1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጉባኤዉ ተግባራዊ ዉጤቶች ይጠበቅበታል፤

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 28 2010

የጀርመኗ ቦን ከተማ የምታስተናግደዉ የአየር ንብረት ለዉጥ ተመልካች ጉባኤ በትናንታዉ ዕለት በይፋ ተጀምሯል። ጉባኤዉ ከሁለት ዓመታት በፊት ፓሪስ ላይ ሃገራት የተስማሙበት የበካይ ጋዝ ቅነሳ ዉል ወደተግባር የሚለዉጥ ዝርዝር አሰራርን የሚያመላክት ሰነድ ያወጣል ተብሎ ይጠበቃል።

https://p.dw.com/p/2n9qq
Cop 23, internationale Klimakonferenz in Bonn
ምስል DW/Eric Topona

የፓሪሱን ስምምነት ተግባራዊ የሚያደርግ ሰነድ ይጠበቅበታል፤

ከሁለት ዓመት በፊት ፓሪስ ላይ የተካሄደዉ ተመሳሳይ የተመድ አየር ንብረት ለዉጥ ተከታታይ ጉባኤ ከእስከዛሬዉ ድርድሮች ሁሉ የተሻለ እና ሃገራትን አግባብቶ አንድ ርምጃ ወደፊት ያራመደ እንደነበር አይዘነጋም። ያኔ ነዉ መንግሥታት በየግላቸዉ ከባቢ አየርን በካይ እና ሙቀት አማቂ ጋዞችን የመቀነስ ርምጃ ለመዉሰድ የተስማሙት። ከስብሰባዉ በኋላም በየሀገራቸዉ ዉሳኔዉን አስጸድቀዉ ባለፈዉ ዓመት መስከረም ወር ላይ ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ አብዛኞቹ መንግሥታት ለተመድ ዓመታዊ ጉባኤ ኒዉ ዮርክ ላይ ሲሰባሰቡ ይፋ አደረጉ። ይሁንና ብዙም ሳይቆይ ዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንቷን ለወጠች እና የአየር ንብረት ለዉጥ መኖሩን አላምንም የሚሉት ዶናልድ ትራምፕ መንበረ ስልጣኑን ተረከቡ። የእሳቸዉ መመረጥ ሲሰማም ሞሮኮ ማራካሽ ላይ ባለፈዉ ዓመት በዚሁ ወቅት ይካሄድ የነበረዉ 22ኛዉ የአየር ንብረት ለዉጥ ተከታታይ ዓለም አቀፍ ጉባኤ መደናገጥ ዉስጥ ገባ። በዚህም ምክንያት መገናኛ ብዙሃን ከጉባኤዉ ይልቅ አዲሱ የአሜሪካን ፕሬዝደንት ምን ያደርጉ ይሆን በሚል ግምት እና  መላ ምት ላይ ተጠመዱ። እንዲያም ሆኖ ግን ተደራዳሪዎቹ የፓሪሱን ስምምነት እንዴት ማጠናከር እንዳለባቸዉ ዉይይታቸዉን ቀጥለዋል። ትራምፕም ብዙም ሳይቆዩ ሀገራቸዉን ከፓሪስ ዉል ስምምነት አስወጡ። ያኔም የዉሉ ፈራሚ ሃገራት በፓሪሱ አቋማቸዉ ፀኑ። እስካሁንም ዉሉን አጽድቀዉ የፈረሙ ሃገራት ቁጥር 169 ደርሷል። የጀርመን የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ባርባራ ሂንድሪክስ ትራምፕ የወሰዱት ሀገራቸዉን የማስወጣት ርምጃ የተፈራዉን መዘዝ አለማምጣቱን የዘንድሮዉ ጉባኤ ማለትም COP 23 ከተከሰፈተ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዲህ ገልጸዉታል፤

«በዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ለየት ያለ ነገር እናስተዉላለን፤ ይኸዉም COP 23 ዩናይትድ ስቴትስ ከፓሪሱ ስምምነት ራሷን ካገለለች በኋላ የሚካሄድ የመጀመሪያዉ ጉባኤ ነዉ። ርምጃዉን በወሰደች አንድ ወር ገደማ፤ አንዱ ሌላዉን አስከትሎ የመንኮታኮት ማለትም ምናልባት ሌሎች ሃገራትም ይህንኑ ያደርጋሉ የሚስል ስጋት ነበር። ይህ አልሆነም እንዳይሆን በጋራ ብዙ ተሠርቷል እናም እስካሁንም ሁሉም በአንድነት ይገኛሉ። ከዚህ ተነስቼም በዚሁ እንደሚቀጥል መናገር እችላለሁ። በፖለቲካዉ ረገድ ከዚህ ከቦንም ቀሪዉ ዓለም አንድነቱን የሚያሳይ ምልክት እንደሚያስተላልፍ ይታመናል።»

