1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

DW እና የገጠመው የሥርጭት እክል፧

ሐሙስ፣ ኅዳር 12 2000

DW ራዲዮ የአማርኛው አገልግሎት፧ ሥርጭቱ ሆን ተብሎ እንዲሠናከል እየተደረገ ስላለበት ሁኔታ ከክፍሉ ኀላፊ፧ Herr Ludger Schadomsky ጋር ተክሌ የኋላ ያደረገው ቃለ-ምልልስ፧

https://p.dw.com/p/E0X2
ምስል DW / Kisner

DW የአማርኛው አገልግሎት ለኢትዮጵያ አድማጮቹ የሚያስተላልፈው ሥርጭት፧ ሆን ተብሎ አጨናጋፊ፧ የመሰናክል እርምጃ ከተወሰደበት ቀናት አልፈዋል። አድማጮቻችን አዝነዋል፧ ቅሬታም እያሰሙ ነው፧ ስለተፈጠረው ሁኔታ ምን ይላሉ?
«ይህ በእርግጥ በፕረስ ነጻነት ላይ የተሠነዘረ አሳሳቢ እርምጃ ነው። በዚህ በአሁኑ ወቅት፧ ይህን ሥርጭት የማሰናከል እርምጃ በመውሰድ ላይ ያለ፧ ሆን ብሎ የሚያካሂደው ማን እንደሆነ አላወቅንም። በአካባቢው የፕረስ ነጻነትን የሚያርቅ፧ ኀላፊው ማን እንደሆነ አላውቅነውም። ይሁንና ሁኔታውን በጥሞና በመከታተል፧ የሚያሠናክለው ተጻራሪ አሠራጭ ጣቢያ ከየት በኩል እንደሆነ፧ መረጃ ለማግኘት ጥረት በማድረግ ላይ ነን። ከ ኅዳር 1 ቀን 2000 ዓ ም አንስቶ ሥርጭት የማሠናከል እርምጃ መወሰዱን፧ ለመገንዘብ ችለናል። ትናንት ረቡዕ፧ በተጨማሪ ያስተዋወቅነው 3ኛ ማሠራጫ የሞገድ መሥመርም መሰናክል ተፈጥሮበታል። እርምጃው በአጠቃላይ በሚገባ ትኩረት የተደረገበት ነው የሚመስለው። የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮም 3 የሞገድ መሥመሮቻቸው ሆን ተብሎ መሰናክል ተፈጥሮባቸዋል።በአጭሩ ለማጠቀለል፧ ይህ በእርግጥ በፕረስ ነጻነት ተመርኮዞ፧ መረጃዎች በሚያቀርበው በጀርመን የአጭር ሞገድ ሥርጭት ላይ የተሠነዘረ ጥቃት ነው።«
ይህ የማሰናከያ እርምጃ በዚህ ወቅት የተወሰደበት ምክንያት ምን ይሆናል ብለው ያስባሉ?
«ይህ በእውነቱ፧ ሁላችንም፧ አሜሪካ ያሉ የሙያ ባልደረቦቻችን ጭምር የምናቀርበው ዐቢይ ጥያቄ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ግምት ብቻ ነው መግለጽ የሚቻለው። ሁለት ዐበይት ጉዳዮች አሉ፧ በየጊዜው የሚወሱ። በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው የድንበር ውዝግብ፧ እንደምታውቀው፧ ኅዳር 20 ቀን 2000 ዓ ም፧ ድንበር ማካለሉን የተመለከተ አሳሳቢና ወሳኝ ሁኔታ ይጠበቃል። የሶማልያው ውዝግብም ሌላው ጉዳይ ነው። አያሌ ወራት በዚህ ነጥብ ዙሪያ ዘገባ ስናቀርብ ቆይተናል። እነዚህ፧ በጥሞና የሚታዩ አሳሳቢ ጉዳዮች ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ሁለት ውዝግቦች፧ የተሣሠሩ ናቸው ብሎ መገመት ይቻል ይሆናል። እዚህ ላይ በአጽንዖት መግለጽ የምፈልገው፧ በዚህ በአሁኑ ቅጽበት፧ የማሠራጫ መሞገድ መሥመሮቻችንን፧ ማን እንደሚያሠናክላቸው ያገኘነው መረጃ እንደሌለ ነው።«
