1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

7ኛው የዶይቸ ቬለ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን መድረክ

ሰኞ፣ ሰኔ 23 2006

ዶይቸ ቬለ በየዓመቱ የሚያዘጋጀው ዓለምአቀፍየመገናኛብዙኃንመድረክዛሬ ተከፈተ። በዚህ ሶስት ቀናት በሚቆየው መድረክ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ እስከ 2000 የሚደርሱ ተካፋዮች ይሳተፋሉ።

https://p.dw.com/p/1CSqu
GMF Global Media Forum 2014 Auftritt Bassem Youssef Saal Übersicht
ምስል DW/K. Danetzki

ይህ 7ኛው የዶይቸ ቬለ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን መድረክ ነው። በአዲሱ የጀርመን ስራ አስኪያጅ ፔተር ሊምቡርግ የተከፈተው መድረክ ዘንድሮ« ከመረጃ አቅርቦት እስከ ተሳትፎ- የመገናኛ ብዙኃን ተግዳሮት» የሚል ርዕስ ይዟል። «በአሁኑ ሰዓት በዮክሬይን እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በተጨባጭ ሁኔታ የሰው ህይወት የሚጠፋበት ድርጊት መሆኑ ቀርቶ የመረጃ ጦርነት ብንለው ይቀላል »ያሉት የሰሜን አትላንቲክ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት ምክትል ዋና ፀሀፊ ጃሚ ሺአ ናቸው። የደህንነት አስከባሪው ምሁር በዘንድሮው የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን መድረክ ተገኝተው ንግግር ከሚያደርጉ የክብር እንግዶች አንዱ ናቸው። እንደ ብሪታኒያዊው አመለካከት ወቅታዊ ቀውስ በሚስተዋልባቸው ዮክሬይን፣ ቱርክ እና በጸደይ አብዮት ሀገራት ኢንተርኔት ግጭቱ ያለውን ቅርፅ እንዲቀይር ብርቱ ሚና ተጫውቷል። ስለሆነም ኢንተርኔት ለመገናኛ ብዙኃን ምን አይነት ሚና ይጫወታል? የሚለው ሌላው የዚህ መድረክ ትኩረት ነው። ከሺአ ሌላ የኤድዋርድ ስኖደን በቅርብ አማካሪነት የምትታወቀው የብሪታንያ ጋዜጠኛ ሳራ ሀሪስ እና ሌሎችም በዚህ የዓለም አቀፍ የመረጃ ልውውጥ እንዴት የሰው ልጅን ደህንነት ማስከበር እና ጥቃትን መከላከል እንደሚቻል ይወያያሉ።

የዶይቸ ቬለ ዋና ስራ አስኪያጅ ሊምቡርግ ከጠዋቱ አራት ሰዓት ላይ የመድረኩ የክብር እንግዶችን እና ተሳታፊዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ ወዲያው ወደ መወያያ ርዕሱ ነው የገቡት።« ዛሬ ኢንተርኔት አማራጭ መረጃ ማግኛ እና መሳተፊያ መድረክ ነው። ህይወታችንን የቀየረ፣ የበለጠ ቀለም እና ሀብት የሰጠ ግኝት ነው። ኢንተርኔት በዓለም ዙሪያ ያለው እውቅና የእርስ በዕርስ ግንኙነትን አስፋፍቶ መረጃን እንዴት እንደምንፈጥር እና እንደምናገኝ ወስኗል። የአጥናፋዊ ትስስር የጀርባ አጥንት ሆኗል።ከዚህም ሌላ የእድገት፣ ትምህርት እና ለበለጠ ማህበራዊ ግንኙነቶች እድል ፈጥሯል። ኢንተርኔትን መፍራት አይገባንም ይልቁንስ ያለውን አቅም ዓለምን በበጎ ለመቀየር ልንጠቀምበት ይገባል።»

GMF Global Media Forum 2014 Intendant Peter Limbourg
የዶይቸ ቬለ ዋና ስራ አስኪያጅ ሊምቡርግ የመክፈቻ ንግግርምስል DW/K. Danetzki

ዛሬ በተከፈተው መድረክ በክብር እንግዳነት ተገኝተው ንግግር ካደረጉት አንዱ ባሴም ዩሴፍ ነው። ሀሳብን በምፀት በመግለጽ የሚታወቀው ግብፃዊው ሀኪም በተለይ በዓረቡ ሀገራት ይተላለፍ በነበረው የቴሌቪዥን ፕሮግራሙ ይታወቃል። ዩሴፍ ባደረገው ንግግር ፍርሃት ለምን ለዲሞክራሲና ነፃነት ትልቅ እንቅፋት እንደሆነ እንዲህ ነበር የገለፀው።

« ካሉ የጦር መሳሪያዎች ሁሉ ስኬታማው ፍርሃት ነው። ፍርሃት አንገት ያስደፋናል፣ ፍርሃት ሰዎች ያላቸውን ጥሩ ግምገማ ከመስጠት ይቆጥባቸዋል። ፍርሃት የሰው ልጅ ትልቅ ስጦታ የሆነውን ስብዕናን ይነጥቃል። »ዩሴም የሚናገረው የራሱን ተሞክሮ ተመርኩዞ ነው። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሞሀመድ ሙርሲንና የእስልምና ሀይማኖትን አንቋሿል ተብሎ ከግብፅ መንግሥት ወቀሳ ደርሶበት ያውቃል። ምንም እንኳን ዩሴፍ ይህንን ቢቋቋመውም የዛሬ አንድ ወር ገደማ የቴሌቪዥን ዝግጅቱ እንዲቋረጥ ተደርጓል። ዩሴፍ እገዳውን በተለመደው ምፀት ነው የገለፀው።« «በግብፅ ታይቶ የማይታወቀውን አይነት ነፃነት እያየን ነው፤ይህን ማየት የማይችል ካለ ምላሱ ይቆረጥ ሲል።» ስለሆነም አለ ዩሴፍ ዛሬ ባደረገው ንግግር ይህንን ፍርሃት ለመወጣት ኢንተርኔት ትልቅ ሚና ይጫወታል። « ምንም እንኳን የቴሌቭዥን ዝግጅቴ ቢቋረጥም ሀሳቦቼ በኢንተርኔት አሁንም እየኖሩ ነው ብሏል።

GMF Global Media Forum 2014 Auftritt Bassem Youssef
ሀሳብን በምፀት በመግለጽ የሚታወቀው ግብፃዊ ባሴም ዩሴፍምስል DW/K. Danetzki

ኢንተርኔት የመወደሱንም ያህል ከኢንተርኔት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ወንጀሎች ሳይነሱ አላለፉም። በኢንተርኔት የሚደረጉ ስለላዎች እና ሌሎች ወንጀሎች ከኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ባለፈ ለመገናኛ ብዙኃንም ተግዳሮት ሆኗል ብለዋል የዶይቸ ቬለ ስራ አስኪያጅ። የዶይቸ ቬለ ዓለምአቀፉየመገናኛብዙኃንመድረክ ነገም ይቀጥላል። በ dw.de ወይም dw.com ላይ በጠረቤዛ ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶችን እና የክብር እንግዶችን ንግግር በቀጥታ መከታተል ይቻላል።

ልደት አበበ

ተክሌ የኃላ