Deutschland Pk zum Weltklimagipfel in Bonn
የጀርመን የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ባርባራ ሂንድሪክስምስል picture-alliance/dpa/S. Kembowski

እናም የዘንድሮዉ ጉባኤም ይህንን አቋማቸዉን አጠናክሮ በተግባር የሚገለፅበትን መስመር የማስያዝ ከፍተኛ ሥራ ይጠብቀዋል።  ቦን ላይ የተሰባሰቡት ዲፕሎማቶች እና የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች እንዲሁም በአየር ንብረት ለዉጡ መዘዝ ለጉዳት የተዳረጉ እና ስጋት ያጠላባቸዉ ሃገራት፤ መንግሥታት የተስማሙበትን ሙቀት አማቂ ጋዞችን የመቀነስ ቃል ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሏቸዉ ቴክኒካዊ ነጥቦች ላይ መወያየታቸዉን ይቀጥላሉ። የተመድ የአየር ንብረት ለዉጥ ማዕቀፍ ዋና ፀሐፊ ፓትሪሺያ ኢስፒኖሳ፤ ሁሉም ወገኖች የአየር ንብረት ለዉጡ እዉን መሆኑን ስለተገነዘቡ ከጉባኤዉ አንዳች ነገር ይወጣል የሚል ተስፋ ነዉ ያላቸዉ።

«ይህ ጉባኤ የተጀመረዉ በዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ እና ባጠቃላይ በሕዝቡ ዘንድ የአየር ንብረት ለዉጥ ስጋት እዉነት መሆኑን በተመለከተ ከፍተኛ ግንዛቤ በተፈጠረበት ወቅት ነዉ ብዬ አስባለሁ። ምን ያህል ሕይወት ሊያጠፋ እንደሚችል በኤኮኖሚዉም ቢሆን የሚያደርሰዉ ምን ያህል ኅብረተሰቡን እንደሚጎዳ እየታየ ነዉ። የካሪቢያን ሃገራትን ምን ያህል ክፉኛ እንደተመቱ መመልከት ይቻላል።»

COP 23 Bonn Weltklimakonferenz
የፊጂ ደሴት ነዋሪዎች ትርኢት ሲያቀርቡi፤ምስል Getty Images/AFP/P.Stollarz

የፊጂ ደሴት ነዋሪዎች ናቸዉ፤ ጉባኤዉ ትናንት ሲከፈት በባህላዊ አለባበሳቸዉ እንዳጌጡ በተመድ የስብሰባ አዳራሽ ተገኝተዉ ይህን ትርኢት ያቀረቡት። የዘንድሮዉ ጉባኤ ፕሬዝደንት የሆነችዉ የፊጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍራንክ ባይኒማራማ ቀጠሉ፤

«ሕዝቦቻችንን አናሳፍራቸዉ። ይህም ማለት መጪዎቹን ሁለት ሳምንታት እና ቀጣይ ዓመታት የፓሪሱ ስምምነት የሚሠራ እና እስከ ጎርጎሪዮሳዊዉ 2020ዓ,ም ድረስ የአየር ንብረትን የሚመለከተዉን ርምጃ የሚደግፍ እንዲሁም የሚያራምድ እንዲሆን የምንችለዉን ሁሉ እናድርግ። የፓሪሱ ስምምነት ያስቀመጣቸዉን ግቦች ለመምታት ማድረግ የሚገባንን ሁሉ በቁርጠኝነት ማድረግ እንጂ ወደኋላ ማለት የለብንም።» 