የኢትዮጵያ አድማጮች ነጻ የመረጃ አገልግሎት የማግኘት መብታቸውን ተገፈዋል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ፧ የ DW መመሪያና እርምጃ ምንድን ነው?
«DW የሥራ አመራሩ፧ በጥሞና ነው ጉዳዩን በመከታተል ላይ ያለው። ኅዳር 6 ቀን 2000 ዓ ም፧ የዶይቸ ቨለ ዋና ሥራ አስኪያጅ Herr Erik Bettermann በርሊን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ደብዳቤ በመጻፍ ሥርጭታችን የተጓጎለበትን፧ እንቅፋቱን በማስወገድ ረገድ እንዲተባበር ጠይቀዋል። ይህን ሲያደርጉ፧ መሰናክል መፈጠሩን ነው ያወሱ እንጂ፧ እንከን ፈጣሪው ማን እንደሆነ ያወሱት ጉዳይ የለም። ደብዳቤ የጻፉትም፧ ችግር ያጋጠመ መሆኑን ኤምባሲው እንዲያውቀው ለማድረግ ነው። ከዚህ በተረፈ፧ ዶይቸ ቨለ፧ ሥርጭቱን የሚያሠናክልበትን አውታር ለይቶ ለማወቅ በቴክኒክ ረገድ የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ ነው። ከዚያም አስፈላጊ የሆነውን እርምጃ ይወስዳል፧ ምክንያቱም፧ መረጃ የማቅረብ ግዴታችንን መወጣት ይኖርብናልና ነው። በተለይ፧ የፕረስ ሳንሱር በሚደረግበት አካባቢ፧ ነጻ መረጃ የማቅረብ ኀላፊነት እንዳለብን ይሰማናል።«
አድማጮቻችን እያዘኑም፧ እያማረሩም ነው። «የማሠራጫ ሞገድ መቀያየሩ ዋጋ የለውም፧ መላ ፈልጉ!« እያሉን ነው። እርስዎ ምን ይሏቸዋል?
«ይገባኛል፧ እውነት አላቸው። በዚህ ቅጽበት፧ አድማጮችንን፧ ይቅርታ ነው የምንጠይቀው። የሥርጭት ሞገድ መሥመሮቻችን የተሰናከሉት በኛ አይደለም። የሥራ ውጤታችን ሠምሮ እንዲቀርብ፧ አጥብቀን እንፈልጋለን። ነጻ መረጃ ማግኘት፧ ቀላል ባልሆነበት አካባቢ፧ ለሥራችን ላቅ ያለ ትርጉም ነው የምንሰጠው። ስለሆነም፧ እንዳልኩት፧ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። አዋኪው አውታር፧ ዬት እንደሆነ ለማወቅና መሰናክሉም እንዲነሣ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። በዚህ ቅጽበት ማለት የምንችለው፧ በአማራጭ ሞገዶች ለመጠቀም መጣር የሚበጅ መሆኑን ነው። እርግጥ ነው፧ እነዚህም የሚሠናከሉበት እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል እናውቃለን። በአሁኑ ወቅት አድማጮቻችንን፧ የምንለምናችሁ፧ የችግሩን መንስዔ፧ (የማሠራጫ የሞገድ መሥመሮቻችን የሚታወኩበትን) ለይተን፧ ተስፋ አለኝ መፍትኄም እስክናገኝለት፧ በተጠጋጉ የሞገድ መሥመሮች፧ ራዲዮ እየጎረጎራችሁ ለማዳመጥ እንድትሞክሩ ነው።«