንደ አማፅያኑ አዝዋርድ የሚል ስያሜ የሰጡትን ግዛት ለመመስረት ያካሄዱት ትግል ግቡን በመምታቱ ውጊያ አብቅቷል ። MNLA በድረ ገፁ ትናንት በአገሩ ሰዓት አቆጣጠር እኩለ ለሊት ላይ ዘመቻው አብቅቷል ሲል መወሰኑን አስታውቋል ። ቡድኑ በዚሁ መግለጫው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአዝዋርድ ጥበቃ እንዲያደርግም ጠይቋል ። የአፍሪቃ ህብረትም ሆነ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰሜን ማሊን መገንጠል አይደግፍም ። ፈረንሳይ በቱአሬጎች ለሚመራው አመፅ መፍትሄው ፖለቲካዊ ድርድር ነው ስትል አስታውቃለች ። በአካባቢው በመስፋፋት ላይ ያለውን አልቃይዳን ለመዋጋት የአካባቢው ሃገሮች በትብብር እንዲንቀሳቀሱ ጠይቃለች ። በሌላም በኩል ፈረንሳይ በኃይል ሥልጣን የያዘውን ወታደራዊ ደርግ ለማስወገድ የአፍሪቃ ኃይሎችን ለመርዳት ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች ።
የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አለን ዡፔ ሃገራቸው ለዚሁ ዓላማ ሎጂስቲካዊ እርዳታ እንደምትሰጥ ሆኖም ወደ ቀድሞ ቅኝ ግዛቷ ወታደሮቿን እንደማትልክ ተናግረዋል ። ይህ በእንዲህ እንዳለ በሰሜን ማሊው ግጭት ቁጥሩ ወደ 2 መቶ ሺህ የሚደርስ ህዝብ መፈናቀሉ ተዘግቧል ። ከአካባቢው የተፈናቀሉት እንደሚናገሩት ብዙ ጥፋት ደርሷል ።
« ብዙ ጥፋት ደርሷል ። እዚያ በአካል እስካልተገኙ ድረስ ሁኔታውን መረዳት አይቻልም ። ብዙ ሰዎች ሞተዋል ። ምግብ የለም ፤ እሌክትሬክ የለም ፣ ሌሎችም ብዙ ነገሮች የሉም ። መውጫ መንገድህን ፈልገህ እግዚአብሔርን ማመስገን ነው ። »
ወታደራዊው ደርግ ባማኮ ተረጋግታለች ቢልም በዚያም ቢሆን የፀጥታ ዋስትና አለመኖሩን ይሰማል ። የነዳጅ ዘይት ና የአንዳንድ ሸቀጦች እጥረት ተከስቷል ።
በሌላ በኩል ከ 2 ሳምንት በፊት በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዘው የማሊ ወታደራዊ ጁንታ የኃያላኑን ምዕራባውያን መንግሥታት እርዳታ ተማፀነ ። የጁንታው የበላይ ሻምበል አማዱ ሳኖጎ ለሞንድና ሊቤራስዮን ለተባሉት የፈረንሳይ ጋዜጦች በሰጡት ቃለ ምልልስ በቱአሬግ አማፅያን እጅ የወደቀውን ሰሜን ማሊን መልሶ ለመቆጣጠር የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ እገዛ እንደሚያሻቸው አስታወቀዋል ። ሳኖጎ ኃያላኑ መንግሥታት አክራሪዎችን ለመዋጋት ውቅያኖስ ተሻግረው አፍጋኒስታን ድረስ ጦር ማዝመት ከቻሉ እኛስ ጋ መምጣት ምን ያግዳቸዋል ሲሉም ተናገረዋል ። በዚሁ ቃለ ምልልስ ወታደራዊው ደርግ ለማሊ የተሻለው ሁሉ እንዲደርግ እንደሚፈልግም ያሳወቁት ሳኖጎ የሚታወቀው ጠላት ርዐስ ከተማ ባማኮ ስለሌለ ጣልቃ ገብነቱ በሰሜን ማሊ መሆን ይኖርበታልም ብለዋል ።
የውጭ ኃይላት የቱአሬግ አማጽያን ግስገሳ እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል ። ያም ሆኖ ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ሳንጎን ለሥልጣን ያበቃውን የዛሬ 15 ቀንኑን መፈንቅለ መንግሥት አውግዟል ። ሳኖጎ በአሁኑ ጊዜ በባማኮ ህይወት እንደ ቀድሞው የቀጠለ መሆኑና ምንም ዓይነት ቀውስ እንደሌለ ፤ ወታደራዊው ደርግም አክብሮት እንደተቸረው ተናግረዋል ። በሰሜን ማሊ ግን ሁኔታው አንገብጋቢ መሆኑን አስረድተዋል ። ሻምበል ሳንጎ በሮች ሁሉ ለውይይት ክፍት መሆናቸውን አስታውቀው ሆኖም በማሊ ሉዓላዊነት ላይ ግን ምንም ዓይነት ድርድር እንደማያካሂዱ አስታወቀዋል ።