COP 23 ጉባኤ ትናንት በይፋ ይከፈት እንጂ ድርድሩ እና ዉይይቱ በተለያዩ ቡድኖች ደረጃ ለቀናት ሲካሄድ ነበር። በኢንዱስትሪ ያልበለፀጉ ሃገራት መድረክን በሊቀ መንበርነት የምትመራዉ ኢትዮጵያ ተደራዳሪ አቶ ገብሩ ጀምበር እንዳለዉ እንደገለፁልንም ለዚሁ ስብሰባ ዝግጅት ይረዳ ዘንድ ከሦስት ሳምንት በፊትም አዲስ አበባ ዉስጥም የባለሙያዎች እና ሚኒስትሮች ጉባኤ ተካሂዷል። በኢንዱስትሪ ያልበለፀጉት ሃገራት ከዚህ ጉባኤ ምን ይጠብቃሉ? ያልናቸዉ አቶ ገብሩ ምንም እንኳን ሃገራቱ የሚጠብቋቸዉ በሙሉ በአንድ ጉባኤ ዉጤት ያገኛሉ ባይባልም ቅድሚያ የሰጧቸዉ ጉዳዮች ግን ዘርዝረዋል።  

Deutschland Klimaziele der EU- Schriftzug «CO2» brennt
ምስል picture-alliance/dpa/U. Anspach

ከኮፐን ሃገኑ የአየር ንብረት ለዉጥ ተመልካች ጉባኤ ጀምሮ በኢንዱስትሪ ያደጉት ሃገራት 100 ቢሊየን ዶላር ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2020ዓ,ም አንስተዉ በኢንዱስትሪ ላላደጉት እና በአየር ንብረት ለዉጡ እየተጎዱ ላሉት ሃገራት በየዓመቱ ለመስጠት ከስምምነት ተደርሷል። እስካሁን ግን ቃል ከተገባዉ ገና ጥቂቱ ነዉ የተገኘዉ። የጉባኤዉ አስተናጋጅ ሀገር ጀርመን ለዚሁ ድጋፍ የሚዉል የ50 ሚሊዮን ዩሮ ተጨማሪ ገንዘብ እንደምትሰጥ አሳዉቃለች።

ጉባኤዉ በዚህ መልኩ ሲጀምር ታዲያ የድጋፍ ድምጾች ብቻ አይደለም የተሰሙት። 40 በመቶዉ የኃይል አቅርቦቷን ከድንጋይ ከሰል የምታመኘጨዉ ጀርመን CO2ን በከፍተኛ መጠን ወደከባቢ አየር የሚለቀዉ ይህን ስልቷን እንድታቆም ግፊት እየተደረገባት ነዉ። ከቅዳሜ ዕለት ጀምሮም ቦን እና የድንጋይ ከሰል ማዕድን በሚወጣበት በሃምባህ «ምድራችንን ታደጓት፤ ከሰልን አቁሙ» የሚሉ መፈክሮች የተስተጋቡበት ከፍተኛ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል። ትናንት የጉባኤዉ መክፈቻ ንግግሮች በተደረጉበት አዳራሽም ሕጻናት በሰልፍ ገብተዉ ተመሳሳይ ድምጻቸዉን አሰምተዋል።

UN-Klimakonferenz 2017 in Bonn | Demonstration & Protest
የድንጋር ከሰል መጠቀም ይቁም ከሚሉት ሰልፈኞች በከፊል፤ምስል DW/M.M. Rahman

በቀጣይም በርካታ ሰልፎች እንደሚኖሩ ይጠበቃል። ፖሊስ እዉቅና የሰጠዉ ለ11ዱ ነዉ ተብሏል። በተለይም የፊታችን ቅዳሜ ሁለት ትላልቅ ሰልፎች እንደሚካሄዱ ከወዲሁ ተገልጿል። ለሁለት ሳምንት በሚቆየዉ በዚህ ጉባኤ ላይ የአዉሮጳ ኅብረትን ጨምሮ ከ197 ሃገራት የተዉጣጡ 23 ሺህ ተሳታፊዎች እንዲሁም 1,500 ጋዜጠኞች በጉባኤዉ የመገኘት ፈቃድ አግኝተዋል። 500 መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ይሳተፋሉ። ኢትዮጵያም የመንግሥት ልዑካኗ እና ከሲቪክ ማኅበራት የተዉጣጡ ከ50 በላይ ተሳታፊዎች መላኳን ለመረዳት ችለናል።  እንግዶቹን በተለያዩ ዘርፎች የሚያስተናግዱ 5,000 ሠራተኞችም ተሠማርተዋል። ቁጥራቸዉ ሲታይም በጀርመን ሀገር እንዲህ ያለ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ሲካሄድ ይህ የቦኑ ጉባኤ COP 23 የመጀመሪያ መሆኑ ነዉ የሚነገረዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